የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አይዞህ መሞት የለም

“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።” ዮሐ. 14 ፡ 6-7 ።

ንጉሥ ዳዊት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ብዙ ትግል አሳልፎአል ። ዳዊት ያጽናናው ንጉሥ ሳኦል ካልገደልኩህ ብሎ አሳዶታል ። ከሞት የተረፈው ሰው ከጉድጓድ ያወጣውን ዳዊትን አልይህ ብሎ ጠልቶታል ። የእኔ ሕይወት ያለው የዳዊት መቃብር ላይ ነው በማለት ሳኦል አምኗል ። ሳኦል የዳዊት እርግጠኛ ጠላቱ ሲሆን የሳኦል ልጅ ዮናታን ደግሞ የዳዊት እርግጠኛ ወዳጁ ነበር ። ጨርሶ አይጨልምም ፣ ሁሉ ጠላት ሁሉ ወዳጅ አይሆንም ። ለዳዊት በእረኝነት አቅም የንጉሥ ጠላትን መሸከም ከባድ ነው ። ሰው ግን የተሰጠውን አልችልም አይልም ። ሳኦል የነገውን የዳዊት ክብር አይቶ ፈራ ፣ ዳዊት ደግሞ የዛሬውን ትግል አይቶ ተስፋ ቆረጠ ። መድረሻችን ከእኛ ይልቅ ለሚጠሉን ይታያቸዋል ። ዮናታን ምንም እንኳ አልጋ ወራሽ ቢሆንም ዳዊት እንዲነግሥ ይፈልግ ነበር ። ፍቅር ለወዳጁ ንግሥናንም ይለቃል ። እነዚህ ቡሩካን በብሉይ ኪዳን የሐዲስ ኪዳንን ኑሮ የኖሩ ነበሩ ። ዮናታን ዳዊት ተስፋ እንዳይቆርጥ ሊያበረታታው ሲሞክር ፣ ዳዊት ግን ሁሉም ነገር አብቅቷል የሚል ስሜት ውስጥ ገብቶ ነበርና እንዲህ አለ፡- “በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ ።” /1ሳሙ.20፡3 / ምሎ ተስፋ ቆረጠ ፣ የሞትን ድምፅ ሰማ ።

ሕይወት ሳይሆን ሞት የሚሸተው ፣ በአቅሜ የማልመልሰው ጠላት መጥቶብኛል ፣ መደበቅ እንዳልችል ሠራዊት ያስሰኛል ፣ ዘመን እንደ ገደል ከድቶኛል እያለ የሚጨነቅ ሰው ብዙ ነው ። “አዲሱ ሬሳ የቆየውን አስነሣ” እንዲሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳለፈውን ትግል እያሰበ ፣ የዛሬን ማዕበል እየደመረ እኔ ለደስታ አልተሠራሁም ፣ እንባ ቀለቤ ፣ ልቅሶ ኑሮዬ ነው የሚል ዕለት ዕለት እየጨመረ ነው ። በሞትና በእርሱ መካከል አንድ እርምጃ የቀረ የሚመስለው ሰው ብዙ ነው ። ያዕቆብ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ የጭንቀት ሌሊትን ፣ የፍርሃት አዳርን አስተናግዶ ነበር ። ወንድሜ ይገድለኛል ብሎ በመፍራት የምጥ ሌሊት አሳለፈ ። የነደፋቸው ስልቶች ዕረፍት አልሰጡትም ። ለሚስቶቹና ለልጆቹ ለማማከር ልቡ አላዘዘውም ። ብቸኛው ያዕቆብ ካልባረከኝ አልለቅህም ብሎ ሙሉ አዳር በእንባ ጸለየ ። ሲነጋ ግን እንደ ፈራው አልነበረም ፣ ወንድሙ በፍቅር ተቀበለው ፤ የዘመናት ፍርሃቱ ከንቱ ነበር ። ቦታው ላይ ሲደርስ ሁሉም ነገር እንዳሰበው አልነበረም ። ዳዊትም አብቅቶልኛል ፣ ካልተገናኘን ስላደረግህልኝ በጎነት ሁሉ አመሰግናለሁ ብሎ ዮናታንን ቢሰናበትም እውነቱ ግን ያ አልነበረም ። ዮናታን ቀድሞ ሞተ ፣ ዳዊት በሳኦል ዙፋን ተቀመጠ ። እንደውም የምንሞት ሲመስለን ልንኖር ተፈቅዶልናል ማለት ነው ። ጠላት የሞትን ድምፅ ሲያውጅብን ከዘማሪው ዳዊት ጋር በመሆን “አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ” ልንል ይገባናል ። /መዝ. 117፡17/።

ድባቴዎች እየተጫጫኑ ሲመጡ ሰውነት መዛል ፣ ተኝተን ስንነሣም የድካም ስሜት ፣ ደጁን መፍራት ፣ ከሰዎች ጋር መገናኘት አለመፈለግ ፣ ካለንበት ዞን ላለመውጣት መጣር ፣ እሞታለሁ የሚል ፍርሃት እየተጫነን ይመጣል ። ከብዙ ውጣ ውረዶች ፣ ጠብቀናቸው የነበሩት ነገሮች ካለ መሳካታቸው የተነሣ ፣ በዙሪያችን የሚያረካ ነገር ፈልገን በማጣት ወደዚህ ስሜት ልንገባ እንችላለን ። ድባቴዎች እንደ ድንጋይ የሚጫኑ ፣ የራሳቸው ሙቀት ያላቸው እስር ቤቶች ናቸው ። ፈጥኖ መጸለይ ፣ ቃለ እግዚአብሔር መስማት ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ፣ ከወዳጆቻችን ጋር መጫወት አስፈላጊ ነው ። የሚሰማን የሞት ድምፅ ከሰማይ የመጣ ሳይሆን ድባቴ ያስከተለው መሆኑን በመገንዘብ መንቃት አለብን ። ሞት ሌባ ነውና ማንም ጋ መጣሁ ብሎ መጥቶ አያውቅም ። ከሁሉ በላይ በውስጣችን የሞት ድምፅ ስንሰማ ክርስቶስ እኔ ሕይወት ነኝ ያለውን ማስታወስ ይገባል ። በባሕሩ ማዕበል እየተወዘወዘ ያለው ጳውሎስ ፣ የቁም እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም የሚወሰደው ሐዋርያ፡- “ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ” ብሏል ። /የሐዋ. 27፡20/። ክርስቲያን ተስፋ ቆርጦ አይቀርም እንጂ ተስፋ መቍረጥ ሊሰማው ይችላል ። ጳውሎስን ያበረታው ግን በሮም መናገሻ በቄሣር ፊት ወንጌልን ትሰብካለህ ያለው የጌታ ቃል ይፈጸማልና በባሕር ውስጥ አልቀርም የሚለው እምነቱ ነው ። ሰው ቃል እያለውም ይፈራል ፣ ተስፋ ይቆርጣል ።

የእኔ ነገር አብቅቷል የሚሉ ድምፆች እየተበራከቱ ነው ። ዙሪያውን ሲያይ ጨለማ ፣ ጆሮውን ቢቀስር የመርዶ ድምፅ የበዛበት ሰው ይደክመውና አብቅቷል ብሎ ለራሱ ይናገራል ። ይህ ድምፅ ብዙ ጊዜ በአፍ የማይናገሩት ለራስ ግን የሚነግሩት ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉም ነገር አብቅቷል ፣ ጌታም ሊያዝና ሊሰቀል ነው ፣ እንዴት ነው የምንኖረው ( ጅምሩ ለምን አላልቅም አለ ( በሚል ተስፋ መቍረጥ ውስጥ ገብተው ፣ ሰዉ ሁሉ አድካሚ ሆኖባቸው ሳሉ ጌታችን እኔ ሕይወት ነኝ አላቸው ።

አዎ በራሳችን ፈቃድ አልመጣንምና በራሳችን ኃይል መኖር አንችልም ። ክፉ ጠረን ያለው የሞት ሽታ ሲመጣብን ክርስቶስ የሕይወት ሽታ መሆኑን ማመን አለብን ። ዓላማችን ቢጠፋንም እግዚአብሔር ግን በእኛ ላይ ዓላማ አለው ። ተረስተን በምድር ላይ የቀረን ፣ የማይኖር ኑሮ የተሰጠን አይደለንም ። ለቀኑ የሚሆን ኃይል ከሰማይ ይመጣል ። ክርስቶስ ለቆሰለው ሥጋችን ፣ ለዛለው መንፈሳችን ሕይወትን ይሰጣል ። መጠውለጋችንን ሊያለመልም እርሱ ወደ እኛ ይመጣል ።

አላበቃም ሕይወት ክርስቶስ ነው ። ትሞታለህ የሚለውን የጠላት ድምፅ አትስማ ፣ ክርስቶስ ሞትን የሚያሸነፍ ሕይወት ነው ። ጨለማ የራሱ ህልውና የለውም ፣ የብርሃን አለመኖር ጨለማን ይፈጥራል ። ሞትም ህልውና የለውም ፣ ክርስቶስ ሕይወት ካልሆነልን የሚበረታብን ነው ። ክርስቶስ ሕይወት በሆነበት ሞት የለም ። አይዞህ ወዳጄ መሞት የለም !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ