የትምህርቱ ርዕስ | ገንዘብ

…ጌታችን ገንዘብን ምን ብሎ እንደ ሰየመው ማየት መልካም ነው ።

ክፉ ጌታ

በምድር ላይ ሁለት ጌቶች አሉ ቢባል ማንም ሰው እግዚአብሔርና ሰይጣን ብሎ ሊናገር ይችላል ። ጌታችን ግን እግዚአብሔርና ገንዘብ በማለት ተናገረ (ማቴ. 6፡24)። እግዚአብሔር ደግ ጌታ ነው ፣ ገንዘብ ግን ክፉ ጌታ ነው ። ለእግዚአብሔር የሚገዛ ሰው ለገንዘብ አይገዛም ። ገንዘብ ሲገዛን ጨካኝ ፣ እኔን ብቻ ይድላኝ ባይ ያደርጋል ። ገንዘብ የሚገዛው ሰው ለውርስ ብሎ የወላጆቹን ሞት ይመኛል ። ለውርስ ብለው አባት እናታቸውን ከቤት አስወጥተው የሚኖሩ ዛሬም አሉ ። ገንዘብ ጌታ ሲሆን እንደ ይሁዳ ክርስቶስን ያሸጣል ። ለገንዘብ ብሎ እውነቱን ሐሰት የሚል ፣ ተመሳስሎ የሚኖር ፣ ተምሮ እንዳልተማረ የሚያስብ አያሌ ሰው አለ ። ገንዘብ ሲገዛን ፍትሕን ማዛባት እንጀምራለን ፣ ላለው ባለጠጋ እንስቃለን ፣ ድሀውን እናስጨንቃለን ። የዓለም ሕግም ድሆችን ለመግዛት የሚረቀቅ ነው ይባላል ። ማነው ጌታችን ? እግዚአብሔር ወይስ ገንዘብ ?

የዓመፃ ገንዘብ

ዓመፅ እምቢታ አልገዛም ባይነት ነው ። ገንዘብ ሲያገኙ ጸሎት የሚያቆሙ ፣ ጓደኛውን የሚረሱ ፣ ከቤት ወጥተው የሚቀሩ ፣ ሁለት ትዳር የሚያምራቸው ብዙ ቀሊል ሰዎች አሉ ። ገንዘብ የዓመፅ መሣሪያ ነው ። ኃጢአት ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ አልገዛም የሚል ዓመፅ ነው ። ገንዘብም አለመታዘዝን ሊወልድ ይችላል ። ስለዚህ ጌታችን የዓመፅ ገንዘብ አለው (ሉቃ. 16፡9)። ብዙ ውሸቶች ፣ ብዙ መሐላዎች በንግድ ስፍራ ይሰማሉ ። ገንዘብ የገዛው ነጋዴ እናቱንም ያስማማል ። ከአፍኒንና ከፊንሐሶች ጋር ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን ያወድማል ። ገንዘብ ካወቁበት በሰማይ የሚያጠራቅሙት ሀብት ነው ። የሰማይ ባንክ ቤትም የድሆች ሆድ ነው ። የጠገበውን ብላ እያልን እንለምናለን ፣ ጠግቦ ሊጋፋን ይፈልጋል ፣ የተራበውን ግን እየለመነን እናልፈዋለን ።

“ሐሰት ከመናገር በእውነት ድዳ መሆን ፣ በዓመፅ በሰበሰቡት ገንዘብ ሀብታም ከመሆን ጥሮ ግሮ ባገኙት ገንዘብ ድሀ መሆን ይሻላል ።”

ከሁሉ የሚያንስ

ገንዘብ ከሁሉ በላይ ተደርጎ የሚታይበት ዘመን የእኛ ዘመን ነው ። የዓለም መንግሥታት ፣ ምሁራን ሳይቀር ዋናው ሰውነትና ክብር ሳይሆን ገንዘብ ነው እያሉ ነው ። ገንዘብ ከሁሉ የሚያንስ አሽከር ነው ። ዕቃን ሊገዛ ይችላል ፣ ሰላምን መግዛት ግን አይችልም ። እንደውም ገንዘብ የሰላም ተዋጊ ነው ። ከሁሉ ለሚያንሰው ገንዘብ ብለን ወንድማችንን ካድነው ፣ ወገናችንን ቀማነው ። ፍቅር ይበልጣል ፣ ሰው ይበልጣል ወደሚል እውነት መመለስ አለብን ። ገንዘባችን መሬት ላይ ቢወድቅ ሁሉም ሰው ያነሣዋል ፣ እኛ ብንወድቅ ግን የሚያነሣን የለም ፣ ገንዘብ ሰውን ተክቷልና መፍራት ይገባናል ።

ምን ገንዘብ ቢተርፈን ኑሮአችን ቢሞላ ፣
እንጀራ በወጥ ነው በወርቅ አይበላ ።


ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 19 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ