የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰው አሳብ

“በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።”  (ምሳሌ  ፲፱ : ፳፩)

አንዳንድ ጊዜ ልባችን የሚፈነዳ እስኪመስለን በአሳብ እንወጠራለን ፣ ሌላ ጊዜ ቀልባችን እንዳይከዳን እንሰጋለን። ጭልጥ ብለን በአሳብ እንጠፋለን፣ አለህ አለሽ ሲሉን ምንተ ህፍረታችንን አለሁ እንላለን። ከሰዎች ጋር እያወራን ካለንበት ጊዜ የሌለንበት ጊዜ ይበዛል፤ በአካል ተቀምጠን በአሳብ እንጠፋለን ። የሚገርመው  ነገር ያንን ሁሉ መንገድ የነዳነው፣ ያንን ሁሉ ዜብራ የተሻገርነው በፍጹም ከአእምሮአችን ውጭ ሆነን ነው። ስንተኛ የሚጠብቀን ጌታ ስንጓዝም ይጠብቀን ነበር።

ግን ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምንድነው? ሕይወትን እኛ እንደ ጀመርናት በራሳችን አቅም የምንለካት ለምንድነው? የእኛ ከመጠን በላይ መንቃት አጠገባችን ያሉት እንዲተኙ ፣ አሳብ የለሽ ሆነው እንዲኖሩ ምክንያት አልሆነም ወይ? ሁሉንም ነገር ማስተካከል እችላለሁ ብለን እንዴት አሰብን? ሁሉንም ሩጫ ያሳካ፣ በሁሉ ሙሉ የሆነ ሰው እናውቃለን ወይ? ቤተሰቦቻችንስ የራሳቸውን ሸክም መሸከም የለባቸውም ወይ? ታናሽ ሆነን እንደ ታላቅ እናስባለን። ወላጆች ልጅ ሲሆኑብን ወላጅ ካልሆንኩ እንላለን። ደግሞስ እግዚአብሔር ሁሉን እያየው ከሆነ ፍትሕ ጠፋ ብለን መጨነቃችን ምን ይጠቅማል? ለቀኑ ብልሃት እንዳለው ረስተን ፣ ሲያመጣው ከመቻያው ጋር መሆኑን  ዘንግተን መዋተታችን ለምን አይበቃም? ችግርን መቀነስ እንጂ ማጥፋት እንደማንችል ለምን ረሳን? የድርሻችንን መወጣት እንጂ መረበሽ ጥቅም እንደሌለው ዛሬም አላመንም። የሆኑ ነገሮችን እንዳልሆኑ መመኘት ምን ይፈይዳል? የአቅማችንን ከጣርን ፈንታው የጌታ መሆኑን ለምን አንቀበልም?

በልባችን ብዙ አሳብ አለ። አንዱን ጨረስኩት ስንል ሌላው ይተካል። ችግር ካለቀማ ምድር ገነት ሆኗል ማለት ነው። የሚጠሉን ሰዎች ይረብሹናል። ከሚሸነግሉን ሰዎች የተሻሉ መሆናቸውን ገና አላወቅንም። ምቀኞች ባይኖሩ ጠንቃቃ አንሆንም ነበር። ጠላቶችን መውደድ ያለብን ዕድሜአችን እንዲረዝም ስለሚያደርጉት ነው። ምንም በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ያሉት ዝማሬ ላይ ሳይሆን መጠጥ ላይ ነው።  ሰው ችግር ከሌለበት ችግር ይፈጥራል።

ምኞታችን እጅግ ብዙ ነው። ዓለም ለእነ እገሌ ብታልፍም እኛ ጋ ላታልፋ የመጣች ይመስለናል። አንድን ነገር እስክንጨብጠው ያለን ጥረት ብዙ ነው። ከጨበጥነው በኋላ ትርጉም እናጣለን። ሁሉም ነገራችን የችኩላ ነው፣ ለማግባትም ለመፍታትም ፈጣን ነን። በአንድ ጊዜ ሁለት ትምህርት፣ ሁለት ሥራ ፣ ሁለት ሃይማኖት ማራመድ እንፈልጋለን። ሁሉም ነገር ሰልችቶን ደግሞ አስቀምጠነው እንሄዳለን። ዕቅድ በዕቅድ እንሆናለን። ከማማከር በራስ መወሰንን እንደ ጀግንነት እንቆጥረዋለን። እንደሚኖር ብንሠራም እንደሚሞት መዘጋጀት አለብን። የሞቱትን ስናስብ ከሞታቸው ዕቅዳቸው ያስለቅሳል።

አዎ እኛ እውነትም ውሸትም ነን። እውነቱ  አለሁ እያልን ነው፣ ውሸቱ ደግሞ ላንኖር እንችላለን። ለቀጠሮ የማንበቃ፣ እገሌ ይሞታል ብለን እያስታመምን እኛ ልንቀድም የምንችል ፣ እርግጠኛ ባልሆነ ሕይወት ውስጥ ያለን ነን። እርግጡ እግዚአብሔርና የዘላለም ሕይወት ብቻ ነው፡፡ “እርሱ እኮ ልጅ ነው” ስለሚሉን ልጅ አይደለንም። ልጅ አይሞትም ያለው ማን ነው? የማንንም ውድቀት መመኘት አያስፈልገንም ፣ ማንንም ለመበቀል መኖር አያሻንም። ለዕለት የሚበቃ ካለን ማመስገን አለብን። ስለ ታመምን አንሞትም ፤ ጤነኛ ስለሆንን ምንም አይነካንም ማለት አይደለም። ሕፃን ልጅ ወላጆቹ ወደሚያውቁት መንገድ ስለሚጓዝ አይሰጋም። ላመሉ የት ነው? ብሎ ይጠይቃል  ፣ ቢነግሩትም አይገባውም ፤ በወላጆቹ እውቀት ያርፋል። እኛም እንደ አማኙ ሕፃን አንተ ታውቃለህ ብለን ማረፍ አለብን።

አታስቡ አልተባልንም ፣ አትጨነቁ ተብለናል። ኩንታል አሳባችን በሙሉ ግን አይፈጸምም። በአሳባችን ላይ እርሱ ሲያስብበት ብቻ ይሆናል። ትራፊኩ እጁን ወደ ላይ አንሥቶ ቁሙ ሲል መኪናውም ሾፌሩም ይቆማሉ ። የእግዚአብሔር ሥልጣንም የሰዎችን አሳብ፣ ሥልጣንና ኃይል ያስቆማል። ለምንድነው ያስቆምከኝ ብለን ትራፊኩን አንጠይቅም። ለእኛ ደኅንነት ያስቆመንን አምላክ ለምን ? አንለውም። ብቻ ብዙ ብናስብም የሚጸናው ምክረ ሥላሴ ነው!

አምላኬ ሆይ፣
አንተ ያልከው ይሁን። ዛሬ እንኳ ሁሉን ላንተ ልተውልህ! ሁሉን መተው ቢያቅተኝ ነገን እንኳ ላንተ ልተውልህ። ረጅም አስቤ ባጭር የምቀር ነኝ። ልቤ ከፍ ከፍ ያለበትን አሳብ ወዲያው ወርዶ አገኘዋለሁ። ማን ያድነዋል? ሲሉኝ ባንተ ድኜአለሁ፣ እውቀትህ አሳልፎኝ በእውቀቴ እደገፋለሁ። የእኔም የሰዎችም አሳብ  ወጥመድ ነው ። ያንተ አሳብ ግን መንገድ ነው። አዎ አንተ ያልከው ይሁን። ሁሉን ላንተ መተውን፣ በእምነት ማደርን አለማምደኝ። ማጉረምረምን፣ ተስፋ ቢስነትን አሸንፍልኝ። ንቀትን እንድታገሥ እርዳኝ። ቢልልኝ እዚህ እደርስ ነበር ማለትን ከእኔ አርቅ። ያልከው ይሁን ። በሰጠኸኝ ነገር አስደስተኝ ።  አሜን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ