መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » አንድ ቀን አለ

የትምህርቱ ርዕስ | አንድ ቀን አለ

ለዘመናት የጠበቅነው ወረፋ የሚደርስበት ፣ ስማችን ተጠርቶ የምንሸለምበት ፣ አደባባዩን የምንወርስበት ፣ ጥላቻን በፍቅር የምንለውጥበት ፣ ርግማኑ ቀርቶ ምርቃት የሚዘንብበት አንድ ቀን አለ ። ስህተታችን የሚታረምበት ፣ ውድቀታችን በትንሣኤ የሚለወጥበት ፣ ቀና ብለን የምንሄድበት ፣ በሕሊናችን ፊት ነጻነት የምናገኝበት ፣ ተስፋ ለቆረጡብን ተስፋ የምንሆንበት አንድ ቀን አለ ። የገፉን የሚያፍሩበት ፣ ስድብ የተለማመዱብን ምን ሆኜ ነበር? የሚሉበት ፣ የከሰሱን የሚመሰክሩበት ፣ ሞታችንን የተመኙ ዕድሜ ይስጣችሁ ብለው የሚመርቁበት አንድ ቀን አለ ። ያልተረዳናቸውን ሰዎች የምንረዳበት ፣ ስህተት የመሰለን እውቀታቸውን የምናከብርበት ፣ የእነርሱ መኖር ለእኛ በጣም የሚያስፈልግበት ፣ የወዳጅን ዋጋ የምናውቅበት አንድ ቀን አለ ። ያለፋን ኑሮ የሚሸነፍበት ፣ የተጫነን ደመና የሚገፈፍበት ፣ ሞት ሞት ያሰኘን ትግል ገለል የሚልበት ፣ የተሰናበትነውን ፍቅር ሰላምታ ሰጥተን የምንጀምርበት አንድ ቀን አለ ። ያስተማሩንን የምናመሰግንበት ፣ ያሳደጉንን የምናኮራበት ፣ ልጅነታችንን ያልናቁትን የምናከብርበት ፣ ልጄ ላሉን ልጅ የምንሆንበት አንድ ቀን አለ ። እንደ ኒቆዲሞስ በጨለማ ተምረን በገሀድ የምንሸኝበት ፣ ፍርሃታችንን የምንታዘብበት ፣ ከሰፈር ፍርድ የምንወጣበት ፣ የሰውን ሰውነቱን አቃለን ተስፋ ቢስ ባደረግንበት የምንጸጸትበት አንድ ቀን አለ ። ረሀባችን ዳርቻ ፣ ጥማታችን ድንበር የሚያገኝበት ፣ የሰው ያለህ እንዳላልን በሰው የምንከበብበት አንድ ቀን አለ ።

ትዕግሥቱን ቸል ብለን ፣ ቃሉን ተጋፍተን ፣ ፍርድ እንደሌለ ራሳችንን አሞኝተን የተጓዝንበት መንገድ የሚቀጣበት አንድ ቀን አለ ። የተሰጠንን መብት ያባከንበት ፣ በረከታችንን ያድፋፋንበት ፣ ሥራችንን ያቃለልንበት ምርጫ የሚዳኝበት አንድ ቀን አለ ። በፈረድንበት ፍርድ የምንገኝበት ፣ “የወረወርሁት አንካሴ መልሶ ለራሴ” ብለን እያለቀስን የምንማርበት አንድ ቀን አለ ። የሚወዱንን መለየት አቅቶን የሚጠሉንን ለማሳመን የሮጥንበት ፣ የወደድነውን አጥተን የጠላነውን የምንቀላውጥበት አንድ ቀን አለ ። የማይሞቱ መስለውን ያሳዘናቸው ወላጆቻችን ፣ ሲፈልጉን የራቅናቸው ወዳጆቻችን ምነው ዛሬ ባገኘኋቸው ብለን የምናጣበት አንድ ቀን አለ ። ተባብረን ምስኪኑን ያጠቃንበት ፣ አድማው ፈርሶ እርስ በርስ የምንበላላበት አንድ ቀን አለ ። ሥልጣን አገኘሁ ብለን ደጉን የገፋንበት ፣ አውርቶ አደሮችን ያከበርንበት እንደ ሥዕል የሚመጣበት ፣ እየተገረፍን የምንማርበት አንድ ቀን አለ ።

በቁመናቸው ያልሰማናቸውን ፣ ጥበባቸውን ጋርደው ያለፉትን ፣ ምነው ባልተማርሁ ብለው የተጸጸቱትን አዋቂዎች መቃብራቸውን ይቅርታ የምንጠይቅበት አንድ ቀን አለ ። ወገን ለይተን ያሳደድናቸውን ፣ ዘረኛ ሆነን ያፈረስናቸውን ፣ ሕፃናትን ሳይቀር የጠላንበትን ያንን ክፉ አእምሮአችንን የምንወቅስበት አንድ ቀን አለ ። የማንሞት መስሎን የገደልንበትን ፣ የማናጣ መስሎን የቀማንበትን ፣ የማንዋረድ መስሎን ያዋረድንበትን ፣ የማያልፍ መስሎን ሰባሪ ቃል የተናገርንበትን በእጥፍ የምንሸከምበት አንድ ቀን አለ ። ትዕግሥተኛው አምላክ ፈራጅ ነው ፣ ፈራጁም መሐሪ ነው ።

አልገባ ያለን እውቀት እንደ ቀትር በነፍሳችን ላይ የሚበራበት ፣ የተሰወረ ጥበብ ገንዘባችን የሚሆንበት ፣ መጋረጃው ተቀዶ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት አንድ ቀን አለ ። ፈርተን እንዳላነጋን በዕረፍት የምንተኛበት ፣ ተሸማቀን እንዳልተሰማራን በእምነት የምንወጣበት ፣ እንዳላቀረቀርን ቀና የምንልበት አንድ ቀን አለ ። እግዚአብሔር እኛን የሚጎበኝበት ፣ ከተራብንበት ቤት የምንጠግብበት ፣ የተሸከሙንን የምንሸከምበት ፣ ያከበሩንን የምናከብርበት ፣ የዋሉልንን የምናደንቅበት አንድ ቀን አለ ። ቀን የእግዚአብሔር ባሪያ ነው ። ቀኑን ለእኛ የሚያስገዛበት ፣ ያለፉ ወራቶች የሚካሱበት አንድ ቀን አለ ። ሃምሳ ዓመት ዘርተን ያላጨድነውን በሃምሳ ደቂቃ የምናጭድበት ፣ እግዚአብሔር ሲዋጋ በዝማሬ የምንቆምበት አንድ ቀን አለ ። እንደ ሰው የምንቆጠርበት ፣ ተሸልመን በጸጋው የምንከብርበት አንድ ቀን አለ ። እዚች ቀን ለመድረስ አንደበታችንን እንጠብቅ ። ይህችን ቀን ለማየት ከፈለግን የነቢዩን ምክር እንስማ፡- “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው ? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ ? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ ። ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም ።” (መዝ. 33 ፡ 12-14) ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 4 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ