መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ተፈትኖ መማር

የትምህርቱ ርዕስ | ተፈትኖ መማር

“አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።” ሉቃ. 22 ፡ 32 ።

ጌታችን ለጴጥሮስ የተናገረው ድንቅ ተስፋ ነው ። ጴጥሮስ እንደሚወድቅ ጌታ ተናግሯል ። እምነቱ እንዳይጠፋ ግን ጌታ አሰበው ። ከጌታ ጋር እሞታለሁ የሚለው እምነቱ ቢጠፋ ፣ የጠፋውን ልጁን ጌታ ይቀበላል የሚለው እምነት እንዳይጠፋ አገዘው ። በእሳትና በስለት ፊት ለጌታችን ታማኝ መሆን ሊያቅተን ይችላል ፣ ከአንድ ወታደር ፣ ከአንድ ታማኝ ሎሌ አንሰን ልንገኝ እንችላለን ። እግዚአብሔር እኔን አይቀበለኝም የሚል አስተሳሰብ ግን ከባድ ነው ። መውደቅ ቢያቅት የጌታ እጅ እንዲያነሣን እጅን መዘርጋት ግን ተገቢ ነው ። የጴጥሮስ የድፍረት እምነቱ ቢጠፋም የመመለስ እምነቱ ግን አልጠፋም ። ለሰዎች እንዲጸኑ ለምነን ቢያቅታቸው ፣ ለመመለስ ግን ልቡን እንዲያገኙት መጸለይ አለብን ። ዛሬ የወደቀ ሰው የሁልጊዜ ውዳቂ አይደለም ፣ በመሠረቱ የሚወድቅ የቆመ ፣ የተራመደና ከፍ ያለ ቦታ የተቀመጠ ነው ። የወደቁ ሰዎች ሁሉ ትላንት ሌላውን የሚደግፉ ፣ ወደ ዓላማቸው የሚገሰግሱ ፣ በክብር ላይ የነበሩ ናቸው ። የወደቁ ሰዎች ትልቅ ፈተናቸው እግዚአብሔር እንደሚምራቸው እምነት ማጣትና ማፈር ነው ። ሰይጣን በሐፍረት ይዋጋቸዋል ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሚል ትልቅ እንቅፋትም ይይዛቸዋል ። እነዚህን ሰዎች ማበረታታት ለእነርሱም መጸለይ ይገባል ።

የወደቀን የሚረዳ መውደቅን ያወቀ ነው ። ጌታችን ለጴጥሮስ “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።” ሉቃ. 22 ፡ 32 ። ጴጥሮስ እንደሚመለስ ፣ ውድቀት በትንሣኤ እንደሚለወጥ ጌታ ነገረው ። ሰዎች የምናይላቸውን ከፍታ ይወርሳሉ ። የሚሄዱትም ወደ ተናገርንላቸው ተስፋ ነው ። በሰዎች ላይ ያለን እምነት አንድ ቀን ራእያቸው ይሆናል ። ቃል ያነሣል ፣ ቃል ይጥላል ። ሰዎች አሁን ያሉበትን ውድቀት ሳይሆን ነገ ላይ የሚኖራቸውን ከፍታ ማየት አስፈላጊ ነው ። ሰው በቆመበት ቦታ አይኖርምና ። ብዙ እልፍ የምናደርጋቸው ሰዎች አሉ ። የቆመ ሰው የማቆም አቅም አለው ። እልፍ ስናደርጋቸው እልፍ ነገር ይሰጡናል ። ሰው ባዶ ሊሆን አይችልም ፣ ወይ ያሳርፈናል ፣ ወይ ያስጨንቀናል ። በሰዎች ላይ የምናፈሰው መዋዕለ ንዋይ መልሶ ለራሳችን ነው ። ጌታችን ከጴጥሮስ ውድቀት ባሻገር እንደሚመለስና ለብዙዎች መጽናናትና መጽናት ምክንያት እንደሚሆን ተናገረ ። ውድቀት ይህን የማስገኘት አቅም ስላለው ሳይሆን እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ ስለሚያስተምር ነው ። የወደቀ ሰው ይህም ያልፋል ብሎ መምከር ይችላል ። የወደቀ ሰው የሌላውን ቍስል መረዳትና ስሜትን መካፈል ይችላል ። የወደቀ ሰው የወደቀን መርዳት ይችላል ። ብዙ ሰው አቅም አለው ፣ ስሜታዊ እርዳታ ስናደርግለት ከእኛ የተሻለ ብርታቱን ማውጣት ይችላል ። ሰዎች የሚገነዘባቸው ሰው ይፈልጋሉ ፣ የሚፈርድባቸውንና ሊገባው የማይችለውን ሰው ይሸሻሉ ። የሚገነዘባቸውን ሰው ይፈልጋሉ ። ሕመምን ከታመመ ጋር ማውራት የስሜት ደጋፊ ማግኘት ነው ።

ጴጥሮስ የወደቀው በጠማማነት አይደለም ። አንዳንድ ሰው ማፍቀር ፈልጎ ራሱን በጥላቻ ውስጥ ያገኘዋል ። ኳስ በጣም የሚወዱ ግን መጫወት የማይችሉ ብዙ ሰዎች አሉ ። ጴጥሮስ ጌታን በጣም ማስደሰት የሚፈልግ ግን ያልቻለ ሰው ነው ። ጌታም በተግባሩ ሳይሆን በመሻቱ ተቀበለው ። ሜዳው ላይ ሲደርሱ ነገሮች እንዳሰብናቸው ቀላል ላይሆኑ ይችላሉ ። ለማፍቀር ወጥቶ የሚሰበረው ፣ የሚያዝነው ፣ ራሱንና ያፈቀረውን የሚጎዳው የገጠመውን ነገር ማስተዳደር አለመቻሉ ነው ። ሲዋደዱ መጣላትም እንዳለ አስቦ መዘጋጀት መልካም ነው ። ጥንቃቄ ጥርጣሬ አይደለም ። የሰዎችን መሻታቸውን መገንዘብ ብንችል በተግባራቸው ብቻ አንገመግማቸውም ። ለእኛ ያላቸው አስተሳሰብ ምን እንደሆነ በማሰብ በመሻታቸው ተግባራቸውን ይቅር ማለት አለብን ። አንዳንዶች ጥሩ ፊት ያሳዩናል ፣ ጥሩ ቃል ይናገሩናል ፣ ልባቸው ግን ጩቤ ነው ። ከጀርባችንም ጦር የሚሰብቁ ፣ አድማ የሚፈጥሩ ናቸው ። ሌሎችንም የምንርቃቸው ለራሳቸው አልሆኑምና ለእኔም አይሆኑም ብለን ነው ፣ ይህም መታሰብ አለበት ።

ጴጥሮስ የወደቀው ከመጠን በላይ በራሱ በመደገፉ ነው ። በራስ መደገፍ በትልቁ ጸሎትን ያስረሳል ። የሚጸልይ ሰው ሲገጥመንም እንደ ሰነፍና እንደ ፈሪ እንድናየው ያደርገናል ። ትምክሕት መዘናጋትን ያመጣል ። በዚያ ጉዳይ ላይ ዝግጅት ስለማይኖረው በራሱ የሚመካ ሰው ቶሎ ይወድቃል ። ትምክሕት የጸሎት ጠላት ነው ። መጸለይ ባቆምንበት ጉዳይ የምንወድቀው ጠላት በመዘናጋታችን ስለሚያገኘን ነው ። ትምክሕት ፈራጅ ያደርጋል ፣ ሌሎች አይረቡም እንድንል ያደርጋል ። ብዙ ጊዜ የሚታመሙ ረጅም ዘመን ይኖራሉ ። ከበሽታው ጋር ይላመዳሉ ፣ ይጠነቀቃሉ ። ታሞ የማያውቅ ግን ጥንቃቄ ስለሌለው የተጎዳ ቀን መቋቋም ይከብደዋል ። አልወድቅም ብሎ የሚያስብም ድንገት ሊወድቅ ይችላል ።

በሕይወት ውስጥ ተፈትኖ ማለፍ ዓላማው የሚፈተኑትን ለማጽናናት ነው ። እግዚአብሔር በዚያ ፈተና ውስጥ ያሳለፈን ባለፍንበት መንገድ ለሚያልፉት ውኃ እንድናቀብል ነው ።

ፈተናችንን መማሪያና ማስተማሪያ ካደረግነው ያ ጊዜ አልባከነም ። መምህር አስተምሮ ይፈትናል ፣ ሕይወት ግን ፈትና ታስተምራለች ይባላል ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ