የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዚአብሔር መልካም ነው

“እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል ::” (ናሆ  ፩ ፥ ፯)

ያለው ማማሩ ፣ … እያሉ እንደ ዋዛ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ያለው ሰው ሁሉም ነገሩ ያምራል። ሰውዬው ባለ ጠጋ ነው ፣ ቆንጆ ሴት ያዘ ። አንድ ቀንም “ቆንጆ ነኝ ወይ እቱ?” ብሎ ቢጠይቃት “ጌታዬ የባለጠጋ አስቀያሚ የለውም” አለችው ይባላል። ባለጠጋ በመንገድ ቢወድቅ የሚደግፈው ብዙ ነው ፣ ንግግሩ ቢሰበር የሚጠግንለት፣ እንዲህ ያሉት እንዲህ ለማለት ፈልገው ነው በማለት የቃል ወጌሻዎች ይሰለፉለታል። አንድ ምስኪን ሰባኪ የቃል ስህተት ሲያሰማ ሁሉም ተሳስተሃል ፣ ውጉዝ ነህ ሊለው ይጣደፋል። ተራራ የሚያህል ስህተት የሚናገሩ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎች ብቅ ሲሉ ቃላቸውን የሚጠግን ወጌሻ ቊጥር የለውም። ለማለት የፈለጉት እንዲህ ነው፣ ከዐውዱ ተገንጥሎ ታይቶባቸዋል በማለት በከንቱ እሪ ይሉላቸዋል። እርሳቸው መልስ ስጡልኝ አላሉም። ላለው ቅንጭብ ያረግዳል ይባላል። እንኳን ሰዉ ቀጤማውም ልጎዝጎዝልህ ይለዋል።  ደሀው ግን በመንገድ ሲወድቅ በሞትኩት ከሚለው ምነው ሞቶ ባረፈው የሚለው ብዙ ነው። በቃሉ ሲሰበርም አፍ አፉን የሚለው ምነው ዝም ብትል ብሎ የሚመክረው ሁሉም ነው።

ክፉ ቀን አይምጣ ወዳጅ እንዳላጣ ይባላል። ክፉ ቀኖች ነፋስ ገለባን እንደሚበትን ወዳጆችን ይበትናሉ ። ደጉ ሰው ክፉ ይሆንብናል። መንገድ ሲያገኘን ተወርውሮ የሚያቅፈን መንገድ አሳብሮ ይሸሸናል። የተከፈቱ በሮች ዝግ ይሆኑብናል። ለልመናና ለእርዳታ የመጣን መስሏቸው ሰዎች ይሰለቹናል። እኔም ችግር አለብኝ ምን ላድርግህ በማለት በልቡ የሚያማን ይኖራል። በመከራ ቀን መልካም ሰው ማግኘት ውድ ነው።

ጴጥሮስ በሰላም ቀን ተገኘ ፣ በክፉ ቀን ከዳ። የቀሬናው ስምዖን ግን በግብዣው አልነበረም፣ በመከራ ቀን ግን መስቀል አጋዥ ሆነ ። በመከራ ቀን እግዚአብሔር ሰው ይሰጣል። ለቀኑ በልኩ የተሰፉ ሰዎችን ያመጣል። በመከራ ቀን የሚገኙ ሰዎች ጠባይ የመጀመሪያው በመከራ ማለፋቸው ነው። የሌሎችን መከራ ሲያዩና ሲሰሙ ያለፉበትን የጭንቅ ጊዜ ያስታወሳሉ። መከራን ከመከረኛ ጋር ማውራት ጥሩ ነው ይባላል። እነዚህ ሰዎች ካነበቡት ብቻ ሳይሆን ከኖሩትም ይመክራሉ። አብሮነታቸው ፣ አይዞህ ባይነታቸው ልብን ይደግፋል። በመከራ ቀን የሚገኙ ጨዋ አስተዳደግ ያላቸው፣ የታረሙ  ሰዎች ናቸው ።  በመልካም ቀን ሁሉ ይገኛል፣  በክፉ ቀን አለሁ የሚሉ ሰዎች ክርስቶስን በምድር ላይ የሚያሳዩን ናቸው።

መከረኞች በመከራቸው ቀን መልካሞችን አያገኙም። የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ የሚፈርድባቸው ፣ በቁስል ላይ ጥዝጣዜ የሚያወርድባቸው ክፉ ሰው ይገጥማቸዋል። እግዚአብሔር ግን በመከራ ቀን መልካም ነው። ብቻችንን አይተወንም፣ እሰይ ተቀጡ አይለንም። በብሉይም በሐዲስም ያለው አገልግሎት ተመሳሳይነት አለው። ከመከራ በፊት የማስጠንቀቅ፣ መከራ ሲመጣ የማጽናናት ፣ ከመከራ በኋላ የማበረታታት አገልግሎት ይደረጋል:: እግዚአብሔር በመከራ ዘመን አጽናኝ አገልጋዮችን ይልክልናል። እነ ኤርምያስ፣ እነ ሕዝቅኤል ፣ እነ ዳንኤል የማጽናናት አገልግሎት ሲያከናውኑ ነበር። እግዚአብሔር ያጽናናል፣ የኀዘን ማቅን እየቀደደ የደስታ መጎናጸፊያን ይደርባል።

“እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤” እግዚአብሔር ይህን ቃል የተናገረው በነቢዩ በናሆም በኩል ነው። ናሆም ማለት የስሙ ትርጓሜ መጽናናት ማለት ነው። ይህ መልእክት የተላለፈው ከእስራኤል ውጭ ላሉት ለነነዌ ሕዝቦች ነው ። በዮናስ አገልግሎት ንስሐ የገባችው ነነዌ መልሳ በኃጢአት ጭቃ ላይ እየተንከባለለች ነበር። በዚህ ጊዜ ዳግመኛ ነቢዩ ናሆም ተላከ። የሚመጣውን ፍርድ  አመለከተ ። አሁንም በፍርዱ ውስጥ ምሕረት አለውና  ወደ እርሱ ቢመጡ እንደሚቀበላቸው ተናገረ። ምክንያቱም እግዚአብሔር መልካም ነውና።

መልካም ማለት ሁልጊዜ በጎ የሚያስብ ፣ በሌለንበት እንኳ ስለ እኛ ጥሩ የሚናገር፣ ብንራቆት የሚሸፍነን ፣ ብንወድቅ የሚያነሣን፣ የመጽናናት ቃል ለእኛ ያለው፣ በክፉ ቀን የማይከፋብን፣ በትላንቱ የማይለካን፣ ተስፋ የሚሰጠን፣ ዝቅ ብሎ ከውድቀት የሚያነሣን ፣  እጆቹን ለምሕረት የዘረጋልን፣ ቆርሶ የሚያጎርሰን፣ ቀዶ የሚያለብሰን ነው ። የሰው መለኪያው ክፉ  ቀን ነው ። እግዚአብሔር በክፉ ቀን የሚገኝ አምላክ ነው። መልካምነቱን ጊዜ አያሸንፈውም። መልካምነቱም የባሕርይ ገንዘቡ ነው። ከመፍረድ ማዳን የሚወድ ነው። አይታዘበንም፣ ተስፋ ያደርገናል። በእኛም ደስ ይለዋል ።

መከራ አሳዳጅ ነው። በመከራ ውስጥ ያለ ሰው ሰማይና ምድር አልደብቅህ የሚሉት ተንከራታች ነው ። ተናግሮ አይረካም፣ ሄዶ አያርፍም። መፍትሔ አለ በተባለ ስፍራ ፊት ለፊት ቆሞ ወረፋ የሚጠብቅ ነው። ሌሊት እንቅልፍ፣ ቀን ዕረፍት የለውም። ሕሊና ይከሰዋል፣ ወዳጅ ይፈርድበታል። ያጽናናቸው ሰዎች ያቆስሉታል። እግዚአብሔር ግን በመከራ ቀን መሸሸጊያ ነው ። ይደብቃል፣ ይሰውራል፣ ገዳዩን ያሳልፋል። እስራኤልን በቤት ሸሽጎ ቀሳፊውን መልአክ አሳለፈላቸው። የእግዚአብሔር ምሽግነት አይደፈርም። አምባው አይፈርስም። መሸሸጊያ ዋሻ፣ ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ፣ መማጸኛ ከተማ ፣ ከሞት ማምለጫ እግዚአብሔር ነው። ይህን መጽናናት የላከው ለነነዌ ሰዎች ነው። ለሁሉ ቃል ያለው አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን !

“የሚታመኑትንም ያውቃል” ይላል። በመከራ ቀን ብዙ ሙከራዎች አሉ። የምናውቃቸው ሰዎች፣ ስልክ ቁጥሮች፣ ባለ ሥልጣናት … ይሞከራሉ። አንዳቸውም አለሁ አይሉም። ያላስቀደምነው እግዚአብሔር ግን ቀድሞ ይደርስልናል። በመከራ ዘመን በእግዚአብሔር መታመን ይገባል። ተራራውን ሳይሆን በተራራው ራስ ላይ የነገሠውን አምላክ ማሰብ ልብን ያበረታል። እግዚአብሔር እነማን እንደሚታመኑት የሚፈትነው በመከራ ቀን ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ብፈተንም አምላኬ ድል ይሰጠኛል። ወደ እርሱ ባለቅስ መልስ ይሆነኛል፡ በሱባዔ ባስሰው ይገኝልኛል፣ ብጠራው አቤት ይለኛል ብለው የሚታመኑበትን ያውቃል።

መከራ ዝቅ ሊያደርጋችሁ ፣ ወዳጅ ሊያሳጣችሁ ቆርጦ ቢነሣ እግዚአብሔር መልካም ነው። በጥይት እሩምታ፣ በገዳይ ማሳደድ ውስጥ ክፍት የነበረው የወዳጅ በር ቢዘጋባችሁ እግዚአብሔር መሸሸጊያ ነው። በእርሱ ለሚታመኑት ዕውቅናና ድል ይሰጣል። እንደ ነነዌ የወደቃችሁ ብትሆኑ እግዚአብሔር ለእናንተ ቃል አለውና በርቱ ! ቀኑ ጎርፍ ቢሆንባችሁ ከብርሃን ፈጥኖ ሊያድናችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው። የተመሰቃቀለ የመሰላችሁን ነገር ባለሙያው ጌታ ያስተካክለዋል። እሾሁን ነቅሎ ዕረፍት ይሰጣችኋል።

ምስጋና ለአንድ አምላክ ለእግዚአብሔር ይሁን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ