..“ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት ፥ እንዲህ እያለ፡- ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።” ሉቃ. 19፡41-42።
በሽታ ሲይዘን ለሌላው ያዘዝነው መፍትሔ ይሰወርብናል ። የበሽታ ጠባዩም የምናውቀውን ማስጠፋት ነው ። ኢየሩሳሌም ለአሕዛብ ያስተዋወቀችው መድኃኒት ለእርስዋ ተሰወረባት ። የምንፈልገው ነገር ከፊት ለፊታችን እያለ ይሰወርብናል ። እያዩ አለማየት ይገጥመናል ። የሚያየው ዓይን ሳይሆን ልብ መሆኑ ይገባናል ። ኢየሩሳሌም አምላክ ሥጋ ለብሶ በመካከልዋ ነበረ ። ሰላምዋ እጅግ ቅርብ ሆኖ መጥቷል ። አላወቀችውም ። የመደበኛ ሠራተኞችን ያህልም አላከበረችውም ። ለሐሰት ነቢያት ፣ ለዘራፊ ረበናት ልብዋ ስስ የነበረችው ለመሢሑ ግን ጠንካራ ሆነች ። በቤትዋ ተቀብላው ምግብ ነፈገችው ። ናልኝ ብላው ሲመጣ አኮረፈችው ። ሕመምተኞችዋን ሲፈውስ እርሱን ላቍስለው አለች ። ሰላምን ስትገፋ የሚመጣው ሁከት ነው ። አድኖ የሚገዛውን ችላ ስትል የሞት መልእክተኛን ትጠራለች ። ዛሬ ልዩ ቀን ነበረች ፣ ኢየሩሳሌም በመጨረሻ ዕድልዋ ላይ ቆማ ነበር ። ዕድልና ባለ ዕድል ተላለፉ ።
ነገ ላይ የሞራልና የክብር ቅጥር ይኖር ይሆን ? ነገ ላይ መቅደሶቻችን ቀዳሽ ያገኙ ይሆን ? ጠፍተን መማር አንችልም ፣ ጥፋትን ካስተናገዱት አገራት ግን መማር አለብን ። ሰላማችን የሆነውን ክርስቶስን ማወቅና ለእርሱ ቃል መታዘዝ አለብን ። ዛሬስ አምላካችን እኛን ቁልቁል ሲያየን እያዘነ ይሆን ? በጥፋተኞች እናዝንባቸዋለን ፣ እርሱ ግን አዛኝ ነውና ያዝንላቸዋል ። ነገ ላይ ማኅበራዊ ኑሮአችን ይናጋል ፣ በዚሁ ከቀጠልን ሁሉም እኔ እንጂ እኛ ብሎ መቆርቆር ያቆማል ። ሃይማኖት የመቀለጃ ርእስ ፣ የመዝናኛ ቋንቋ ይሆናል ። የሚደመጥ አባት ፣ የሚመራ ሰባኪ አይኖርም ። ሕንፃ ታቅፈን ልንኖር ፣ ዛሬ ላይ ከገባው ገንዘብ ወለዱን እየበላን ብቻችንን ልንቀር እንችላለን ። አዋቂ ቀድሞ ያለቅሳል ፣ በጥፋቱ ቀን ተረጋግቶ ይቆማል ። በአንዳንዶች ቀብር ላይ እንባችን የደረቀው ቀድመን ስላለቀስን ነው ። ልባችን የጨከነው ብዙ ዘመን ስለመከርን ነው ። ብልህ ቀድሞ ያለቅሳል ፣ በቀብሩ ቀን ያረጋጋል ። ከተማችን ሞት ያደባባት ፣ ወጣቶች በማይድኑ በሽታዎች በየዕለቱ የሚለከፉባት ፣ ተማሪዎች ለትምህርት ወጥተው ሱስን ተምረው የሚመጡባት ሆናለች ። ዛሬም ከተማይቱን ቁልቁል ማየት ብንችል የምናለቅስበት ብዙ ነገር አለ።
መጪውን ዘመን የሰላም ያድርግልን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም.