ግራ መጋባት ፣ ወዴት ነው የምሄደው ? ብሎ መንገድ ላይ መቆም ፣ የትላንቱ ትዝታ ከአእምሮ ሙልጭ ብሎ ሲወጣ ፣ የነገው ተስፋ አልታይ ሲል መፍትሔው ምን ይሆን ? አሁንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ነኝ ብለን ለራሳችን መናገር እንችላለን ። ምሥጢራትንም እየፈጸምን እንደሆነ ይታወቃል ። መላ ዘመናችንን ለአገልግሎት ሰጥተናል ። ታዲያ ይህ ጥቁር ቀን እንዴት ሊመጣ ቻለ ? እያባበሉን ልቅሶ ፣ አይዞአችሁ እየተባልን መንቀጥቀጥ እንዴት መጣ ? አዎ እነዚያ ዘመናት እግዚአብሔር እኛን ያሞላቀቀበት ፣ አፈር አይንካችሁ ብሎ የተሸከመበት ፣ ማንም አይናገራችሁ ብሎ አንደበት የሆነበት ፣ በክፉ ካየን ጋር የተጋጠመበት የምቾት ዘመናት ናቸው ። ሁልጊዜ እንዳማሩ መኖር ፣ እንዳማሩ መሞት ላይኖር ይችላል ፣ መታዘል ቢመችም በእግር መሮጥ ይበልጣል ፣ ማሙሽ መባል ቢያስደስትም አንቱ መባል ይልቃል ። የመረጥነውን ሳይሆን የተመረጠልንን ልንጋፈጥ እንችላለን ። ታዲያ ልብ ድው ድው ሲል ፣ አምባውን ለቆ ልውጣ እያለ ሲታገል ፣ ቃላት በፍርሃት ሲቆራረጡ ፣ በብርዱ ውኃ ሲጠማን አንድ ቃል ይሰማል ። “ልባችሁ አይታወክ ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ ።” ቅዱሳን ሐዋርያት የገጠማቸው ይህ ዓይነት ስሜት ነው ። እውነትን ሳይሆን ግምትን አመኑ ። በማመን ሳይሆን በማየት ለመኖር አቀዱ ። ሰው ሊለየኝ ነው ብለን ስናስብ እንኳ ያለውን ፍርሃት መግለጽ አይቻልም ። እግዚአብሔር ሊለየኝ ነው የሚል ክፉ ዜና በጣም አስጨናቂ ነው ። ብዙዎች ከእግዚአብሔር እጅ ሊጣሉ ትንሽ እንደ ቀራቸው አድርገው ያስባሉ ፣ ይናገራሉ ። ግን ማንን እንደ ጣለ ይጥላቸዋል ? እነ እገሌን ጣለ ተብሎስ በታሪክ ተነግሮ ያውቃል ወይ ?
ይህ ዓለም የመቆያ እንጂ የመኖሪያ አይደለም ። ይህ ዓለም የመኖሪያ ቢሆን ኖሮ ከባድ ነበር ። ፍሥሐውም ጭንቁም ገደብ አለው ። በሐሰተኛው ዓለም እውነተኛውን ቤት ማግኘት አይቻልም ። ቤታችን በሰማይ ነው ። በእውነት ከሠራነው ሕንፃ የምንቀበርበትን መሬት ብዙ ዘመን እንኖርበታለን ። በሠራነው ሕንፃ የምንኖረው ሰባ ሰማንያ ዓመት ነው ። በመሬት ውስጥ ግን እስከ ምጽአት እንኖራለን ። አፈር ሁሉንም እኩል ያደርገዋል ። ሁሉም ወደ ዘመዱ ይሄዳል ። ሥጋም ወደ አፈር ፣ ነፍስም ወደ እግዚአብሔር ። በዚህ ዓለም ባለ ቤቶች ፣ በሰማይ ቤት አልባዎች ይሆናሉ ። በዚህ ዓለም ቤት አልባዎች በሰማይ ባለ እልፍኝ ባለ አዳራሽ ይሆናሉ ። ለዚህም ነዌና አልዓዛር ምስክር ናቸው /ሉቃ. 16፡19-31/። ዛሬ በደጃፋቸው ላይ ለማኝ እንዳይቀመጥ ውኃ የሚረጩ ፣ አባራሪ የሚልኩ በሰማይ በተቃራኒው ያገኛሉ ። በምድር ድሀ የተባለ በሰማይ ድሀ ሆኖ አይቀጥልም ፣ የምድሩ ጄነራል በሰማይም ጄነራል ሆኖ የሚገባ አይደለም ። እንኳን የሥጋን ክብር ሥጋንም እንደ ልብስ አውልቀነው እንሄዳለን ። ዓለም ፈራሽ ነው ፣ ሰማይ ጽኑ ነው ። በሰማይ ቦታ እንደ ተዘጋጀልን ሲገባን ቦታ አጣሁ ፣ ስፍራ አላገኘሁም ፣ ሁሉ ገፋኝ ፣ የሚቀበለኝ አጣሁ የሚል ብሶታችን ይጽናናል ። ብቻ በምድር ጌታ ፣ በሰማይ ከርታታ ከመሆን ይጠብቀን !
ሳቁ ካረፈደ የማይውልበት ፣ ከዋለ የማያመሽበት ዓለም ላይ ነን ። እስከ ሰማይ የሚደርስ ቅምጥልነት ፣ ጨዋታ አምጡ ባይነት ሊኖር አይችልም ። እውነተኛው ቤታችን በሰማይ ነው ። ለእውነተኛው ቤታችን ማመንና መኖር አለብን ። ወደ ሰማዩ ቤት በድሆች ሆድ በኩል ቅርስ መላክ አለብን ። ወንጌል እንዲስፋፋ መስጠት ግዳጃችን ነው ። አወይ ታድሎ አለመታደል ሰጥቶን መስጠት አለመቻላችን ነው ። ገንዘብ ባይኖርህ ፣ ጊዜ መስጠት ትችላለህ ፣ ጊዜ ቢያጥርህ ሕይወትህን ለአምላክ መስጠት ትችላለህ ። የማይሰጥ ሰው የለም ። በምድር የሠራነው ጎጆ ሲያፈስ የሚኖር ነው ። አንዱን ስንደፍነው አሥር ቀዳዳ ይሸነቆራል ። ጉልላቱን ደመደምኩ ስንል መሠረቱ ይናጋል ። ዓለም ሁልጊዜ ጉድለት ነው ። ዓለም ፍለጋው የማያልቅ ፣ የማይገኝ ነው ። በሰማይ ግን መኖሪያው ተዘጋጅቷል ። ሀብታም ባል የሞተባት በአንድ ዓይንዋ ስታለቅስ በአንድ ዓይኗ ትስቃለች ይላሉ ። ይህ ዓለም ቢሞትብን በዚያኛው ዓለም እንስቃለን ። ደቀ መዛሙርቱ ግራ ተጋብተዋል ። ልባቸው በፍርሃት ይናወጣል ። የጌታን የሞቱን ዜና ሰሙ ። ሞቱን ሲሰሙ ትንሣኤውን ግን ከልብ አልሰሙም ። የይሁዳን በልቶ ካጅነት ሰሙ ። ይህም ከማን ጋር ነበርን እስኪሉ በጥርጣሬ አናወጣቸው ። ከበግ ጋር ተኩላ ተሰማርቶ ነበር ። ቀጥሎ ምን ይሆን ? በማለት ታወኩ ። ጌታ ግን ለሁከታቸው አልተዋቸውም ። ልባችሁ አይታወክ አላቸው ። አካላቸውና ገጽታቸው የሚታወክባቸው ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በውስጣቸው ምንም ስሜት የለም ። ከላያቸው ወይኔ ወይኔ እያሉ ያለቅሳሉ ፣ ልባቸው ግን አያዝንም ። ደቀ መዛሙርቱን የገጠማቸው ልባዊ መታወክ ነበር ። የልብ አምላክ ብቻ የሚያውቀውና የሚያረጋጋው ማዕበል መጣባቸው ።
እንዴት ይህ ቀን እንሻገረዋለን ? ማለፊያው በየት በኩል ነው ? ይህን ቀን አልፈን ማውራት እንችል ይሆን ? ብለው ጥያቄ አቀረቡ ። ጌታ መንገድ አላመለከታቸውም ፣ መላ በሉ አላላቸውም ፤ መንገዱ እኔ ነኝ አላቸው ። መንገዱ ከተገኘ መውጣት ይቻላል ። የብልሃት ያለ የሚል መንገዱን ሲያገኝ እፎይ ይላል ። የበረሃ አዙሪት የገጠመው ፣ የሚኖርበትን ከተማ መንገድ ያላገኘው በፍርሃት ይናጣል ። ድካሙ ትርፍ እያጣበት ፣ የረገጠውን መልሶ እየረገጠ አዙሮት ይወድቃል ። ውሻ ጭራውን ለመንከስ ሲሽከረከር እንደሚውል መንገዱን ያላገኘ እንዲሁ ይሆናል ። መንገዱ ግን ክርስቶስ ነው ። “ፍኖት ለኀበ አቡሁ ፤ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ” በማለት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ታወድሰዋለች ። ትርጉሙ እንዲህ ነው፡-
“ወደ አብ ለመድረስ ጎዳናው ፣ ወደ ወለደው ለመግባት በሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም.