ወዳጄ ሆይ በኅሊና ስለሚመላለሱ ፈተናዎች የጻፍህልኝ ጦማር ደርሶኛል። ሕሊና የጠላት ትልቁ ዒላማ ነው። በሕሊና ውስጥ አሳብ፣ እውቀት ፣ ምኞት፣ ትግል፣ ጦርነት አለ። በሕሊና ውስጥ አሳብ ይፀነሳል ። አሳቡ ከራስህ ተፈጥሮ ፣ ካየኸውና ከሰማኸው ነገር ይመጣል። አንድን የእውቀት ቃል ሰምተህ ረስተኸዋል። አሳብ ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ይጠቀመዋል። የምትሰማውና የምታየው በሕሊና ባንክ ወይም ጎተራ አሊያም በውስጠኛው ጓዳ ይቀመጣል። አንድ ቀንም የበጎና የክፋት መነሻ ይሆናል። የሚሰማና የሚታይ ነገር ወደ ውስጥ ገብቶ የሰውን ማዕከል ይቆጣጠራል። ይልቁንም ዘመናዊው ዓለም ውበትን መሣሪያ በማድረግ የሚጠቀማቸው ማስታወቂያዎች ባትፈልግም እንድትሸምት ያደርጉሃል። ሰው ዓይንና ጆሮው ከተያዘ ሌላው ቀላል ነው። ሰይጣን የሰውን ዓይን በፊልሞች፣ የሰውን ጆሮ በዜና ይዞታል። ያየኸው ክፉ ነገር ፣ ሰይጣናዊ ፈተና የሚያመጣ ከሆነ ደግመህ አትየው። ክፉ ነገርንም አትስማ። የሰውን ችግር መስማትና ማወያየት መልካም ነው። የሰውን ግፍና ተንኮል መስማት ግን ውስጣዊ ዝለት ያመጣል። ደግሞም ክፉ ነገርን እንድትለምደውና እንደ ቀላል እንድታየው ያደርግሃል። ስለ አንዳንድ ኃጢአት በማውገዝ ስም ደጋግሞ መናገር የሰይጣን ስልት ነው። ሰይጣን ጆሮን ማስለመድ ዋነኛ የውጊያ እቅዱ ነው።
ይህ ሁሉ የዓለም ሕዝብ ፣ ይህ ሁሉ እንስሳ የፅንስ ውጤት ነው ። አሳብ ጽንስ ነው። አካል እየነሣ፣ እየገዘፈ ይመጣል። የሰይጣን ትልቁ የውጊያ ሜዳ አሳብ ነው። ሰይጣን በሕሊና ላይ የስድብ ቃላትን እያወጣ እንድትሳቀቅ ያደርግሃል። ይህ ስድብ በእግዚአብሔርና በቅዱሳን ላይ ሊሆን ይችላል። አንተም ካንተ የሆነ መስሎህ ቀን ሰላም፣ ሌሊት እንቅልፍ ታጣለህ። የምታስበውን አንድ ቀን ብናገረውስ ብለህ ትጨነቃለህ። ከእግዚአብሔር ጋር የተለያየህ መስሎ እንዲሰማህ፣ ስርየት የሌለው ኃጢአት ውስጥ ገባሁ እንድትል ያደርግሃል። በዚህ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ትርቃለህ፣ አገልግሎት ታቆማለህ፤ ከቅዱሳን ኅብረት ተለይተህ ብቻህን ስትሮጥ ያን ጊዜ በቀስቱ መትቶ ፣ በጦሩ ወግቶ ይገድልሃል።
በሕሊና ላይ የሚነሣው የስድብ ፈተና በመንፈሳዊ ሕይወት ባደጉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው። የአራተኛ ክፍል ፈተናና የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና አንድ አይደለም ። ፈተናው ሕይወታቸውን ከክርስቶስ፣ አገልግሎታቸውን ከመንፈስ ቅዱስ ለመለየት የሚመጣ ነው። ይህ ፈተና ደረጃው ከፍ ያለ ሲሆን ካለፉት በኋላ ትልቅ ጸጋ ይመጣል። በዚህ ፈተና ውስጥ በመላው ዓለም ፣ በመላው ዘመን የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች አልፈዋል ።
ሰይጣን ይህን ፈተና የሚያመጣው ሥጋና ነፍስን ፍጹም ለማጥፋት ነው። የፈተናው ተጽእኖ ተፈታኙ ራሱን እንዲጠላና እንዲፀየፍ የሚያደርግ ነው ። አምላኩን ያጣ ስለሚመስለው በሰማይና በምድር ስደተኛነት ይሰማዋል። እንዴት በክርስቲያኖች መሐል እገኛለሁ ብሎ ይፈራል። ከአገልግሎትም ለመራቅ ይወስናል። በቀንና በሌሊት ሙግት ውስጥ ይገባል።
ሕሊና ጎዳና ነው። በጎዳና ላይ ብዙ መኪና ያልፋል፣ ይመለሳል። ምን ዓይነት መንገደኛ እንደሚያልፍ ማወቅ አይቻልም። መንገድ ዳር ያለ ነዋሪ ሁሉንም ግቡ አይልም። በሕሊና አደባባይም ብዙ አሳቦች ያልፋሉ። ከባለቤቱ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አሳቦችም ይስተናገዳሉ። እኔ እንዴት ይህን አስባለሁ? እስኪሉ ድረስ ርኵስ አሳቦች ይመጣሉ። አንዳንዴ በሰዎች ፈርደን እንደሆነ ያ የፈረድነው ነገር በአሳብ መልክ መምጣት ይጀምራል። በሕሊና ላይ ስለሚመጣው የጽርፈት ወይም የስድብ አሳብ ሁለት ነገሮችን ማወቅና ማድረግ አለብን።
የመጀመሪያው ያ አሳብ የእኛ አይደለም፣ በጤነኛ አእምሮአችን የማናስበው ከሆነ ያ አሳብ የኛ አይደለም። በምናከብረው አምላክና በምንወዳቸው ቅዱሳን ላይ እንዲህ ያለ አሳብ ልናስብ በፍጹም አንችልም። የእኛ አሳብ ካልሆነ የማን ሊሆን ይችላል?
ሁለተኛው የስድብ አሳብ ከሰይጣን በቀጥታ የመጣ፣ በሕሊናችን ላይ እየተረጨ ያለ ጨረር ነው። ከራስ ጋር በመታገል አናርቀውም። አንተ ሰይጣን አሳብህን አንስተውም ብለን መገሠጽ ይገባናል።
የኢዮብ ሚስት እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ብላው ነበር። ( ኢዮ. 2፥ 9) ይህች ሴት እግዚአብሔርን ቢሰድብ እንደሚሞት እየተናገረች ነው፤ ደግሞም የሚሞት ከሆነ ከፊት ለፊት የሚያገኘውን እግዚአብሔር ለምን ይሳደባል? ሞት እየመጣ ከሆነ ከሞት በኋላ ከሚያገኙት አምላክ ጋር መስማማት ይገባል። የኢዮብ ሚስት በውጭ ሆና ተናገረች። የኢዮብ ሚስት በውስጥ ሆና ስትናገር እግዚአብሔርን ስደብ የሚል አሳብ ይመጣል።
እግዚአብሔር እኛን ፣ ፈተናችንን ፣ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ያውቀዋል። አእምሮው የታወከ እንኳ ወላጁን ሲስድብ ወላጅ ሸፍኖ ያስታምመዋል። እግዚአብሔር ከፈቃዳችን ውጭ በሆነ የሕሊና ትግል የስድብ አሳብ ውስጥ ስናልፍ ይራራልናል እንጂ አይፈርድብንም። በዚህ ፈተና ውስጥ ስናልፍ ንስሐ መግባት መጸጸት ሳይሆን መገሠጽ ይገባናል። የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳኛችን ነው። ዛሬ በዚህ ስለጠንኩ በሚለው ዘመን የድምፅ መረጃ ተቀባይነት እያጣ ነው። በሰውየው ድምፅ ሰውየው ያላለው ነገር ይተላለፋል። የሕሊና ውጊያም በእኛ ድምፅ እንዳልን አድርጎ ጠላት እኛን የሚከስበት ስልቱ ነው። አንዳንድ ፈተና በጸሎት ብቻ ሳይሆን በመንቃት ድል ይነሣል ሌባን በመንቃት እናባርረዋለን። ሲብስ ደግሞ እንተናነቀዋለን።
“በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤”1ኛ ጴጥሮስ 5፥8
ጌታ ሆይ ንጹሕ ልቡና ፍጠርልን ! በሕሊናችን ላይ የበላይ አድርገን!
ወዳጄ ሆይ ለጻፍህልኝ ጥያቄ እንደ እውቀቴ ደካማነት መልሱን ሰጠሁህ። ከእኔ የተሻሉ አዋቂዎችን ብትጠይቅ በብዙ ይመልሱልሃል። መልሱ እውነት ቢሆንም ዝርዝሩ አንሶብህ ከሆነ ደካማነቴን እይበት ። እንዳቅሜና እንዳቅምህ መጠን ጽፌአለሁ ። በረከተ ሥላሴ ካንተ ጋር ይሁን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም.