የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍርሃት አያልቅም

ፍርሃት የነፍስ ሞገድ ነው። ሰው በራሱ ፣ በሰዎችና በእግዚአብሔር ላይ እርግጠኝነት ሲያጣ ፍርሃት ይገጥመዋል። ፍርሃት ጥርጣሬ ነ ው። ፍርሃት የእምነት ተቃራኒ ነው። ፍርሃት የጨበጡትን ፣ ያለውንና የሚመጣውን አለማመን ነው። ፍርሃት ተገቢና ተገቢ ያልሆነ ብለን ለሁለት እንከፍለዋለን ። ተገቢ ፍርሃት እግዚአብሔርን መፍራት፣ ወንጀልንና ቅጣትን መፍራት ነው፡፡ ይህ ፍርሃት በአምልኮ፣ በሞራል፣ በፍትሐ ጽድቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ለሁሉም ተግባር ዋጋ እንዳለው አድርጎ የሚጠነቀቅ ነው። ሁለተኛው  ተገቢ ያልሆነ ፍርሃት ነው ። ሁሉንም ነገር በስጋት ማየት፣ ቀጥሎ ጥፋትና ሞት ሊመጣ ይችላል እያሉ መበርገግ፣ እየበሉ ቢርበኝስ ብሎ መጨነቅ፣ ሁሉንም ሰው፣ ሁሉንም ተፈጥሮ ማመን አለመቻል፣ ቀጥሎ እንዲህ ቢሆንስ እያሉ ስጋትን ማመን ነው።

አለመፍራት ተገቢ ያልሆነበት ጊዜ አለ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው በሕይወት ዘመንህ ካጋጠሙህ አራዊት በጥቂት ብቻ እንደሚለይ እወቅ ይባላል። የሰው ልጅ ከሁለት አንዱን ካጣ ፍርድን ቆርጥሞ ይበላል። እግዚአብሔርን መፍራት አሊያ ሰውን ማፈር አለበት።  እግዚአብሔርን የሚፈራ መንፈሳዊ ነው። ሰውን የሚያፍር ለክብሩ ሲል ከነውር የሚርቅ ነው። ሰውን በማፈር የማይሰክሩ፣ የማያመነዝሩ፣ የማይሰርቁ  አሉ ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ፣ ሰውን የማያፍር በድሆች እንባ የሚራጭ፣ በምስኪኗ  ልቅሶ የሚዝናና ፣ ግፍን የማይጠግብ፣ ያለውን እንጂ የሌለውን ሰው መውደድ የማይችል፣ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ እግዚአብሔርን የማያምን፣ ስለ ሰውነት እያወራ አራዊት የሆነ ፍጡር ነው። እግዚአብሔርን የማይፈራ ፣ ሰውን የማያፍር ፍትሕን በገንዘብ የሚሸጥ፣ የቅን ዳኝነትን የማያውቅ ፣ ለሚፈስስ እንባና ደም ግድ   የሌለው ፣ በጉቦ  የሰከረ፣ በመበለቲቱ ጭንቀት የሚደስት ነው። ይህንን የሚነግረን የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 18 ነ ው።

ተገቢ የሆነ ፍርሃት የሌለው ወይም የማይፈራ ሰው ጤንነቱ፣ የአእምሮ ሚዛኑ አጠራጣሪ ነው። መዋሸትን ፣ መግደልን ፣ መስረቅን፣ ሴቶችና ሕፃናትን መጉዳትን የማይፈራ አእምሮው ልከኛ አይደለም። ፍርሃት ኃጢአት ነው፣ እርሱም አለማመን ነው፤ አለመፍራት ኃጢአት ነው፣ እርሱም ግፍን መሥራት ነው። እግዚአብሔርን ፣ ሕግን ፣ ታላላቆቹን የማይፈራ ሰው አሳፋሪ ነው ። የማይፈራን እንፈራዋለን ። እርሱም ጨካኝ ነው። ከእኔ በላይ ነፋስ እንጂ እግዚአብሔር የለም ብሎ የሚያስብ ፣ ልቡ የሰይጣን ዙፋን የሆነ ነው። የሚፈራን ሰው እንወቅሰዋለን። ይህ ሰው ባለ ማመን የሚሰቃይ ነ ውና።

ለመኖር እርግጠኛ አለመሆን፣ ሁሉን መጠራጠር፣ ለደግነት ክፉ ትርጉም መስጠት፣ ለማቀድና ለመፈጸም ፣ ለመጀመርና ለመጓዝ አቅም የሚያሳጣ ፍርሃት ይገጥማል። ፍርሃት እጦት የሚወልደው ሳይሆን ማግኘት የሚያመጣው ነው። እጦት የሚያመጣው ፍርሃት ገደብ አለው፣ ጨካኝ አንዳንዴም ቆራጥ ያደርጋል። ማግኘት የሚያመጣው ፍርሃት ግን ተሸናፊና ምርኮኛ የሚያደርግ ነው። እጦት የሚያመጣው ፍርሃት በማግኘት ይስተካከላል ፣ ማግኘት የሚያመጣው ፍርሃት ግን ስስታም እያደረገ ወደማይደረስበት ደሴት የሚያስጉዝ ነው።  ዐሥር ቤት የሚያሠራ አንዱም ውስጥ የማያሳድር ነው። በመጨረሻ የሚፈልጉትን ባለማወቅ ከንቱና ጠበኛ ሰው የሚያደርግ ነው። ጳውሎስ ከክርስትና በፊት ሁሉ የሚፈራው ሰው ነበር። ሰው የሚፈራው በክህነት ፣ በሽበት ክብር ሳይሆን በአሳዳጅነት በገዳይነት ነበር። አሁን ግን አገኘ ፣ ተሳካለት፣ ቀን ወጣላት ፤ የክርስቶስ ሆነ። ብዙ ዓይነት ፍርሃት ከበበው ። አዎ ሬሳ አይፈራም፣ የሚፈራ በሕይወት ያለ  ነው።

ፍርሃ ት ባንፈልገውም የሚፈልገን ነ ው። ብንሽሸውም ይከተለናል። ፍርሃት ካልገሠጹት መቆሚያ የለውም። በቃህ ካላሉት አይቆምም። በዚህ ዓለም ላይ ለመኖር እምነት አስፈላጊ ነው።  ፍርሃት ባለማመን እየናጠ ይመጣል። ይህ ፍርሃት ገደብ ካላገኘ የሚበሉትን ምግብ ፣ የሚጠጡትን ውኃ መጠራጠር ይጀምራል። ምግብና ውኃውን ራሱ ቢያዘጋጅስ ? ብንል እህሉ ከማሳው ፣ ውኃው ከቧንቧው ቢመረዝስ ብሎ መስጋት ይጀምራል። የብዙ ሰው ሕይወት በፍርሃት እየተመሰቃቀለ ነው፡፡ ዘመናዊነት ፍርሃት ይዞ መጥቷል። ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው ፍርሃት ግን ወጥመድ ነው። እግር እያለን የማንራመደው፣ እጅ እያለን የማንክበው በፍርሃት ምክንያት ነው። ፍርሃት ውስጣዊ ብርድ ሆኖ ያንዘፈዝፋል ። አጠገባችን የተኛ ሰው ያየነውን ሕልም በጋራ ማየት አይችልም፣ እንዲሁም አጠገባችን ያሉ ሰዎች የምናልፍበትን ፍርሃት ሊረዱ አይችሉም ። ውስጥ የገባ ብርድ ቢደራርቡበት  ጋብ አይልም። ፍርሃትም ሰው ቢከበን እንኳ ላይርቅ ይችላል። አጥሩ፣ ካሜራው፣ ዘበኛው ፍርሃትን ያባብሳሉ ። የጤና መረጃዎች ፈሪ እያደረጉ ይመጣሉ።

ይቀጥላል

#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ