የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተወደደ ሰዓት አሁን ነው

“በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና ፤ እነሆ ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው ።” 2 ቆሮ. 6 ፡ 2 ።

ብዙ ሰው ሞቶ ቀብረናል ። ዘመናት ቢያልፉም ከሕሊና ጓዳ የማይወጣ አንድ ሟች ይኖራል ። ይህ ወጣት ብዙ አቅዶ ሁሉም ነገር ድንገት የተናደበት ፣ ሩቅ አስቦ መንገዱ ያጠረበት ነው ። ቆሞ የማውቀው ወድቆ አየሁት ፣ ያ ለጉልበት ሥራ የማይበገር በሰው እጅ ወደቀ ። አምስት ሙሉ ልብስ ከጣሊያን አገር አስመጣ ። ልብሱ ሲደርስ እርሱ አልጋ ላይ ወድቋል ። ከ27 ዓመት በፊት የሞተው ያ ወጣት ዛሬም ትዝ ይለኛል ። ታሞ ልጠይቀው እመላለስ ነበር ። መታመሙን ማመን ቸገረኝ ፣ ሁሉም ነገር ጥድፊያ ሆነበት ። የትልልቅ ቤት ባሕል ልዩ ነውና ሰው አይስማ ተብሎ እፍን እፍን ተደርጓል ። እኔን መግፋት ከብዶአቸው ወይም ያስፈልገዋል ብለው መሰል በየጊዜው ይጠሩኛል ። ይህን ወጣት ሳበረታታ ወደ ቁም ሳጥኑ አመለከተኝ፡- “ለአዲሱ ዓመት ከእነዚህ ልብሶች አንዱን ለብሼ ብሞት አይቆጨኝም ፣ እባክህ ጸልይልኝ” አለኝ ። የተመኘው ሳይሆን ሞተ። ይህን ስጽፍ እንኳ ልቤ ያዝናል ፣ ስሜት ይታገለኛል ። ብዙ ወጣት ቆሜ ቀብሬአለሁና ። የኢትዮጵያ ወጣት ብቅ ሲል ፣ የመኖርን መቅድም ማንበብ ሲጀምር በከተማው በሽታ ፣ በዳር አገር ጦርነት ይቀጥፈዋል ። በቅጠል የቀረው የአገሬ ወጣት እጅግ ያሳዝነኛል ።

ዓመት ሙሉ ኖረው የአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ የሚሞቱ ብዙ ናቸው ። አንዱ በዓል ሲያከብር አንዱ የሞተበትን ይቀብራል ። አንዱ መንገድ ሲወጣ ፣ አንዱ ይወልዳል ። የልጅቱም ስም መስከረም ተብሎ ይሰየማል ። ይህ ወጣት እየለመነ ለአንድ ቀን መቆም ፣ ልብሱን መልበስ አልቻለም ። እኛ ግን ሳንለምን ይህን ቀን አይተናል ።

ብዙ ነገሮቻችን በቀጠሮ ውስጥ ናቸው ። የፍርድ ቤት ጉዳያችንን ጨርሰን ፣ ቤታችንን ገንብተን ንስሐ ለመግባት እናስባለን ። ምቹ ቀንን በመናፈቅ ዓይኖቻችን አንጋጠው ይኖራሉ ። ምቹ ሰዓት ግን አሁን ነው ። በዓለም ላይ የተወደደ ቀን አሁን መሆኑን ቃሉ ይነግረናል ። መጽሐፍ ለማንበብ ቀጠሮ የምንሰጥ ምስኪኖች ነን ። ነገ ላይ ዓይናችን ይደክማል ፣ ማንበብም ይሳነናል ። አገር ለመጎብኘት እርጅና ዘመንን እንጠብቃለን ። ያን ጊዜ እግር ይያዛል ፣ ጉልበት ታማሚ ይሆናል ። አገር ጉብኝት ያለ እግር አይሆንም ። ገንዘብ ስላለን ብቻ አንጎበኝም ፣ እግር ያስፈልጋል ። ውለታ የዋሉልንን ደኅና ነገር ይዘን ለመጠየቅ ጊዜ እየጠበቅን ነው ። ከትልቁ ልብ ጋር ትንሹ ስጦታ ትልቅ ነው ። እናቶቻችን አንድ ፍሬ የቡና ሲኒ ስጦታ ሲለዋወጡ እናውቃለን ። እኛ የልባችንን ትንሽነት በትልቅ ስጦታ ለመሸፈን እንሞክራለን ። ስእለት እንኳ ስንሳል ትልቅ ነገር አመጣለሁ ካላልን ጸሎታችን የሚሰማ አይመስለንም ። ለውለታው መታሰቢያ ትንሽ ነገርም መሳል በቂ ነው ። በሰው ላይ የለመድነውን በእግዚአብሔር ላይ ደግመነው ይታያል ።

ሱባዔ ገብተን ብንጸልይ ፣ ለወገን ብንማልድ መልካምና አስፈላጊ ነው ። ለጸሎት ዘግቼ ነበር የሚል ጉራም ብዙ ነው ። እግዚአብሔርን ግን አሁን አፍ ከልብ ሆነን ፣ በተሰበረ መንፈስ በእንባ ለደቂቃ ብንለምነው ይሰማናል ። እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ ጸሎትን የሚሰማበት ቦታ የለም ። በተለየ ልብ የለመኑትን ግን ይሰማል ። በዓለም ላይ የተቀመጠ ምቹ ቀን ፣ የተወደደ ሰዓት የለም ። የመንግሥተ ሰማያትን ኑሮ እንናፍቃለን ። የገነት ኑሮን ግን በምድር ላይ በዚህ ጊዜ ብለን አንናፍቅም ። የገነት ኑሮ ከፈለገን አሁንን መጣጣም ነው ። እኛ የአሁን ሰዎች ሆነን ሌላ ጊዜ እንጠብቃለን ። ድሆችን ለመርዳት የተወደደው ጊዜ ሀብታም መሆን አይደለም ። ሀብታሞች የሚሰጡ ይመስላሉ እንጂ አይሰጡም ። አንዳንዶቹ የገዛ ሚስታቸውን በችግር የሚቀጡ ናቸው ። የሚሰጠው እጅ ሳይሆን የቸርነት ልብ ነው ። ከገንዘብ በፊት መገንዘብ መቅደም አለበት ። የተወደደው ሰዓት አሁን ነው ። እርሱም ካለን ላይ ማካፈል ነው ። ቢኖረን ለእግዚአብሔር ብዙ የምንሰጥ ይመስለናል ። ካገኘን በኋላ አገልጋዮቹ ብሩን በሉት የምንለው ላለመስጠት እንዲያግዘን ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን በአግባቡ የሚበላው አገልጋዩ መሆኑን ማወቅ አለብን ።

ሕይወታቸውን ለአገርና ለወገን መሥዋዕት አድርገው ለሰጡት ወገኖቻችን የምስጋናና የአድናቆት ቀን ካሰብን ዓመታት አልፈው ይሆናል ። በሕይወታችን ላይ አሻራቸውን ላሳረፉት ውዶች ያደረጉልንን እንዳልረሳን መንገር እንፈልጋለን ። ግን መቼ ነው ? አይታወቅም ። ሰዓቱ አሁን ነው ። ወላጆቻችንን ከጠየቅን ብዙ ጊዜ ሆኖናል ። አዎ የሰው አገር እንዳሰብነው አልሆነም ። አፍረን ፣ ምን ይዤ ልደውል ብለን ቀርተናል ። ግድ የለም ፣ ድምፃችንን ዛሬ ሲሰሙ መሬት የሚሰሙ ወላጆች አሉ ፣ ስእለታቸውን ዛሬ ይዘው ለመሮጥ ዝግጁ ናቸው ። አለሁ እንበላቸው ። አለኝ ከማለት አለሁ ማለት ይበልጣል ። አለኝ ለማለት አለሁ ማለት ያስፈልጋል ። መኖር ቀዳሚው ነው ።

የበደልናቸውን በአካል አሸንፈናቸው ፣ በልቡናችን ግን ተሸናፊ አድርገውናል ። በሥጋ ገድለናቸው በመንፈስ ግን ሙት አድርገውናል ። ዘርፈናቸው ሜዳ ጥለናቸዋል ፣ እኛ ግን ቤት እያደርን ይበርደናል ። ሁልጊዜ የሕሊና ቍስለኛ ያደረጉንን ወገኖች ይቅርታ ለመጠየቅ ሰዓቱ አሁን ነው ። ያለን ቀኑ ሳይሆን ያለን ሰዓት ነው ። ያለን ሰዓት ሳይሆን ያለን አሁን ነው ። አዲሱ ዓመት አዲስ ነገር ካላደረግንበት ከቍጥር ውጭ አይደለም ። ቍጥር ማለቂያ የለውም ፣ እኛን ይጨርሰናል ። እንደ ትላንቱ እንደ አምናው ለመኖር ዘመን አልተጨመረልንም ። አዲስ መንገድ ያስፈልገናል ። የተወደደ ሰዓት የጸሎት ሰዓት ነው ። የተወደደ ሰዓት አሁን ነው ። የተወደደ ሰዓት ሥራዬ ምንድነው ? ማለት ነው ። አሁን ከተነሣን እግዚአብሔር እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል ። መጻፍ የምትፈልጉ አሁን ጻፉ ። መማር የምትሹ አሁን ጀምሩ ። እግዚአብሔር ምኞታችሁን ሳይሆን እንቅስቃሴአችሁን ይባርካል ።

እንኳን አደረሳችሁ ! ቡሩክ ዓመት ይሁንላችሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ