የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (41)

25. አትጨቃጨቅ

ሳታቋርጡ አመስግኑ ፣ ሳታቋርጡ ጸልዩ ፣ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚሉ የአዲስ ኪዳን መመሪያዎች ናቸው ። ሳያቋርጡ ፣ ሳይታክቱ ፣ ሁልጊዜ ሊደረጉ የሚገባቸው አምልኮተ እግዚአብሔር ያለባቸው ነገሮች ናቸው ። ቀኑን በሙሉ የሚዘንብ ዝናብ ሥራ አያሠራም ። ቀኑን ጨፍጋጋ ፣ ጎዳናውን ጠባብ ያደርገዋል ። ጭቅጭቅ የማይቆም ድምፅ ቢሆንም ትጋት አይደለም ። ጭቅጭቅ ቀንና ሌሊት ቢደረግም አለመታከት አይደለም ። ጭቅጭቅ ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም ታማኝ ሎሌ አያሰኝም ። ጭቅጭቅ ራስንና ሌሎችን ያለ ዕረፍት ማወክ ነው ። በደስታ ከእንቅልፉ የተነሣውን ሰው በጭቅጭቅ ቀኑን መቀማት ትልቅ ጠላትነት ነው ። ቤት አለኝ ብሎ ለዕረፍት እየገሰገሰ ያለውን ሰው በጭቅጭቅ መቀበል ኑሮውን መቀማት ነው ። በዓለም ላይ የገንዘብ ሌቦች እንዳሉ ሁሉ የሰላማችንም ሌቦች አሉ ። የገንዘብ ሌቦች ብዙ ጊዜ የማናውቃቸው ፣ የማያውቁን ናቸው ። የሰላማችን ሌቦች ግን የምናውቃቸው አጠገባችን ያሉት ሰዎች ናቸው ። በዕለት ጸሎታችን ልናሰማው ከሚገባው ልመና አንዱ “የሁከት ምክንያት ከመሆን አድነኝ” የሚል መሆን አለበት ።

ጭቅጭቅ ደጋግሞ አንድን ነገር መግለጥ ነው ። ልብስን ጨቅጭቀን ስናጥበው ልናነጻው እንችላለን ። ብዙ ጊዜ የሚታጠብ ልብስ ግን ማለቁ አይቀርም ። በመጨቃጨቅ ሰውን ልንለውጠው አንችልም ። ከስህተቱ በላይ የእኛን መጨቃጨቅ እየጠላው ይመጣል ። መጨቅጨቅ ምጣድ የጣዱ ሴቶች በቀዳዳው ንፋስ እንዳይገባ ፣ በር የሚዘጉ ሰዎች ብርድ እንዳይመጣ ትንሽ ሽንቁር እየፈለጉ የሚደፍኑት ነው ። መጨቃጨቅ ነፋስ አይግባብኝ የሚል የአትንኩኝ ባይነት ስሜት ፣ ከሰዎችም ፍጹምነትን የመፈለግ ስቃይ ነው ።

ጭቅጭቅ ያደረ ጠብ ውጤት ነው ። ጭቅጭቅ በንግግር ፣ በጠብ ፣ በበቀል ያለመርካት ውጤት ነው ። ጭቅጭቅ ትላንትን ዛሬ ላይ አምጥቶ መኖር ነው ። ጭቅጭቅ በራስ ስህተት ሳይሆን በሰዎች ስህተት ይቅርታ አልባ መሆን ነው ። ተጨቃጫቂነት ከልጅነት ጀምሮ ያልተገረዘ ጠባይ ነው ። በመጨቃጨቅ የምንፈልገውን የምናገኝ ሲመስለን ጭቅጭቅን እንደ ኃይል መጠቀም እንጀምራለን ። ወላጆችም ስላመኑበትና ስለሚያስፈልገን ሳይሆን ስለጭቅጭቃችን ሲሰጡን መጨቃጨቅን እንደ ሥልጣን እየቆጠርን እንመጣለን ። ጭቅጭቅ ከቅንዓት ውስጥ ይወጣል ። አትኩሮት መፈለግ የብዙ አቅመ ደካማ ሰዎች ጠባይ ነው ። የተረሳሁና ማንም የማያስበኝ ሰው ነኝ ብለው የሚያስቡ በሁሉም ነገር አትኩሮትን ይሻሉ ። አትኩሮትን ለማግኘት አንዱ ዘዴ ጨቅጫቃነት ነው ። መጨቃጨቅ ግን መጠላትንና መረሳትን ፣ እያሉ እንደሌሉ መቆጠርን ያመጣል ። ምናልባት ድንዙዝ ሰዎች አንድ ቃል ስለማያነቃቸው መጨቅጨቅን ሊወድዱት ይችላሉ ። የሚሠራውንና ለምን እንደሚኖር የሚያውቅ ሰው ግን ጭቅጭቅ ሰላሙን ይረብሽበታል ። አዎ ጭቅጭቅ ቤትን ያፈርሳል ። ጭቅጭቅ በፈጠራ ታሪኮች ፣ ቅንዓት በሚሰጠን ሥዕል ፣ በግምት ላይ ሊመሠረት ይችላል ። ብዙ ጉዳይ የሚያስጨንቀው ያ ሰው የእኛን ጭቅጭቅ መሸከም ሲያቅተው ሊለየን ይፈልጋል ። ጭቅጭቅን የፍቅር መግለጫ አድርገው የሚያስቡት ሰዎች ይኖራሉ ። የብዙ ሰዎች ችግር ፍቅራቸውን እንዴት እንደሚገልጡት አለማወቅ ነው ።

ጭቅጭቅ እኝኝ እንደሚል ዝናብ ነውና የመነሣት ፣ የመሥራት አቅምን ይበላል ። ከተጨቃጫቂ ሰው ጋር የሚኖር ሰው ቀኑንም ሌሊቱንም ይከስራል ። ተጨቃጫቂነት ጠባያችን ከሆነ መገንዘብ ያለብን ነገር አለ ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ መናገር እያስናቀ ጥቂት መናገር እያስከበረ ይመጣል ። የምንፈልገውን ማግኘት ያለብን እጅ ጠምዝዘን ፣ ወይም ያውላችሁ ተብለን ሳይሆን በክብር ፣ በደስታ ሊሆን ይገባዋል ። ሰውን አቅል ነሥተን የምንቀበለው ነገር ከቅሚያ የሚተናነስ አይደለም ። ተጨቃጫቂነት ለእኛ የሚያስደስተን ወይም የፍቅር መግለጫ መስሎ ከተሰማን ብዙ ሰዎችን ግን የሚያሳጣን ሊሆን ይችላል ። ተጨቃጫቂነትን ለማስወገድ የምንለምነው አምላክ ያለን ሰዎች መሆናችንን መቀበል አንዱ ነው ። ሰዎችን ብዙ የተለማመጥነውን ያህል እግዚአብሔርን ብንለምነው ለሰዎቹም እንተርፍ ነበር ። አንደበት መክፈቻ ብቻ ሳይሆን መዝጊያም የተበጀለት ዝም ማለት ስላለብንም ነው ። ሁልጊዜ በመናገር ብቻ አጠገባችን ያለውን ሰው ልንለውጠው አንችልም ። በማለፍና ዝም በማለትም ራሱን እንዲያይ እናደርገዋለን ። ሰው እኛ ስላየነው አይለወጥም ፣ ራሱን በትክክል ሲያይ ግን ለመለወጥ ይነሣሣል ። ጭቅጭቅ የተሰባበረ መስተዋት በመሆኑ መልክን አያሳይም ። ሰዎች በእኛ ጭቅጭቅ ውስጥ ሊደበቁ ይችላሉ ።

ጭቅጭቅ እያደገ ሲመጣ ከግለሰብ አልፎ ሕዝብን ወደ መጨቅጨቅ ሊያልፍ ይችላል ። ስብከታቸውን ጭቅጭቅ የሚያደርጉ ሰባኪዎችም የዚህ ያልታረመ ዕድገት ውጤት ናቸው ። አንድን ነገር መደጋገም ፣ በእኔ እውቀት ብቻ መቀበል አለባችሁ ፣ ለምን ? ብላችሁ አትጠይቁ የሚሉ ሰዎች ጭቅጭቅን እንደ መሣሪያ ይጠቀሙታል ። ሁሉም ነገር በፕሮግራም እንደሚደረግ የማይገነዘቡ መጨቃጨቅን ይወዳሉ ። ተጨቃጫቂዎች የጊዜ ሰሌዳን አይቀበሉም ። ራሳቸውን ብቻ ስለሚያዳምጡ እገሌ ሊቸግረው ይችላል ብለው አያምኑም ። እጅ በመጠምዘዝ ስለ መቀበላቸው እንጂ በዚያ ሰው ልብ ውስጥ ስለሚያጡት ክብር አያስቡም ። ጨቅጫቃ አለቆች ከማትረፍ ይከስራሉ ። ጨቅጫቃ አባወራዎች ልማዳቸው ነው እየተባሉ ይናቃሉ ። ጨቅጫቃ አፍቃሪዎች መንገድ ላይ ይከዳሉ ፣ ይቀራሉ ።

አንተ ግን ከጨቅጫቃነት ውጣ ። ሰላም ስትነሣ መጀመሪያ አንተ ሰላም አጥተሃል ። የምትከስረው ሰላምና ያጣኸው ነገር የሚመጣጠን አይደለም። ሰላም ከዋጋ በላይ ነው ። ሰላም ሳለ የሚናቅ ከሄደ በኋላ ግን በውድ ዋጋ የማይገኝ ነው ። አንድ ጊዜ ኮስተር ብለህ ተናገር ። ውሳኔ የሚባል ነገር አለና ወሳኝነትህን አሳይ እንጂ አትጨቃጨቅ ። መወያየት መልካም ነው ። አጉረምራሚነት የአውሬ ጠባይ ፣ ተጨቃጫቂነትም የከንቱ ሰው መገለጫ ነውና አርቀው ። ከእንቅልፍ ስትነቃ መጀመሪያ የምታገኘው ራስህን ነውና ከራስህ ውጭ አንተን የሚረዳህ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ስለዚህ በመጨቃጨቅ ሰዎችን ወተት አዝንቡልኝ አትበል ። ፍቅርህንም በተግባር ግለጠው እንጂ በጭቅጭቅ የሚገለጥ ፍቅር እንደሌለ አስተውል ። ከሁሉ በላይ ለማንም ሰላም ማጣት ምክንያት አትሁን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ