የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተቆራረሰ ልብ

ያላቸው በሌላቸው ጨከኑ፣ አግኝተው ካልሰጡ ከቶ መቼ ሊሰጡ ነው ? ደግሞም የማይሰጥ  ድሀ ማነው ? ለድሀ ጥሩ ቃል መናገር እርሱም ምጽዋት ነው። የአፍ ጮማ መቁረጥ በድU  መሳለቅ፣ በእግዚአብሔር ማፌዝ ነው ። የማይቀበል ሁሉ ያለው ባለጠጋ ማነው? ገንዘብ ሰጥቶ ከድሀ  ደስታ ይቀበላል። ድሀ ማለት ምንም የማይሰጥ ማለት አይደለም፤ ባለጠጋ ማለትም ምንም የማይቀበል ማለት አይደለም። ለመስጠት ሀብተ ሥጋ ፣ ሀብተ ነፍስ ያስፈልጋል። ለመስጠት በሕይወት መኖር ያስፈልጋል። የማይሰጡ እጆች ዛሬ በሰይጣን ተገንዘዋል፡ ነገ በፈትል ይገነዛሉ። መስጠትም ዕድል ነው። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የበለጠ ደስተኛ ነው። ወገን የጨከነባቸው ልባቸው ይቆራረሳል። በበረሃ በውኃ ጥማት እንደ ተሰነጣጠቀ መሬት ይሆናሉ። ያዘኑብን ደስታችንን ይዘውብናል። የእኛን ስንሰጣቸው የእነርሱን ሊሰጡን ተዘጋጅተው የሚጠብቁን አሉ።

እኔ ነኝ ማለት የማይችሉ፣ ራሳቸው ፍሬኑ  እንደ ተበጠሰ መኪና አልቆም ያላቸው፣ ጽድቅን እያዩ ኃጢአትን የሚግጡ፣ ሁልጊዜ እየማሉና ራሳቸውን እየገዘቱ በቆሻሻው ስፍራ የሚገኙ ልባቸው የተቆራረሰ ነው። ራስን ማጣት፣ የሚፈልጉትን አለማወቅ፣ በመንፈሳዊ ድንዛዜ መኖር፣ በእግዚአብሔር ቤት ሆኖ ከእግዚአብሔር መለየት፤ በፍቅር ቤት በቂም ፣ በጸሎት ቤት በትዝብት መኖር ያደከመው ልቦቹ የተቆራረሱ ናቸው ።

ሳይናገር ብልሃት የሚፈልግ ሞኝ፣ የልቤን ለምን አላወቁልኝም? ብሎ የሚጣላ ምስኪን ልቦቹ የተቆራረሱ ናቸው ። በግብጽና በከነዓን መካከል የሚኖር የሕይወት ጥጋብ፣ የነፍስ እርካታ የለውም። መርዛማ አሳቦች ይበክሉታል። ማኩረፍ ዘመዱ፣ ዝምታ አገሩ ይሆናል። ሰዎች አስረድተናቸውም ከተረዱን ዕድለኛ ነን። ሰው የሰውን ችግር ለመረዳት ራስ ወዳድነቱ መሰናክል ይሆንበታል። የሚጮኸው ከራሱ አንጻር ነው ። ከተማ ቢፈርስ ግድ የለውም፣ አጥሩ ሲነካ ግን ያመዋል። ሚሊዮን ሲረግፍ ሰምቶ እንዳልሰማ ያልፋል፣ ልጁ ሲያተኩሰው ግን ሆድ ይብሰዋል። መናገር የማይችሉ፣ በውስጣቸው በማጉረምረም የሚሰቃዩ ልባቸው የተቆራረሰ  ነው።

ፍቅርን ሰጥተው ጥላቻን ያተረፉ የመሰላቸው፣ ልቤን ሰጥቼ ቀልባቸውን እንኳ አልሰጡኝም ብለው የሚያስቡ የተቆራረሰ ልብ ይዘዋል። ይህ ስንጥቅጥቅ የመንፈስ ቅዱስ ዘይት ካልሆነ ምንም ሊያረጥበው አይችልም። የተቆራረሱ ልቦች ሰባራ አንገት፣ ስንኩል ጉልበት ይፈጥራሉ።

ጥላቻ ሰባኪ አላት፣ ጥላቻ ሠራዊት አላት፣ ጥላቻ  ደቀ መዝሙር አላት። በጥላቻ የተወጉ  ሰዎች የማይጣሉት ሰው የለም። የበደላቸውንና ያልበደላቸውን መለየት አይችሉም። እንዴት የቆመ ሰው ከሞተ ሰው ጋር ይጣላል? በጥላቻ የተመረዙ የጅምላ ፍረጃ፣ የጅምላ ፍጅት ያውጃሉ። ሰዎች ስለ ተመረዘው ቃላቸው፣ ስለሚገድል ፍላፃቸው ይጠሏቸዋል። በውስጣቸው የሚያሳልፉትን ስቃይ ግን ማንም አይረዳላቸውም። ካልታመመ የሚያሳምም፣ ባልታወከ የሚያውክ ማንም የለም።  ለሰው ሁሉ ቅን አመለካከት የሌላቸው የተቆራረሱ ልቦችን ይዘዋል።  የተቆረሰ ልብ ለሌላው የሚያዝን ነውና ያረካል፣ የተቆራረሰ ልብ ግን በጥማት ምድረ በዳ የሚያልፍ ነው።

የተቆራረሱ ልቦች በራስ ሥራ ከማፈር የተነሣ ፣ ራስን ይቅር ካለማለት ይከሰታሉ። የተቆራረሰ ልብ ከሰዎች ብዙ ጠብቆ ጥቂት ባለመቀበል ይከሰታል። የጀመርኩት ሁሉ አይሳካም ፣ የተሳካው ዕድሜ የለውም ብሎ የሚያስብ ሰው የተቆራረሰ ልብ ይይዘዋል። ያን ጊዜ በደመና ውኃ ይጠማዋል። ሆዱን ባሕር ባሕር ይለዋል ። ሆደ ባሻነት ያስለቅሰዋል። የቆሙትን ትቶ የሞቱትን እያስታወሰ  ያዝናል። የተቆራረሰ ልብ መኖሪያውን ከመቃብር ሥፍራ ያደርጋል። የእኔ ነገር የሚል ልቅሶ ያስጀምራል። ሰውም እግዚአብሔርም ትተውኛል የሚል ሹክሹክታ ያመጣል።

የተቆራረሰ ልብ የሚድነው በንስሐ ፣ በእምነት ፣ መለኮትን ብቻ ተስፋ በማድረግ ነው ። አዎ ነገሥታት የመኖሪያ ፈቃድ ይስጡ ይሆናል ፣ የመኖር ፈቃድ የሚሰጥ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው። አንተ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር እኖራለሁ በል!

“መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤” ዘዳ. 33፥27

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ