የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ይሉኝታ ወይስ እውነታ

አምልኮት በእውነትና በመንፈስ መሆን አለበት (ዮሐ. 4፡24) ። የአዲስ ኪዳን የአምልኮ መስፈርቱም ይህ ነው ። አምልኮ እግዚአብሔርን እያዩ በእውነተኛ ልብ መደረግ ይሻል ። በምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያን በአካል ፣ በመንፈስ ደግሞ በሰማያዊቷ ቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ መቅረብ አለበት ። መንፈሳችን በጸሎት ሰዓት ከብዙ ቅዱሳን ጋር በሰማይ ትገኛለች ። አጠገባችን ከምሥራቅ አገር ፣ ወይም ከደቡብ የዓለማችን ክፍል የመጣች መንፈስ ቆማለች ። እኛ ባናይም ብቻችንን ጸሎት አቅርበን አናውቅም ። እግዚአብሔር ጸሎትን የሚሰማው በእውነተኛ ልብ ፣ ዋጋ ከፋይነቱን በማመን ፣ በኅብረት ሲቀርብ ነው ። ጸሎትን በሚመለከት አፋዊ ማነብነብ የሆነበት፣ ልባችን ግን የሌለበት ልመና አለ ። ሁለተኛው ከሰው የውዳሴ ከንቱ ዋጋ ለመቀበል ፣ ጸሎተኛ ነው ለመባል የሚደርስ አለ ። ሦስተኛው ሰዎችን በመፍራት የሚደረግ የይሉኝታ ጾምና ጾሎት አለ ። በአገራችን አንዱ የአንዱ የጾም ፖሊስ ስለሆነ ምን ይሉኛል ( ብሎ የሚጾም ብዙ ሰው አለ ። የጾም ዋጋ ከፋይ ግን እግዚአብሔር ነው ። አምልኮ ከፈሪሀ እግዚአብሔር ወደ ሰው መፍራት ከወረደ ከንቱ ልፋት ይሆናል ።

ይሉኝታ አምልኮን የመበጥበጥ አቅሙ ከፍተኛ ነው ። ሰማይን እያየን ምድር እንድንቀር የሚያደርገን በመጠባበቅ ላይ የተመሠረተ አምልኮ ነው ። በዛሬ ዘመን ሰዎችን ለማብሸቅ የሚደረሱ መዝሙራት አሉ ። ለውድድር ፣ የእኔ ይበልጣል ለማለትም በእግዚአብሔር ስም የሚቀርቡ አምልኮዎች አሉ ። ደመወዛቸውን ታሳቢ አድርገው የሚቀድሱና የሚያስቀድሱ ፣ መቅደሱን እንደ ቢሮ የሚቆጥሩም አሉ ። አድናቂዎቻቸውን ለማስደሰት መቅደስ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ እያስተላለፉ የሚቀድሱ ፣ ኔትወርኩ ሲቋረጥ ሰው አላየኝም ብለው የሚረበሹ ካህናት እያፈራን ነው ። ትላንት ድምፅ ማጉያው የነጠቀንን ተመስጦ አሁን ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያው ሱስ ጨምሮ ወስዶብናል ። እግዚአብሔርን እያየ የሚዘምር የሚያመልክ እየጠፋ ነው ። ድካሙ አለ ፣ የሥላሴ በረከት ግን የለም ። እግዚአብሔርን ብንፈልገው ይገኝልን ነበረ ፣ የምንፈልገው ሰውን ስለሆነ የሰማይ በረከት አልተገኘም ። ቤተ ክርስቲያንና በዓላት ፎቶ መነሻ ከሆኑ ሰንብተዋል ። በዓላቱ በዩኔስኮ መመዝገቡ የሚደንቀው መንፈሳዊ አባት እያተረፍን ነው ። ለቱሪስት መስሕብ ተብሎ የሚደረግ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ በዓል የለንም ። በዓል ማለት እግዚአብሔርን በቤታችንና በአገራችን ላይ መጋበዝ ማለት ነው ። የበዓሉ እንግዳ እግዚአብሔር ነው ። በበዓላት ቀን የሚጎበኙን ሳይሆን አምነው የሚጠመቁ ካፈራን ለእንግዳው እግዚአብሔር ልጆችን እናበዛለት ነበር ። አምልኮቱና በዓላቱ ይሉኝታ ላይ ስለ ታሰሩ ፣ የልብስ ውድድር ፣ የግሪክ ቆብ ፣ የኢየሩሳሌም ካባ የምንባባልበት ስለሆነ እግዚአብሔር አልተቀበለውም ።

ይሉኝታ ግዛቱን እያሰፋ ሲመጣ ባለጠጋ የሆነች አገር ሳይሆን የምትመስል አገር እየፈጠርን እንመጣለን ። በአገራችን በብዙ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ ። አንድ የውጭ ዜጋ ቢሄድ የሚነካው ማንም የለም ። ኢትዮጵያዊ ግን በገዛ መልኩ በገዛ ወንድሙ ሊጎዳ ይችላል ። ግብዝነታችን ባዕድን የሚያከብር ፣ ራሱን የሚንቅ አድርጎናል ። እንግዳ ተቀባይ ነን ፣ ራሳችንን ግን ገና አልተቀበልንም ። እንግዶቻችንን በብዙ ዋጋ እንቀበላለን ፣ ድሆቻችን እንዳይታዩብን እንሰውራለን ። ውጤቱን ስናየው ከሚሰጡን የምንሰጣቸው ይበዛል ። “የስሙኒ ዶሮ የብር ካምሳ ገመድ ይዛ ጠፋች” ይባላል ። ይሉኝታዎቻችን በጣም ስጉ አድርገውናል ። ዝግጅቶቻችን ከመጠን ያለፉና ራሳችንን የምናስጨንቅባቸው ናቸው ። ይሉኝታ አባወራውን ትቶ እንግዳውን ወደ ማክበር ፣ የቤቱን ሰው ጥሎ የውጭውን ለማጥገብ ይሰደናል ። እዚህ ያለው ሙስሊም ስለ ፍልስጤም ፣ እዚህ ያለው ክርስቲያን ስለ እስራኤል አለሁ ይላል ። ፍልስጤምና እስራኤል ጠባቸው የመሬት እንጂ የሃይማኖት አለመሆኑን የሚገነዘብ ጥቂት ነው ። የራሳችን ስንት ችግር እያለብን ተንጠራርተን እናጨበጭባለን ። ቅድሚያ ለራሳችን አገርና ወገን መስጠት አለብን ። በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑ አገራት ለዜጎቻቸው ቅድሚያና ክብር የሰጡ ናቸው ። ራሳችንን ከናቅን የሚያከብረን የለም።

ሃይማኖት ለዋጮችን ሥራቸውን እንጠየፋለን ። በሃይማኖቱ የማይጸና ሰው በምድር ላይ የረከሰ ሰው ነው ። ይህ ትውልድ ምግብ ቤት እንደ መቀያየር ሃይማኖቱን ሲለውጥ ቅር የሚለው አይደለም ። ታዲያ አንድ ወጣት ሲነግረኝ የሄደባቸው ሃይማኖቶችና አስተማሪዎች ቅር እንዳይላቸው እስካሁን ሦስት ጊዜ ተጠምቄአለሁ ብሎኛል ። በጣም ያስፈራል ። ሦስት ጊዜ የሚያስጠምቅ ይሉኝታ ፣ የሄደባቸው ስለ ጎተጎቱት ነው ። ይሉኝታ ሃይማኖትን እንድናፈርስ እያደረገን ነው ። አልኮል መጠጥ መጠጣት ውድቀታችን እንጂ የእኛ መገለጫም አይደለም ። ሌላ ይሉኛል ብሎ የሚጠጣ ሰው አለ ። ኦርቶዶክሳዊነት በነቢያትና በሐዋርያት መንገድ መሄድ ነው ። መገለጫውም ቃለ እግዚአብሔርን በኑሮአችን ተዳሳሽ ማድረግ ነው ። ጾምን በኃጢአት የሚቀበል ፣ ጾሙንም በዓመፃ የሚፈስክ በእግዚአብሔር ስም የሚበድል ነውና ለራሱና ለአገር ትልቅ መከራ ያመጣል ።

እግዚአብሔር ከይሉኝታ ሊፈታን ፣ ለእውነታ ሊያኖረን ይቻለዋል ።

“እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ