ሐዋርያውን ትክ ብዬ አየሁት ። እርሱ ግን የዛሬ መልኬን ሳይሆን ነገ የምፈጽመውን የሃይማኖት ገድል እያሰበ ድልን በሚመኝ መንፈስ ያየኝ ነበር ። ማዕበል የሚያሰጋው መሐል ባሕር ላይ እንጂ ወደቡ ላይ ለደረሰች መርከብ አይደለም አለኝና “እኛ በዕረፍት ነን ፣ እናንተ ግን ገና በተጋድሎ ላይ ናችሁ፤ እኛ ስለ እናንተ እናስባለን ፣ ሰማይ በምድር ያሉትን ምእመናን እየጠበቀ ነው” አለኝ ። ያለፉት አባቶች ለሚመጡት ልጆች ቢመክሩ ፣ ያሉት ልጆች ያለፉትን አባቶች ቢያከብሩ ምንኛ መልካም ነው ! ብዬ አሰብኩ ። የሞቱት ስለ ዕረፍታቸው ሙታን ቢባሉ የሕያዋን አምላክ የተባለው በእነዚህም ቅዱሳን ላይ ነውና ሕያዋን ናቸው ።
ሐዋርያው አሁንም፡- “ወደ አገሩ የገባ አምባሳደር/እንደራሴ ከመንግሥቱ ጋር የሚኖር ፣ የክብር ዕረፍት ያለው ነው ። እናንተ ግን ከአገራችሁ ርቃችሁ ያላችሁ አምባሳደሮች ናችሁ በርቱ ። በገዛ አገሩ አምባሳደር ሁኖ የሚሾም የለም ። አምባሳደር ስትባሉ ከአገራችሁ ርቃችሁ እንዳላችሁ እንድታውቁ ነው ። ራሱን ጠርቶ አምባሳደርነቱን ትቶ ወደ አገሩ የሚመለስ የለምና የላካችሁ ጌታ እስኪጠራችሁ ድረስ ታገሡ እንጂ ደርሶ ሞታችሁን አትለምኑ ። የዕድሜ ልክ መከራችሁ በመንግሥተ ሰማያት የአንድ ደቂቃ ደስታ ይካሳል ። እኛ ክብሩን ስናይ ምነው ተመልሰን በተጋደልን ብለን ጠየቅን ። እግዚአብሔር ግን ወደ ዕረፍቴ የገባውን ወደ ውጭ አላወጣውም አለን ። ሰማይ ስትደርሱ ትልቅ የመሰላችሁ አገልግሎት ያንስባችኋል ። ዘመኔን ለእግዚአብሔር ሰጥቼ እያላችሁ በደስታ ሳይሆን እግዚአብሔር የእኔ ዕዳ አለበት በሚል ስሜት ስትናገሩ ይሰማል ። ክርስቶስ ሕይወቱን እንደሰጣችሁ ፣ ብዙ ኃያላን መላእክት ሳሉት እናንተን ደካሞቹን መውደዱን ትረሳላችሁ ። ዘመናችሁ ለእርሱ ካልሆነ ለሥጋና ለሰይጣን ለዓለም መሆኑ የማይቀር ነው ። ባዶ ጊዜ የለም ። እግዚአብሔር የሚከብርበት አሊያም ሰይጣን የሚያድፋፋው ዘመን ይኖራችኋል ። ስትመለስም የብዙዎችን ድካም ተሸክመው የእነርሱን ጥቂት ድካም የሚሸከምላቸው አጥተው በማዘን ወደ ዓለም የተመለሱትን አገልጋዮች በርቱ ፣ ሰማይ እየጠበቃችሁ ነው ፤ ዘመኑ እያለቀ ነውና ልደቱ ሲደርስ በምጥ አትሙቱ በላቸው ። ይህን የምልህ ወደ ላይ ስትወጣ ሰውን የሚለያይ የድንበር መስመር የለም ። ሰው ግን የድንበር መስመርን በአሳቡ እየሳለ ከእኔ ወገን አይደለህም ይላል ። ክርስትና ግን የእኛ ላልሆነው ፍቅርና ደግነት ማሳየትም ነው ። እግዚአብሔር ዓለምን እንደ አንድ ቤት ስለሚያውቃት አንድ ፀሐይን አደረገላት ። ከቤታችሁ ወጥታችሁ የሰማዩን ጠፈር ተመልከቱ ። አጭሩ ጣራ ቅርብ እያሳያችሁ ነው ። በምክር አድልኦ የለምና ይህን መልእክት ለሁሉ አድርስልኝ አለኝ ። ዞር ስል ቅዱሱ መልአክ ትክ ብሎ ያየኛል ። መላእክት በጆሮ ሳይሆን በልብ የሚሰሙ ሰዎችን ይወዳሉ ። እግዚአብሔርን መፍራት ባለበት ሠራዊቱ ይገኛሉ ። ሠራዊቱ ንጉሡንና የንጉሡ የሆነውን ሁሉ እንደሚጠብቁ መላእክትም የእግዚአብሔር የሆኑትን ምእመናን ይጠብቃሉ ።
ሐዋርያው ጳውሎስ የሕይወቱን ታሪክ ሊነግረኝ ተነሣሣ ። እኔም የረሳ መስሎኝ ላስታውሰው ስል በልቤ፡- “በሰማይ ዝንጋዔ የለም ። የሚያዘናጋው ያ ሥጋ እንደ አዳፋ ልብስ ወልቋል” አለኝ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቁሙ ይህን ሁሉ ሊነግረኝ ሲሻ መቀመጥ ቢችል ብዬ አሰብኩ ። እርሱ ግን፡- “ከምድር ገና በመምጣትህና የሰማይ ድንበር ላይ ስላለህ አላወቅህም እንጂ መቀመጥም ፣ መቆምም ፣ መነሣትም ፣ መንበርከክም እነዚህ ያለ ድካም የሚፈጸሙ ናቸው ። እንደቆምን ሺህ ዓመት ሊፈጸም ይችላል ። የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችን ነው ። ልጆቹ ወደ መንግሥቱ በሰላም ስለገባን ሁልጊዜ ደስ ይለዋል ። እኛም እንደ ቆምን ሳናውቀው ሺህ ዘመን በምድር ተቆጥሯል እንባላለን ። ሺህ ዘመንን እንደ አንድ ቀን የሚያደርግ የእግዚአብሔር ደስታ ነው ። እናንተ ዓመቱ ቶሎ አለቀ እያላችሁ ታዝናላችሁ ። ቶሎ ያለቀላችሁ ስለጣፈጣችሁ ነው ። መራራ ቀን አንዱ ሰዓትም የዓመት ያህል ነው” አለኝ ።
ሐዋርያው ቀጠለ፡- “እኔ በኪልቅያ አገር በዋና ከተማዋ በጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ነኝ ። አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአገራቸው አድረው አያውቁም ። ሃይማኖታቸውን በልባቸው አድርገው በመላው ዓለም ተበትነው ነበር ። ይህም በመላው ዓለም ያለውን ቋንቋ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል ። በእነርሱ ዓለምን መስበክ የፈለገው እግዚአብሔር በዚህ የቋንቋ ሀብት ባርኮአቸዋል ። ስደትንም የሚባርክ እግዚአብሔር ነው ። ከባቢሎን ምርኮ በኋላ የሜዶንና የፋርስ ጥምር መንግሥት ቀጥሎ የግሪክ መንግሥት ከዚያም የሮም መንግሥት መጣ ። እኔ የተወለድሁት ሮም መላውን ዓለም በምትገዛበት ፣ መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያደርሳሉ ተብሎ በሚነገርበት ዘመን ነው ። የሮማውያን አገዛዝ መላውን ዓለም በመንገድ ያገናኘና በመላው ዓለም ለመዘዋወር ፈቃድ የማይጠየቅበት ፣ ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እውቅና በመስጠት ብቻ ሁሉም አገር በራሱ ሥርዓት የሚኖርበት ነበር ። ክርስትና በዚህ ዘመን ሲመጣ ዘመንን መርጦ ነው ። እኔም በሮማ ግዛት ውስጥ በመወለዴ ሮማዊ ዜግነትን በልደት አግኝቻለሁ ። በዚያ ዘመን ሮማዊ መባል ትልቅ ክብር ያለውና በአጥቢያ ዳኞች የማይዳኝ ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ከተማ የሚዳኝ ነበር ። ለዚህ ነው በኢየሩሳሌም በተያዝሁ ጊዜ ወደ ሮም ለይግባኝ የሄድኩት ። በሮማ ዘመን ወንጌል መስበክ መልካም ነበረ ። ድንበሮች ክፍት፣ መንገዶች ምቹ ነበሩ ። ሮማውያንም እስከ ስድሳ አራት ዓመተ ምሕረት ድረስ ክርስትናን የሚቃወሙ አልነበሩም ። እግዚአብሔር የኦሪት መጻሕፍትን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በሦስተኛው ዘመን ወደ ግሪክ ቋንቋ እንዲተረጎም አደረገ ። መላው ዓለም ወደ ግሪክ ቋንቋ አዘንብሎ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ግሪክኛ ሁኖ ነበር ። መላው ዓለምም ብሉይ ኪዳንን ለማንበብ ዕድል አገኘ ። የክርስቶስ ልደት በቤተ አሕዛብም ይጠበቅ እንደነበር በበለዓም ትንቢት ፣ በሰብአ ሰገል ስግደት መረዳት ትችላለህ ። እኔም ባልመካበትም ፣ ሰማይ ለደረሰ ምድር ትንሽ ብትሆንም ሮማዊ ዜግነቴን ለወንጌል ማሮጫ ፣ የግሪክ ቋንቋ ማወቄን ለመስበኪያ አውዬው ነበር ። መርጠን ሳይሆን ያለንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ስናውለው ያለን ነገር የጸና ይሆናል ። በአካል ጠርሴስ ብሆንም በልቤ ግን በሃይማኖት አገሬ በኢየሩሳሌም ነበርሁ ። ከቤተሰቦቼም የዕብራይስጥን ቋንቋ ፣ ከረበናቱም የብሉይ ኪዳንን ትምህርት ተምሬአለሁ ። በወቅቱ የነበረውን የሄለናውያንን ወይም የግሪኮቹን የአኗኗር ዘይቤ ጠንቅቄ መርምሬአለሁ ። ስለ ክርስቶስ የሚጎዳኝን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመኝን ትቼ መጥቻለሁ ። የሚጎዳቸውን መተውማ ብልጦችም ያደርጉታል ፣ እኔ ግን የሚጠቅመኝን ነገር ትቼ ሀብትና ሥልጣንን ከንቱ ነው ብዬ ለክርስቶስ ገብሬአለሁ” አለኝ ።
ሐዋርያው ሲናገር ልቤ በደስታ ይዘል ነበር ። በሰማይ ያሉ ስለ ታሪክ የማያውቁ ይመስለኝ ነበር ። ሰማይ የምንሄደው ለመላቅ እንጂ ከእውቀት ለማነስ አይደለም ። የምንኖረው የእኛ ኑሮ ፣ ያለፉት ሺህ ዘመናትና የሚመጡት ዓመታት ሁሉ በሰማይ በሸራ ላይ እንደ ተወጠረ ሥዕል ይታያሉ ። ቀጣዩን ሊነግረኝ ሲል እኔም ቆይ እንደ ገና ላሰላስለው አልሁት ። ቅዱሳን የሚያግዙ እንጂ የሚታዘቡ አይደሉምና የጌታን ትዕግሥት አሳየኝ ። እኔም የልብ አውቃ ወዳጅ እፈልግ ነበርና ለካ ብዙ ወገን በሰማይ አለኝ አልኩ ።
ሐዋርያው ጳውሎስም ወደ ቀጣዩ ትረካ ከማለፉ በፊት፡- “አንተንና የአንተ የሆኑትን እግዚአብሔር ይባርክ” ብሎ ሐዋርያዊ ቡራኬ ሰጠኝ ። እኔም ቆሜ ከመቀበል ዝቅ አልኩኝ ። እኔ ተባርኬ የእኔ የሆነው ካልተባረከ የፈረሰ አጥር ነው ፣ የእኔ የሆነው ተባርኮ እኔ ካልተባረክሁ በበረከቴ የምሞት ነኝ ። አዎን ጌታ ሆይ እኔንና የእኔ የሆነውነ ባርክ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታሕሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም.