የምንበላው የምንጠጣው ለራሳችን ነው ፣ የምንኖረው ግን ለሰው ነው ። ደስ ያለንን አንናገርም ፣ ደስ ያለንን ልብስ አንለብስም ፣ ሰዎች ደስ የሚላቸውን እንደ አዝማሪ እናዜማለን ፣ ሰዎች ደስ የሚላቸውን እንለብሳለን ። “ሰው አፍ እንዳትገባ” ፣ “ሰው እንዳያይህ” በሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ውስጥ ወድቀናል ። ጸጋ የሚቀበረው ፣ ተሰጥኦ ፈንቅሎ የማይወጣው ፣ አገር የማያድገው እርስ በርስ በመጠባበቅ ስንኖር ነው ። የሰው ምላስ ሰባሪ ነው ፣ በእነ እገሌ አፍ አትግባ እየተባለ ስለሚነገረን ለአገር የሚበቃ ስጦታ ይዘን እቤት ተቀብረን እንቀራለን ። ፍርሃቱ እያየለ ሲመጣም የገዛ ቤተሰባችንን እንኳ ማነጋገር ፣ በጸጋችን መጥቀም አንችልም ። በርግጥም ቀና ያለውን ሰው በብረት ዘነዘና መትተው የሚፈጠፍጡ ሁልጊዜ በንቃት ላይ ናቸው ። ቀና ያለ ፣ ለዛው ያማረ ፣ እውቀቱ እያሸተ ያለ ሰው ስናይ ከመደሰት እንፈራለታለን ። በአገሩ ላይ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲናገሩ አፈ ማር ፣ ሲሠሩ መልአክ ተብለው ለመወደስ ተደራጅተዋል ። ቅስም ለመስበር ፣ ከመስመር ለማስወጣት ፣ ብለን ነበር የሚለው ትንቢታቸው እንዲሰምር አፋፍ ላይ ያለውን ገፍተው መጣል የሚያስደስታቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ። ነገር ግን ተሰብረን ካልጠበቅነው ማንም ሊሰብረን አይችልም ። ሰዎች መስበር ሥራቸው ሊሆን ይችላል ፣ አለመሰበር ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው ። ሞተን ካልጠበቅነው ማንም አይገድለንም ። የአገራችን ሰው ላለመለወጥ ተጠንቅቆ የሚጓዝ ነው ። በዚህ ውስጥ አሸንፎ መውጣት ፣ በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፍ ታሪክ መጻፍ ፣ እግዚአብሔር የመከረው ሰው ጠባይ ነው ።
ንጽሕናችንን እንኳ የምንጠብቀው ከሰዎች ጋር ቀጠሮ ካለን ነው ። ደኅና ልብስ የምንለብሰው ሰርግ ሲገጥመን ነው ። ቤታችንን የምናጸዳው እንግዳ የሚመጣ ከሆነ ነው ። የገዛ ጥርሳችንን የምንቦርሸው ደጅ የምንወጣ ከሆነ ብቻ ነው ። ለራሳችን ክብር ፣ ለሕይወታችን ንጽሕና ያስፈልገናል ። በደጅ ስልክክ ብሎ የሚታየው ጉብል ቤቱ የተዝረከረከ ነው ። መሬት ለመርገጥ የሚጸየፈው ጎበዝ እቤቱ መሬት ላይ የሚተኛ ነው ። ይሉኝታ ጉረኛ ፣ የዛሬ መመኪያ ብናጣ በአያት በቅድመ አያት የምንመካ እያደረገን ነው ፤ ግጥም እየተወራወርን በአፍ ጦር መወጋጋት ፣ ሰውን ሰብሮ መግባት እንደ ድል መቍጠር ጠባያችን ከሆነ ሰንብቷል ። የምንማረውም እውቀት አስፈላጊ ስለሆነ ሳይሆን መሃይም ብለን ሌላውን ለመሳደብ ነው ።
ያለ አቅማችን ሰዎችን መጋበዝ ፣ ተበድረን ሰርግ መደገስ ፣ በር አዘግተን የሁሉንም ሒሳብ መክፈል እንፈልጋለን ። ብዙ ትዳር የድግስ ዕቃው ሳይመለስ ጠብ የሚጀምረው ለይሉኝታ ብለው በገቡበት ዕዳ ነው ። በአቅማችን መኖር አልቻልንም ፣ እውነተኛውን ነገር ከማድረግ ለሰው አፍ ብለን የምንከፍለው ይበዛል ። ባለ ትዳሮቹን ከማቋቋም ፣ ለአሞራ አብልተን ፣ አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ ብለን ዘፍነን እንሸኛለን ። በሚሊየን የተደገሰላቸው አዲስ ሙሽሮች የሚገቡት ኪራይ ቤት ውስጥ ነው ። ለቀጣዩ ወር የኑሮ ጭንቅ ውስጥ ይገባሉ ። ከሚለብሰው ተርፎት የሚከናነበው አለው ለመባል ቀሚስ ሳይኖረን ካባ እንደርባለን ። አስበን የምናደርገው ነገር የለም ፣ ሁሉንም ነገር ትእዛዝ እስኪመጣ እንጠብቃለን ። ሠራተኛው አለቃው እስኪመጣ የወሬ ስፌት ይሰፋል ፣ አለቃውን ሲያይ ይሯሯጣል ። የገዛ ሕሊናው የማያዝዘው ሰው ከቆሙት በታች ፣ ከሞቱት በላይ ነው ። ሽማግሌው ቆሻሻ ሲጠርግ ምነው እኛ እያለን የሚለው ብዙ ነው ፣ እኒያን ሽማግሌ የሚያዳክም እንጂ አስቦ የሚያጸዳ የለም ። እግዚአብሔር ለሠራው ምድር ፣ ለፈጠረውም ወንዝ ያስባል ፤ ስናጎሳቁለው ይቀጣናል ። የምንበክለው ተፈጥሮ ዋጋ ያስከፍለናል ።
ከውጭ አገር በሚላክ ገንዘብ ሰው ሲጋብዙ የሚውሉ ፣ “እርስዋን ያቆይልን” እያሉ የሚያስመርቁ ፣ ለዚያች ልፋተኛ ግን መሬት እንግዛላት የማይሉ ብዙ ጨካኞች አሉ ። ልጆቹን እያስራበ ሲገባበዝ የሚውል ፣ አባ መስጠት ተብሎ ለመጠራት የማይጠቅም መጠጥ የሚራጭ ብዙ ነው ። ይሉኝታ ውዳሴ ከንቱ ምግቡ ነው ። በእውነቱ ስናየው ሥራ ማጣት እንዳለ ሆኖ ሥራ ቢገኝስ የሚሠራ አለ ወይ ( ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ቧንቧ ሠራተኛው ቀጥራችሁት የሚመጣው በወሩ ነው ። ሥራ ጠፍቷል ወይስ ሥራን ገፍተናል ( ብለንም መጠየቅ ያሻናል ። የምሠራውንም በመሰልቸት ስለምንሠራው የተሠራለት ሰው ሲረግመን ይኖራል ። ከሰው ጉቦ ተቀብሎ ወይም ቀምቶ ማታ ላይ ሰው ሲጋብዝ የሚውል አለ ። እንዴት ሰው ፣ ሰውን አስለቅሶ ሰውን ለማስደሰት ይሞክራል ( ይሉኝታ ፣ የይሉኝታ ኑሮ የማትሞት የማትድን አገር ይፈጥራል ። አምነንበት የምናደርገው በጎነት ፣ አምነንበት የምንተወዉ ክፋት ከሌለ እውነተኛ ሰዎች አይደለንም ።
ለሚለምነው መስጠት መልካም ነው ። ለሚሠራው ማበረታታት ተገቢ መሆኑን ማመን አልቻልንም ። ለጉራ ወፍራም ቲፕ ስንሰጥ የታክሲ ረዳትን ተከራክረን ድቃቂ ሳንቲም መቀበል ግን እንደ ድል እንቆጥረዋለን ። የሚለምነው እንደሚያሳዝነን የሚሠራው ሰው ሊያስደስተን ፣ በርታ ልንለው ይገባል ።
ይሉኝታ እውነታ አይደለም ። በይሉኝታ የጋበዘ ሰው ሲጸጸት ይውላል ። ይሉኝታ ሰውን ለማትረፍ እግዚአብሔርንና ራስን ማጣት ነው ። ሰዎችን የምንረዳቸው ስለራራን ነው ወይስ ለይሉኝታ ብለን ነው ( ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ሰዎች መልካም እንዲሉን የምናደርገው ደግነት በእግዚአብሔር ዘንድ የመጠሪያ ስሙ “ግብዝ” የሚል ነው ። ለወንበራችን ፣ ለስማችን ፣ ለታሪካችን የምንኖር ነገር ግን ለዛሬው ሰው የማንጠቅም መሆን አለመታደል ነው ። ዛሬ ላለው ሰው ምን ይጠቅመዋል ( ለትውልድስ ምን ይተርፋል ( ብሎ ሥራን መሥራት ተገቢ ነው ። የጠገቡትን ከማጥገብ የተራቡትን ማጥገብ ትርጉም ያለው ፣ ሕሊናንም እግዚአብሔርንም ማትረፊያ ነው ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም.