ንግግር ኃይል ነው ። በንግግር ጦርነት ይጀመራል፣ ጦርነት ይቆማል። በመናገር ኃይል እናገኛለን፣ ኃይል እናባክናለን። ኃያል ሥራዎች የሚሠሩት ከንግግር ይልቅ በዝምታ ነ ው። እግዚአብሔር ፍጥረትን በሦስት መንገድ ፈጥሯል። በዝምታ፣ በመናገርና በተግባር ። ካለመኖር ወደ መኖር ፣ ከሌለ ነገር ወዳለ ነገር ያመጣቸው ፍጥረታት በዝምታ የተፈጠሩት ናቸው። ንግግር መልካም ፣ አስፈላጊና ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። “ካልተናገሩ ብልሃቱ፣ ካልታረደ ስባቱ አይታወቅም” ይባላል። ንግግር ግን ኃይልን ያባክናል። ጥልቅ ጥበብ፣ ብርቱ ሠራተኛነት፣ ቋጠሮን መፍታት፣ ሳይሸበሩ መቆም፣ አስተውሎት ዝም የሚሉ ሰዎች አቅም ነ ው። ሁልጊዜ ዝምታ፣ ሁልጊዜ ንግግር አስፈላጊ አይደለም። ሁሉም አይነገርም፣ ሁሉም ነገር ዝም አይባልም።
አንዲት ሴት ለሥራ ጉዳይ እያለች ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ድረስ ትመጣለች። ባልዋም ልጅዋም የሚያውቁት ለሥራ መሄድዋን ነው። ይህች ሴት ግን በካንሰር ሕመም ውስጥ እያለፈች ነው። ከስምንት ጊዜ በላይ ከባድና አስቸጋሪ የሆነውን ኬሞቴራፒ ወስዳለች። ቀጥሎ የጨረር ሕክምና አድርጋለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ የሥጋ ዘመዶች፣ የትዳር አጋር፣ ልጅዋ አያውቁም። በመጨረሻ አቅም አጣች፣ ሆስፒታል ተኛች ። በመጨረሻው ሰዓት ላይ ሁሉንም ሲያውቁ በጣም ተጎዱ። ወዲያው ዐረፈች። ይጨነቃሉ፣ መሸከም አይችሉም የምንላቸው የተሻለ አቅም ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንድ ዝምታ አላስፈላጊ ነ ው። ሰዎች በቁመናዬ እንጂ በሞቴ ሊያግዙኝ አይችሉም በማለት የሚናገሩ ሰዎች ሊደነቁ ይገባል ። ሁሉ በሆዱ ነው የሚለው ሙገሳ ብዙ የአእምሮ ታማሚዎችን ያፈራ ነው።
የሚናገሩ ሰዎች ማኅበረሰቡ ያወጣላቸው ፣ ለራሳቸውም ያወጡት ስም አለ። ምንም አያውቅም፣ ሆዱ ባዶ ነው የሚል ነው። በርግጥ የሚራሩ ሰዎች በአብዛኛው ተናጋሪዎች ናቸው። ተናጋሪዎች የድብቅ ሕይወት ስለሌላቸው ሁሉንም በግልጽ ያወራሉ። ነጻነትና ደስታ አላቸው።
በጣም ተናጋሪዎች፣ ተናግረው የማይረኩ ፣ ስለ ሁሉም ነገር የመናገር ግዳጅ ያለባቸው የሚመስላቸው ፣ አላውቅም ማለትን የማይወዱ ሰዎች አሉ። ዓለም ድምፅ እየሰጠ ያለው ለተናጋሪዎች ነ ው። ጥሩ የሚናገሩ ጥሩ ተግባር የሌላቸው አያሌ ናቸው ። በንግግራቸው ተጣጥፈው ማለፍ የሚችሉ ጎበዝ ይባላሉ። እውነት መናገር ሳይሆን ውሸትን እውነት አስመስሎ ማቅረብ መደነቅ እያስከተለ ነው። አፉን አይተው ያገቡት፣ ንግግሩን ሰምተው የመረጡት ሲያስለቅስ ይኖራል። እግዚአብሔር የአፍ ክብርን ሳይሆን የልብ መገዛትን ያያል። “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤”(ማቴ 15፣ 8)። የዛሬ ወጣቶች ንጹሕ ልብስና ንጹሕ ንግግር አላቸው። ንጹሕ ኑሮን ግን እያጡ ነው ።
ንግግር የሚያበዙ ሰዎች ሥራ ላይ የሚገኙ አይደሉም። ንግግር የልግመኞች ምጽዋት ናት። ንግግር መልካም ነው፣ ንግግር ብቻ መሆን ግን ቃልቻ ወይም ቃል ብቻ የሚያሰኝ ነው። ቃል ብቻ ወይም ቃልቻ ይሆናል። ሰይጣን ቃል ብቻ የሆነ ሰው ሁነኛ አገልጋዩ ነው:: “ሁሉ ሆነ ቃልቻ፣ ማን ይሸከም ስልቻ” እንዲሉ። ቃልቻ ይህን አደርግልሃለሁ፣ ይህን እፈጽምልሃለሁ በማለት ያወራል ግን አያደርገውም። ባለሙያ ሰዎችን ተመልከቱ ፣ ንግግራቸው የተቆጠበ ነው። ንግግር ጊዜ ይፈጃልና ተናጋሪ ሰው ለሥራ ጊዜ ያጥረዋል። ተናግሮ ይረካልና ለቸርነት እጁ ካንጋሮ ነው። ተናጋሪዎች ያዘምታሉ እንጂ አይዘምቱም። “ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣም” ይባላል። ፍቅራችንንም በጣም ማውራት ተግባር ያሳጣል። ዓላማን ሲዘረዝሩ መዋልም ከፍጻሜ ይገታል። የሚያደርጉ ሰዎች አያወሩም። ከውሻ እንኳ የሚጮኸው ሳይሆን ዝም የሚለው ይናከሳል።
ችግሩ ያለው ዝምታ ላይ ወይም ንግግር ላይ አይደለም። ዝምታው ማድፈጥ አይሁን። ቃልም ቃል ብቻ አይሁን። ሃይማኖታችን “ቃል ሥጋ ሆነ” የሚል ነው። ተዋሕዶ ማለትም የማይታየው የሚታይ ሆነ ማለት ነው። ቃላችን የሚታይ ይሁን። ሰዎች እኛን አይተው እግዚአብሔር በምድር ታየ፣ ዛሬም አምላክ ሰው አለው ይበሉ። ሁልጊዜ ቃል ብቻ ከሆንን በሰው ሞት ተሳላቂ እንሆናለን። እንናቃለን። የተሳለ የግድግዳ አንበሳ ወይም ሥዕል እንሆናለን። የተሳለ አንበሳ አጠገብ ሻይ ይጠጣል፣ እውነተኛው አንበሳ አጠገብ ግን የሚደፍር የለም ።
ንግግራችንን አሳጥረን ወደ ተግባር እንሂድ። በአገራችን ስመ አምላክ በሃይማኖት ሥፍራ ሲጠራ ይውላል፤ ያድራል ። ዛሬ ግን በሬድዮ በቴሌቪዥን ሲጠራ ይውላል። ግን ቃል ብቻ ነው። ሁሉም ያወራል፣ የሚሠራ እየጠፋ ነው። ቻይናዎቹ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ሌላ አገር አላቸው ወይ? ከእናቱ መቀነት የሚሰርቅ የመጨረሻው ክፉ ሌባ ነው። እናቱ ጋ ያለው ለራሱ የተቀመጠ ነበር። እናት አገሩን የሚሰርቅ ጨካኝ ሌባ፣ ልጅነቱን የካደ ነው። እንዲህ ላድርገው የሚል የለም። እንዲህ አልተደረገም የሚል ግን ብዙ ነው። ሁሉም ሰው ደጃፉን ካፀዳ አካባቢው ይፀዳል። ትንንሽ ምንጮች ሲያብሩ የዓባይን ወንዝ ይወልዳሉ። ብቻ ተናጋሪ በዛ። ንግግሩን አይተው ለጋብቻ ይመርጡታል፣ ለአገር ያጩታል ፤ ከዚያ በኋላ እህ እያሉ መኖር ነው። የፊት ምስጋና ለኋላ ሐሜት ያስቸግራል ። አዎ ሁሉ ሆነ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ ?
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 24 /2017 ዓ.ም.