“በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።” ሉቃ. 2፡7 ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት በመወለዱ ድህነትን በፈቃዱ ተቀበለ ። ድህነት ግድ ሆኖብን እንጂ የምንፈልገው አይደለም ። በትምህርቱም “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” አለ ። በመንፈስ ድሀ መሆን ማለት ሁሉ እያለን እንደሌለን ሆኖ መኖር ነው ። የክርስትና መልኩም ትምህርቱም ትሕትና ነው ። ቤተ ልሔም ሁሉም ወደ ትውልድ ቀዬው ስለገባ ተጣበበች ። ለክርስቶስ የሚሆን ስፍራም አልተገኘም ። ዛሬ ልደቱ በትልልቅ ካቴድራሎች ይቀደሳል ፣ ይወደሳል ፤ እርሱ ግን በግርግም ተወለደ ። ሁሉም ወደ ተወለደበት ከተማ ስገባ ስፍራ አልተገኘም ፣ ዛሬም አብዛኛው ሰው ወደ ሰፈሩ ገብቷል ፣ በጎሣ በተቧደኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ተጨንቃለች ። ስለ አንድ የሰው ዘር ፣ ስለ አንድ ጥላ ወይም ባንዲራ የሚያስብ እየጠፋ ነው ። በትውልድ ሰፈሩ ብቻ የተጣበበ ለጌታ የሚሆን ስፍራ አያገኝም ። ዘረኛ ሰው ክርስቶስን ማስተናገድ ይቸግረዋል ።
እንግዳ ነገር በመላው ዓለም እየመጣ ነው ። ሥልጣኔ የሰው ልጆች ለእግዚአብሔር ልባቸውን እንዳይከፍቱ የጊዜና የእውነት ድሀ እያደረጋቸው ነው ። እንግዳ ልምምዶች እየመጡ ፣ መንፈሳዊ አምልኮ እየተጎሳቆለ ፣ በዓላትም እንደ መዝናኛ እየተቆጠሩ ነው ። ዛሬም ለክርስቶስ የሚሆን ስፍራ እያጣን ነው ። በፍልስፍና በዓለማዊ ምኞት የተጣበበ ልብ ክርስቶስን ለማስገባት ይቸገራል ። ዓለም በራስዋ ግርግር ተይዛ ችላ ያለችው ፣ ሞልቷል ብላ የመለሰችው ፣ የገፋችው ክርስቶስ በበረት አደረ ። መንበሩን ከተሸከሙት አንዱ ገፀ ላህም ነው ። ቤተ ልሔም ሰማይን መሰለች ። ይህን ክብር ለማየት የታደለች ድንግል ማርያም ናት ። ሰማይና ምድር የማይችሉትን በክንድዋ ታቀፈችው ፣ ምሉዕ አምላክ በጠባብ ግርግም ተወሰነ ። ልደቱን እኛ ነጭ ለብሰን እናከብረዋለን ፣ እርስዋ ግን የምታለብሰው አጥታ በቅጠል ሸፈነችው ። ልደቱ ለእኛ የእልልታ ዝማሬ ነው ፣ እርስዋ ግን በጭንቅ አሳለፈች ።
ግርግሙ አሕዛብን ይወክላል ። የእንስሳት ዓለም በሕግ የማይገዛ እንደሆነ ሕግ አልባ የሆኑት አሕዛብን ያመለክታል ። በግርግም መወለዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ አሕዛብ እንደምትሄድ አሳወቀ ። ሕግና ነቢያት ቤት ናቸው ። ቤት የነበራቸው ገፉት ። ከሕዝብና ከአሕዛብ ተፀንሶ ዓለምን እንዳስተባበረ በልደቱም ከአይሁድ እረኞችን ፣ ከአሕዛብ ሰብአ ሰገልን ጋበዘ ። እረኞቹ ከአሕዛብ ወገን ቢሆኑ የመምጣት አቅም አይኖራቸውም ነበር ፣ ሰብአ ሰገልም ከአይሁድ ቢሆኑ የሀብታቸውና የሥልጣናቸው ክብር አንቋቸው በቀሩ ነበር ። ማንን ለምን መጥራት እንዳለበት እርሱ ያውቀዋል ። ቤተ ልሔም ቤተ ክርስቲያንን መሰለች ። ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብና ከአሕዛብ የታዋጀች ናት ። ሀብታምና ድሀ በመቀመጫ የማይለያይባት የእኩልነት ስፍራ ናት ። በእንስሳት ምግብ ላይ የተኛው ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ ነበረ ። አባቶች እንደ ነገሩን ግርግሙ መሠዊያን ፣ አሕዛብን ፣ ቤተ ክርስቲያንን ያሳየናል ። የሁልጊዜ ቍርባን ሁኖ የምንበላው ክርስቶስ በከብቶች ምግብ ላይ ተኛ ። እርሱ ከሰማይ ወደ ምድር ሲወርድ ምድራውያን ግን ወደ ምድር መውረድ አቃታቸው ።
በረቱ ትሕትናን ፣ አሕዛብን ፣ መሠዊያን ይገልጻል ። በእንግዶች ማደሪያ ቢወለድ ኖሮ ክስተቶችን በማየት ግርግር ይፈጠር ነበር ። ማንም የማይመርጠውን ቦታ የሚመርጥ ፀጥታን ያገኛል ። መገፋት የጠለለ ሰዓት ለማግኘት ፣ ለቀጣይ ትውልድ ሥራ ለመሥራት በጣም ያግዛል ። በቤተ ልሔም የሆነው ሁሉ በአጋጣሚ አይደለም ፣ ሁሉም በእርሱ ፈቃድ ውስጥ ያልፋል ። እግዚአብሔር ለትሕትና ቀድሞ አቀደ ። ስናገኝ በቅን ለመፍረድ አሁን ማሰብና መዘጋጀት ይገባል ። ሰዎች ሁሉ ለከፍታ ያቅዳሉ ፣ እግዚአብሔር ለዝቅታ አቀደ ። አግኝቼ በሰጠሁ ፣ ተሹሜ ባገለገልሁ ብሎ ለመከጀል ጊዜው አሁን ነው ። ድንግል ማርያም ለመውለድ ብትቃረብም ሁኔታዋን አይቶ ያዘነላት አልተገኘም ። በእግዚአብሔር በተወደድነው መጠን ዓለም ይጨክንብናል ። ሕይወትን ቀለል አድርገን እንድንኖራት ጌታ በበረት ልደቱ አስተማረን ። ለድሆች አለኝታ ለመሆን በደጅ ተወለደ ።
ግርግም ቤት የማይሉት ቤት ፣ ሕግ አልባ ስፍራ ነው ። ቤቱ ደጅ ለሆነበት ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ከሌላቸው ጋር ለጊዜው እየኖረ ላለ ክርስቶስ የመውጫውን መንገድ ያሳየዋል ። የምናገለግለው ጌታ በበረት ተኛ ፣ እኛ በወርቅ ወንበር ካልተቀመጥን አገልጋይ የሆንን አይመስለንም ። ተረሳሁ ብለን እንጨነቃለን ፣ ስሜ አነሰብኝ ብለን እንጋደላለን ። ድሆችን ስንንቅ ትልቁን ድህነት የመረጠውን ጌታ እንንቃለን ። በድህነት የመጣውን የክርስቶስን ልደት ከእኩያዎችና ከባለጠጎች ጋር ማሳለፍ መክሸፍ ነው ።
ሰዎች ያላወቁትን ጌታ ከብቶች አወቁት ። በነቢዩ፡- “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም ፥ ሕዝቤም አላስተዋለም” የተባለው ተፈጸመ (ኢሳ. 1፡3)።
ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም.