መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ጌታ አይንቀንም

የትምህርቱ ርዕስ | ጌታ አይንቀንም

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው መሪዎች አሉ ። እነዚህ መሪዎች በነጻነት በሁሉ አገር የመሄድ ድፍረት የላቸውም ። የአገራቸው መንግሥት የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው ዜጎችም ባሉበት አገር ጥገኝነት ይጠይቃሉ እንጂ የመሄድ አቅም አይኖራቸውም ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመላው ዓለም ገዥ የሆኑት ሮማውያን ፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች አይሁዳውያን ሊይዙት እንደሚፈልጉ ባወቀ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በክብር ታጅቦ ገባ ። ከክርስትና መርሖች አንዱ ፍርሃትን ማሸነፍ መሆኑን ሊያስተምረን ይህን አደረገ ። ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ነው ። ስለዚህች ውርንጭላ ብዙ እውነታዎች አሉ ። ይህን ትእዛዝ ሲሰጥ፡- “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ ፥ ፈትታችሁም አምጡት ። ማንም፡- ስለ ምን ትፈቱታላችሁ ? ብሎ ቢጠይቃችሁ ፥ እንዲሁ፡- ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው።” ሉቃ. 19 ፡ 30-31። ውርንጫዋ ታናሽ ብትሆንም ጌታ አልናቃትም ። እግዚአብሔር ታናናሾችን አይንቅም ። በቤተ መንግሥት ግብዣ ታላላቅ ሰዎች ይጠራሉ ። እግዚአብሔር ሁሉንም ሲጠራ በቤተ መንግሥቱ የሚገኙት ግን በአብዛኛው ታናናሾች ናቸው ። ሁለተኛው ማንም ያልተቀመጠባትን ውርንጭላ ፈለገ ። ብዙ ርእዮተ ዓለም የጋለባቸው ፣ ብዙ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተቆራኛቸው ሰዎች ጌታን መሸከም/ማሳፈር አይችሉም ። የራሳቸው አስተሳሰብ የሌላቸው ፣ ሆ በል ሲባሉ ዘለው እሳት የሚገቡ ፣ የራሳቸው ባልሆነ ጠብ ገዳይ የሚሆኑ እነዚህ የጌታ ማደሪያ መሆን አይችሉም ። አቋም ያላቸው ፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚያስቀድሙ ፣ ከዘመን ጋር የማይለዋወጡ ፣ ሰዎችን ሳይሆን አምላክን ለማስደሰት የሚኖሩ ጌታ ይጠቀምባቸዋል ።

ውርንጭላዋ ታስራ ነበርና ፈትታችሁ አምጡልኝ አለ ። የታሰሩትን የሚፈታ አምላክ ነው ። እንኳን ለሰው ለእንስሳም ያዝናል ። ነጻነት ቀዳሚው ስጦታ መሆኑን ገልጾልናል ። ነጻነት ያላገኘ ፣ በሌሎች ተጽእኖ የሚኖር ሰው የማሰብ አቅም የለውም ። የሌሎችን አሳብ ያንጸባርቃል ። እንደማምንበት ሳይሆን እርስዎ እንዳሉት እያለ የገደል ማሚቱ ሁኖ ይኖራል ። ነጻነት የሌለው ሰው የመናገር ፣ የማስተማር ፣ የመምከር ገደብ አለበት ። ነጻነት በሌለበት ሕዝቦች በድንቁርና ጨለማ ይዋጣሉ ። አገር በቁሳዊ ለውጥ ውስጥ ቢሆን እንኳ ለመንግሥታቸው እንደ ማሽን ይኖራሉ ። ያመኑበትን ሳይሆን የማያምኑበትን ይናገራሉ ። ሰው ኖሮ መሞት ክብሩ ነው ፣ ሞትን መኖር ውርደቱ ነው ። ከላይኛው አእምሮ የታችኛው ሆድ በልጦብን እያስመሰልን እንኖራለን ። እሺ እሺ እያልን የበላዮችን ልንገድል እንችላለን ፣ እንቢ በማለት ግን እናድናቸዋለን ። ነጻነት ቀዳሚ ነው ። ነጻነት በሌለበት ዕድገት ሊኖር አይችልም ። ዕድገት ቢኖር እንኳ ደስተኛና በሰውነቱ የሚኮራ ማኅበረሰብ መፍጠር አንችልም ።

ውርንጫዋ ለጌታ ታስፈልጋለች ። ማንም ጠያቂ ቢመጣ ለጌታ ያስፈልገዋል ብለው እንደሚመልሱና ክርክርን ጸጥ እንደሚያደርጉ ነገራቸው ። ታናሽ ብንሆን ፣ ነጻነታችን ቢገደብ ፣ መፈታታችንን የማይወድ አካል ቢኖር እንኳ ለጌታ እናስፈልገዋለን ። በዓለማችን ላይ አስከፊ እስር ቤቶች አሉ ። ከእነዚያ የባሰው አለማወቅ ነው ። አለማወቅ የጨለማ ጉዞ ነው ። ራስንም ሌሎችንም የማያሳይ ነገር ቢኖር ጨለማ ነው ። ባለማወቅ ውስጥ ያለ ሰው ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሰው ክብር የለውም ። በጨለማ ውስጥ ምንም ዓይነት ቀለም ፣ ውበትና አስደናቂ ነገር የለም ። ባለማወቅ ውስጥ የሚኖር ሰው እንደ እንስሳት እንጂ እንደ ተፈጥሮው ልክ አይኖርም ። በንጋትና በሠርክ ፀሐይ መደነቅ አይችልም ። በተፈጥሮ ውስጥ ስላለው የእግዚአብሔር ልገሳ ማምለክ አይችልም ። ስለ ራሱም ያለው ክብር አነስተኛ ነው ። ዝም ብሎ ነዋሪ ነው ። ሕይወትም ድግግሞሽ እንጂ ወደ ታላቅ ግብ የምትጓዝ መሆኗን አይረዳም ። ባለማስተማር ምእመናንን የሚነዱ እንጂ የሚመሩ አገልጋዮች ሊኖሩ አይችሉም ። ምን እየሠራችሁ ነው ? እንዳይባሉ ሕዝቡን የማያስተምሩ ፈሪ አገልጋዮች አሉ ። ሕዝብን ባለማስተማር ገንዘቡን መሰብሰብ ፣ የሚጣላልን ማግኘት ይቻላል ። ያ ወገን የነቃ ቀን ጠላትነቱ በእጥፍ ይሆናል ። ፈጣሪንና ፍጡርን መለየት የማይችል ወገን ዛሬም ይዘናል ። የደነዘዘም ከማደንዘዣ ይነቃልና ወዮልን ። አንበሳን የሚያክሙ ሐኪሞች ማደንዘዣው ሳይበርድ ቶሎ ብለው ሥራቸውን መፈጸም ይፈልጋሉ ። ማደንዘዣው ካለቀ ሟች እንደሆኑ ይረዳሉ ። ባለማወቅ ማደንዘዝ ብዙ ርቀት አያስኬድም ። ለነገሩ ለአንቱ ማደሪያ የለዎት ከነ አህያዎ መጡ እንደሚባለው እኛም አልተማርንም ይሆናል ። ከዚህ ቀን ጀምሮ ለትምህርት መነሣት ይገባል ። አሊያ በወቅታዊ ርእስ ወገናችንን አማኝ ሳይሆን የምናደርገው ጦረኛ ነው ። ዘላለማዊነትን በወቅታዊነት እንዴት እንለውጠዋለን ?

ጌታችን በተአምራት በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ተቀመጠባቸው ። “አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት ፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ ፥ ተቀመጠባቸውም።” ማቴ. 21፡7። እናቲቱ የኦሪት ፣ ውርንጫዋ የወንጌል ምሳሌ ናቸው በማለት የተባረኩት አባቶች ነግረውናል ። በሁለቱም ኪዳናት የከበረው አንዱ እግዚአብሔር ነው ። ሁለቱም ኪዳናት እግዚአብሔርን ወደ እኛ የሚያደርሱ ናቸው ። በጥንቱ አገሩ ሰላም መሆኑን ለመግለጽ በአህያ ላይ ተቀምጠው ነገሥታት ለሕዝቡ ይታያሉ ። ተረጋግታችሁ ኑሩ ፣ ሥሩ ፣ ዝሩ ለማለት ይፈልጋሉ ። አረጋግቶ መግዛት የነገሥታት መገለጫ ነው ። ሰው ጥላውን እንዳያምን ካደረጉት የደነበረ ፣ በድን የሆነን እየገዙ ይመጣሉ ። ሽምቅ ተዋጊ እንኳ ወንበር ሲይዝ ሰላም ነው ተረጋጉ ይላል ። በደስታ ለመምራትም ለመመራትም ሰላም አስፈላጊ ነው ። አባወራ ቤቱን ካላረጋጋ ትዳሩ ሊፈርስ ይችላል ፣ ልጆቹም በአእምሮና ሥነ ልቡና ጉዳት ውስጥ ይወድቃሉ ። ጌታችን ሰላም ነው ሊል በአህያ ውርንጭላ መጣ ። ከአምስት ቀን በኋላ ግን እንደሚሞት ያውቀዋል ። ሌሎች እንዲሞቱላችሁ ሳይሆን ለሌሎች ለመሞት ሥልጣንን ተመኙ እያለን ነው ። በጥንቱ ዘመን ቀድሞ የሚገደለው ጳጳሱ ስለነበር ኤጲስ ቆጶስ ለመሆን የፈቃደኝነት ማስታወቂያ ይወጣ ነበር (1ጢሞ. 3፡1)። ዛሬ ግን ኤጲስ ቆጶስነትን እንደ መሳፍንት ለመኖር የማይመኘው የለም ።

ጌታ አይንቀንም ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 16 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ