ቤቴን ሠርቻለሁ፣ ጡረታዬን አስተካክያለሁ፣ ልጆቼን ቦታ ቦታ አስይዣለሁ ከዚህ በኋላ ዐርፌ መብላት መጠጣት ነው አትበል። ቤትም ጡረታም መተዳደሪያ እንጂ ሕይወት አይሆኑም። ልጆች ቦታ ቢይዙም ይህ ዓለም ለአንድ ራስም አስጨናቂ ነው። ብኖር ለጌታዬ እኖራለሁ በል። ቢሳካ ደስታ ነው፣ ባይሳካ ምኞትህ ዋጋ ወደሚያገኝበት ዓለም ትሄዳለህ። እንኳን አንተ ታላላቅ ነገሥታት ግቢያቸውን ደሴት ላይ ፣ መታጠቢያ ቤታቸውን በወርቅ ሠርተው ነበር። እንኳን መኖሪያ መቀበሪያ አላገኙም። ማን እንዳረፈ ታርፈለህ? ደግሞም ንብረት አያሳርፍም ፣ ሰውም ልብ አይጥሉበትም። ወደ እኔ ኑ ያለው ወደ ልቡ የጋበዘን ክርስቶስ ብቻ ዕረፍት ነው።
እኔን ካልነኩኝ ስለ ማንም ግድ የለኝም ፣ ለእኔ ችግር ማን ደረሰ ? አትበል። ችግር አልቆ አይቆምም፤ ክፉዎችም ክፋትን በቃኝ አይሉም። በሩቅ ያየሃቸው ክፉዎች ወደ አንተም ይመጣሉ። አንድ ውሻ አንድ ነገር አይቶ ሲጮህ ያላዩት መቶ ውሾች እርሱን ሰምተው ይጮኻሉ ። የሌላው ኀዘን እንዲያሳዝንህ ፣ የሌላው ጩኸት እንዲሰማህ ይሁን። ከውሻ እንኳ አትነሥ ።
ይህን ያደረገው እገሌ ሳይሆን አይቀርም አትበል። ባላየኸው ነገር በንጹሕ ሰው ላይ ዕዳ አታሸክም። እንኳን ግምትህ ዓይንህም ይሳሳታል። ሰውን ያለ ኃጢአቱ እንኳን በአፍህ በልብህም አትኰንነው። የበደል አውራው ንጹሕ ላይ መፍረድ ነው። በርኩሱም እንዳትፈርድ ገደብ ተጥሎብሃል። ደግሞም ግምትህና ፍርድህ ሐሰተኛ ሆኖ ስታገኘው በራስህ ታፍራለህ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም