የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቅንዓት ጦር የወጋው

ለጠቆሙ ሰዎች ጉርሻ እንሰጣለን የሚሉ መመሪያዎችና አዋጆችን እንሰማለን ። የሚጠቁሙ ሁሉ ለአገር ደኅንነት ያሰቡ ላይሆኑ ይችላሉ ። ተግባሩን እንጂ ተግባሩ የተሠራበትን ልብ የዓለም መሪዎች ማወቅ አይፈልጉም ። ቅንዓት የሚዋጋቸው ሰዎች ያለ መመሪያም ፣ ያለ አዋጅም ፣ ያለ ጉርሻም የሌላው መውደቅ ያስደስታቸዋል ። ቅንዓቱ አደግ እያለ ሲመጣም አብረን እንቸገር ፣ ሁሉም ይታመም የሚል ጭካኔ ላይ ይደርሳሉ ። ሁሉ ከተቸገረ የሚሰጥ ፣ ሁሉ ከታመመ የሚያስታምም አይኖርም ። ምኞትና ጸሎታችን “ሁሉ አይቸገር” የሚል መሆን አለበት ። “ምቀኛ ነጋዴ በእርሱ መዘረፍ ሳይሆን በጓደኛው ሰላም ማለፍ ይበሳጫል” ይባላል ። ከማይታዩ እስር ቤቶች ፣ ረቂቅ ከሆኑ ሰንሰለቶች አንዱ ቅንዓት ነው ። ቅንዓት ግዛቱ ሰፊ ነው ፣ በግዛቱም ፀሐይ አትጠልቅም ። በሁሉም አገር ቅንዓት አለ ። ቅንዓት የሰው ጠባይ ነው ። ምቀኝነት ግን የእኛ የግል ሀብታችን ነው ።

ቅንዓት የሚመጣው በማያውቁት ሰው አይደለም ። ቅንዓት የሚያውቁት ሰው ሲያድግና በጎ ሲደረግለት መከፋትና ማዘን ፣ በዚያ ሰው ላይም ጠልቶ የማስጠላት ዘመቻ መጀመር ነው ። የሩቁ አገር ሰው ሲያድግ “ለፍተው ነው ይገባቸዋል” የሚለው ቅንዓት ፣ የራሱ ሰው ሲያድግ ግን “ሰርቆ ነው” ይላል ። የማያውቃቸውና በቀለም የማይመስላቸው ሕዝቦች ዕራቁታቸውን ሲሄዱ ሲያይ “ሁሉም ነገር ያምርባቸዋል” ይላል ፣ የራሱ ሰው ሲለብስ ግን ይተቻል ። ቅንዓት ገንዘቤን ወስደውብኛል ይመልሱ የሚል የመብት ጥያቄ አይደለም ። ለእኔ እንጂ ለሌላው እንዴት መልካም ይሆንለታል የሚል ፍርደ ገምድልነት ነው ። ቅንዓት ዓለም የጋራ ቤት መሆንዋን ይረሳል ፣ ሁሉን ለእኔ ብቻ ብሎ ይደመድማል ። ቅንዓት እሳታዊ ዓይኖች ፣ ነዳፊ ምላሶች ፣ አውዳሚ እጆች አሉት ። በቅንዓት ጦር የተወጉ ሰዎች የዚያ ሰው ሀብት ዝና ፣ ክብር ድምቀት የእነርሱ እንደማይሆን ቢያውቁም ያንን ሰው ካልጣሉ ዕረፍት የላቸውም ። ቀናተኛ ግን ይበልጥ ያሳድጋል እንጂ አይጥልም ። ቅንዓት በውስጡ የገባ ሰው ቀን ዕረፍት ፣ ሌሊት ማሸለብ የለውም ። ዞሮ አይደክመውም ፣ ስም ሲያጠፋ በልክ ሳይሆን ከልብ በላይ ነው ። ማኅበረሰቡ የሚጠላውን ፣ ሁሉም ሰው የሚጸየፈውን ክፉ ግብር ቀናተኛው ያጠናል ። ለጠላው ሰው ያንን ስም ይሰጣል ። ያልተማረ ወገን ሆ በል ሲሉት ሆ የሚል እንጂ እስቲ ላጣራ ባይ አይደለም ። የቀናተኞች ብቸኛ ደጋፊ ያልተማሩና የማያስተውሉ ወገኖች ናቸው ። ቅንዓት ጨካኝ ከመሆኑ የተነሣ ገድሎ እንኳ የማይረካ ነው ። ዕድሜ እንዳስተማረን የተነቀፈና የተጠላ ሰው ብዙ ጊዜ መልካም ሰው ነው ። ያንን ሰው ቀርቦ ማየት ፣ አዘንብሎ ማድመጥ ይገባል ። ቀናተኛ ሰማይን ለሥላሴ የተወዉ በቸርነቱ ነው!

ቀናተኞች ትልቅ በሽታቸው የሰው ሳቅና ደስታ ነው ። የዚያን ሰው የጸሎት መልሱን ለማበላሸት ይነሣሉ ። በዚህ ምክንያት ከተቀባዩ ጋር ሳይሆን ከሰጪው ጋር ይጣላሉ ። ቀናተኞች አጥቻለሁ የሚሉ አይደሉም ፣ እርሱማ ወግ ነው ። ቀናተኞች ለምን ለእኔ አልተሰጠም ባዮችም አይደሉም ፣ እገሌ እንዴት ያገኛል ( ባዮች ናቸው ። ሰባኪ ሳይሆኑ ሰባኪን ይተቻሉ ፤ ቦታውን እንዲለቅ ይጥራሉ ። ነገር ግን ሰባኪውን ተክተው መስበክ አይችሉም ። ጸጋ እግዚአብሔር የሚቀሙት አይደለም ። በሰው ገንዘብ መበልጸግ ይቻላል ። ሌቦችና ጉበኞች እያደረጉት ነው ። በሰው ጸጋ ግን ባለ ስጦታ መሆን አይቻልም ። ጸጋ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ። ቅንዓት ገና በልጅነት የሚቀረጽ ክፉ ጠባይ ነው ። በእኅት በወንድም በመቅናት ፣ ለእኔ ብቻ ይደረግ በሚል ስሜት የሚመጣ ነው ። ይህ ጠባይ ከጠዋቱ ካልተገረዘ እስከ ዕድሜ ልክ ተዋጊ ይሆናል ። የቀናተኞች ትልቁ መሣሪያቸው ስድብ ነው ። ስድብ ያ ሰው በሆነውና ባልሆነው እርሱን አሳንሶ ራስን ለማተለቅ የሚደረግ ትግል ነው ። ክብር በክብር እንጂ በዚያ ሰው ውርደት የሚገኝ አይደለም ። ቀናተኞች በከንቱ ይለፋሉ ። እግዚአብሔርም የጠሉትን ሰው በዓይናቸው ፊት ከፍ በማድረግ ፣ በራሱም ላይ የሹመት ዘይት በመቀባት ፣ ደረጃውን በማላቅ እንዲቀጡ ያደርጋቸዋል ። ቀናተኞች አይሞቱም ፣ ሞትን ግን ይኖሩታል ። ውስጣቸው ሙቅ ነው ፣ ነገር ግን ወንድምን ለማጥፋት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ በራሳቸው እሳት የሚቃጠሉ ቀናተኞች ናቸው ።

እንኳን ቀናተኞች ዝንብም ብዙ ጥፋት ታደርሳለች ። ቀናተኞች ለደስታ በመሠረቱት ትዳር ራሳቸውንና ያገቡትን ሰው ያውካሉ ። እነርሱን የሚታያቸው ፣ ሌላውን ሰው ግን የማይታየው ሥዕል አለ ። ብቻዋን የተቀመጠች ሚስታቸው ከሌላ ሰው ጋር ተቀምጣ ይታያቸዋል ። ቅንዓት ከራስ ወዳድነት ፣ ከበታችነት ስሜት ፣ ካልተገራ አስተዳደግ ፣ በእግዚአብሔር ሰጪነት ባለማመን ፣ በስግብግብነት ይመጣል ። የሚቀኑ ሰዎች ያኛው ወገን ከልቡ እግዚአብሔርን ስላመለከ ይበሳጫሉ ። ቃየን የቀናተኞች አባት ነው ። ቃየን እንደ አቤል ደግ መሆን ፣ ንጹሕ መሥዋዕት ማሳረግ አይፈልግም ። በአቤል ግን ይቀና ነበር ። እግዚአብሔርም ቀድሞ መከረው ነገር ግን አልሰማም ። ቀናተኞች ሌላውን ገደል ውስጥ ሳይከቱ በፊት ቀድመን መምከር አለብን ። በመጨረሻ አቤልን ገደለው ። ከዚያ በኋላ ግን ቀበዝባዛ ሆኖ ቀረ ። በቅንዓት ሚስታቸውን ፣ ባላቸውን የገደሉ ብዙ ናቸው ። የትዳር ጓደኛም አልፈልግም ብሎ ቢሄድ የቀረነው ከእግዚአብሔር ጋር ነውና መደነቅና ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን ብሎ የአጥፍቶ መጥፋት መርሐ ግብር መንደፍ አስፈላጊ አይደለም ።

ቀናተኞች ቅንዓታቸውን የሃይማኖት ካባ ያለብሱአታል ! በዓለም ላይ ከሚቀኑብን ሰዎች ጋር መኖር ከባድ ነው!

ቅንዓት አቅም ባገኘ ቍጥር ለክፋቱ ያውለዋል ። ስለዚህ ቀናተኞች በአቅማቸው ልክ ይበድላሉ ። ፍጹም ሰላም የሌላቸው ፣ ስለ ማንም በጎ ሲወራ ጭቃ መቀባት የሚቀናቸው ፣ ሌላው ካላነሰ ስቃዩ የማይታገሥላቸው ቀናተኞች ናቸው ። ቅንዓት እስር ነው ። እግዚአብሔር ይፈታል ። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡-“እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ። ንስሐ በመግባት ፣ በሰዎች ዕድልና ክብር ለመደሰት በመለማመድ ፣ ፍቅርን እሺ ብሎ በመታዘዝ ከቅንዓት መፈታት ይቻላል ።

አቤቱ እኔ አውጣኝ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ