ሁኔታዎችን ተቀበል/2
ተሰባሪ ነህና የሰው ንብረት በአደራ አትቀበል ። ግድ የሆነብህ እንደሆነ ለቤተሰብህ አሳውቅ። ዛሬ መክፈል እየቻልህ የሰው ብድር ይዘህ አትተኛ ። ነውር ነው ። ለምነህ ተበድረህ ለምነህ መስጠት አለብህ ። ያ ሰው ለሌላ እንዳያበድር ክፋትን እያለማመድከው ነውና ብድርህን ዛሬ ክፈል ። የሰው ገንዘብ አይለፍብህ ። የድሀን ንብረት አትቀማ ። ትልቁ ዘመድ ሕዝብ ነውና በገንዘብህ አትመካ ። ሕዝብ የተናደባቸው ሰዎች ገንዘብ አላኖራቸውም ። የባለሥልጣኖች መጨረሻ የማያምረው ገንዘብ ስላጡ ሳይሆን ሰው ስላጡ ነው ። ፈጥነህ ስለ መፍትሔው አስብ እንጂ ችግር ላይ አትቆዝም ። በሙላትህ ብቻ ሳይሆን በጉድለትህም ሳቅበት ። ሊያስለቅስህ የመጣውን አትሸነፍለት ። ሁሉን ችግር ከሰይጣንና ከኃጢአት ጋር ከሚያያይዙ ሰዎች ራቅ ። ስለ ሰይጣን ቀኑን ሙሉ የሚያወሩ ወዳጆቹ እንደሆኑ አትርሳ ፣ ቤተ ዘመድ አይረሳሳምና ። ዳን ላለው መድኃኒት አለውና ብዙ አትንከራተት ። ምንም ብትደበቅ ሞትን አታመልጥም ፣ የተጣራ የሚተነፍሱ ፣ በልዩ ቤት የሚኖሩ እነ ማይክል ጃክሰን ከሃምሳ ዓመት አልዘለሉም ፣ ለመቶ አቅደው ግማሽ ላይ ቀሩ ። አምነህ እንጂ ፈርተህ አትሙት ። በሁሉም ነገር ጠበቃና ሐኪምን ማማከር አታብዛ ። ከስጋታቸው የተነሣ ሰላም ይነሡሃል ።
ሁኔታዎችን እንድትቀበል ሁነህ አላደግህም ። አሁን ግን ተለማመድ ። መዋደድ እንዳለ መጣላት ይኖራል ። አብሮህ ያለው ድንገት በሞት ይወሰዳል ። ቀን ሲከፋ ልጅህን ጠላት ይሆንሃል ። ትዳርህም በጓደኛህ ሊቀማ ይችላል ። የሚቀጥል እንጂ የሚጀምር ነገር በዓለም ላይ የለም ። እነዚህ የአካል ክፍሎችህ የሚያምፁበት ፣ አንሠራም ብለው አድማ የሚመቱበት ጊዜ አለ ፣ ሽንቱም ሊያመልጥ ይችላል ፤ መከላከያ ሠርተዋልና ያንን በደስታ መጠቀም ነው ። ሁሉም ወደዚያው ነውና አትደነቅ ። ለበሽታው ስም ስለበዛለት እንጂ አዳኙ አንድ አምላክ ነው ። ሁሉንም ነገር በዝርዝር ማወቅ አትፈልግ ። ስለ አንድ ሰው ከመጠን በላይ የሆነ መረጃ መያዝ እመነኝ እንድታብድ ያደርግሃል ። የተሰጠህ ዕድሜ እንኳን ሰው ጓዳ ልትውልበት ለራስህም ጉዳይ በቂ አይደለም ። ዕድሜ የጀመረው በሺህ ዓመት ነበረ ። ታዲያ ለሺህ የታቀደ ፕሮግራም በሰባ ዓመት ይፈጸማል ብለህ አታስብ ። ዓለምን የጀመራት እንጂ የፈጸማት ማንም የለም ። እኔና አንተም አንድ ቀን እንፈርሳለንና ቤቴ ፈረሰ ብለው እጅግ አትዘን ። ሰውን የምትሳደብ ፣ በትችት ዘመንህን የምትገፋ ከሆነ ራስህን አታታልል ፣ አንድ ችግር እያሰቃየህ ነው ። ምናልባት አሰቃቂ የምትለው የጤና ችግር ፣ ሰው ጋ መቅረብ የሚያሳፍርህ እንከን አለብህ ማለት ነው ። ራስህንም አሳንሰህ ስላየኸው የበለጡህን ሰዎች ዝቅ ስታደርጋቸው እኩል የሆንክ ይመስልሃል ። ለዚህ የሚረዳህ ያለህበትን ነገር መቀበል ብቻ ነው ። አዲስ ነገር የለም ፣ ሁሉም የሚደገም ነው ። አዲስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። መጋመድም መፋታትም የነበረ ያለ ነው ፣ ወደ ችግር አትሂድ ፤ የመጣን አለመቀበል ግን ራስን ለእብደት መሸጥ ነው ። በድግስ የጀመርከውን ስትፈጽመውም ደግሰህ ይሁን ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” ይላሉ ። ሬዲዮ ላይ ወጥተህ ፣ ቀራጭ አቁመህ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረድ” አትበል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ያንተን ጓዳ ሊያበጅ የራሱም ችግር ጊዜ አልሰጠውም! ቡና መጠጫ ፣ የቀኑ ማደንዘዣ ያደርጉሃል ! ከተፈጥሮ ጋር ግጭት ውስጥ አትግባ ! ለምን እንዲህ ሆነ ብለህ ራስህን አታድክም ። ለብልሽት ምክንያት አትሁን ፣ ብልሽት ግን እንዲገድልህ አትፍቀድ !
ከአገር አሳደዱህ ? በቃ ተቀበለው ። ምድርና ሞላው የእግዚአብሔር ነው ። አብርሃምም ፣ ሙሴም ፣ ዳንኤልም ቅዱሳኑ ሁሉ ስደተኛ ነበሩ ። አንተ የምታሟሸው ችግር የለም ። አወገዙህ ? አጥፍተህ እንደሆነ ተመለስ ፣ አላጠፋህ እንደሆነ እግዚአብሔር በሰው ምስክር የሚቀጣ አምላክ አይደለም ፣ የራሱ ሚዛን አለው ። ቀኑን ሙሉ አሳደዱኝ እያልህ መሳደብ ፣ ተወገዝሁ ብለህ ስታወግዝ መኖር ጥቅም የለውም ። ሁኔታዎችን ተቀበል ። ቀኑ ሲከዳህ ዞር በል ። አዎ የለፋህበት ንብረትህ በቁምህ ሲወረስ ይቆጫል ። ሞተህም ስለማታየው እንጂ የሚካፈሉት እንዲህ ነውና ዋናው ለመኖርህ ዋጋ ስጥ ። ዕራቁትህን መጥተህ ዕራቁትህን የምትሄድ መንገደኛ ነህ ። ሀብትህ ሁሉ የቀን አበልና የመንገድ ስንቅ ነው ። ስንቅ መንገዱ ሲያበቃ ያበቃል ። ዋናው ገበታ በሰማይ ነው ። አይዞህ ወዳጄ ምንም ነገር ውስጥ ሁን ሁኔታዎችን ተቀበል ። “የማይጋፉትን ግንብ ዞረው ያልፉታል” እንዲሉ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም.