መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ደጉ ሳምራዊ

የትምህርቱ ርዕስ | ደጉ ሳምራዊ

ደጉ ሳምራዊን እናውቀዋለን። የወደቀን በማንሣት ላይ የተሰማሩ የእርዳታ ድርጅቶች ደጉ ሳምራዊን ለመጠሪያ ይጠቀሙበታል። በእኛም ዘመን በክፉ ምርጫ የወደቁ ምስኪኖች አሉ፣ ለወደቀው ሰው እጃቸውን የሚዘረጉ ደጉ ሳምራዊን የሚመስሉ ሰዎች ያስፈልጋሉ ። የወደቁ ሰዎችን ለማንሣት ማዘን ብቻውን በቂ አይደለም፣ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። የወደቀን ሰው ሲያዩ የሚያዝኑ፣ የሚያለቅሱ፣ የሚያስተዛዝኑ አሉ። ከብዙ የኀዘኔታ ድምፆች ይልቅ አንዲት እንቅስቃሴ የወደቀውን ታግዛለች። የወደቀን የምናየው ዜናውን ለማዳረስ ሳይሆን ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ነው። ይህን ዘመን ስናየው ተግባር በብዙ ምኞትና በብዙ ንግግር ተውጧል። እጅ እግር ያለው ሰብአዊነት፣ ሃይማኖት፣ ኀዘኔታና ንግግር እየጠፋ ነው። እንደውም የወደቀ ሰው የወሬ ርእስ ሆኗል። ጎርፍ የሚወስደውን ሰው ቪዲዮ ለመቅረጽ የሚያስችለው የሰው ወገን መጥቷል። የሚደባደቡ ሰዎችን ተዉ የሚል ሳይሆን ያንን የሚያሰራጭ አሳሳቢ ትውልድ እየመጣ ነው።

ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ በብዙ ነገሮች ተይዘዋል። በስብሰባና በውሳኔ ይረካሉ፣ የወሰኑት መፈጸሙን ግን አያረጋግጡም። የሚበልጠውንና የሚያንሰውን መለየት አልቻሉም፣ ቅድሚያ ለሰው የሚለው የእግዚአብሔር ዕቅድ በውስጣቸው የለም። ሦስተኛው ነገር ፍርሃት አለባቸው።  ብዙ አፎች ለስድብ ስለ ተከፈቱ ያለውን ነገር ከድነው ለቀጣዩ ማስተላለፍ ይፈልጋሉ። በዚህም የትውልድ ዕዳ ፣ የአገር መከራ ዕድሜ ያገኛል።

ደጉ ሳምራዊን ሁላችንም እንወደዋለን። ልንወደውም ይገባል። ደግ ነገርን ለመሥራት ማዘን ያስፈልጋል። ችግርን፣ ሞትን በመልመዳችን ማዘን እያቆምን ነው። ሞትን የለመደ አእምሮ መያዝ በራሱ የቁም ሞት ነው። ሰይጣን በግድያ ዓይነቶች ሞትን አለማምዶናል። ይህ ትልቅ በሽታ በመሆኑ እርዳታ ይፈልጋል። በግድያ፣ በታላላቅ የዘረፋ ተግባር፣ በጦርነት የተሳተፉ ሰዎች የሥነ ልቡና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱም ሞትን ለምደዋልና። ዘመናችንም በየትኛውም ጥግና ጎድጓዳ ስፍራ የተፈጸመውን ወንጀል በቅጽበት ያደርሰናል፣ መፍትሔ ግን መስጠት አልቻልንም። ደጉ ሳምራዊ ስምም፣ ታሪክም፣ ከፍታም ባይኖረውም ማዳን ችሏል። ባለጠጋ ባንሆን፣ የከበረ ስም ባይኖረን፣ ማኅበረሰቡ ባይቀበለንም የመፍትሔ አካል መሆን እንችላለን። የመፍትሔ አካል ለመሆን ማዘን፣ ሰዎችን መረዳት፣ ምቾታችንን መልቀቅ ፣ ቀጥሎ ምን ይሆናል ?የሚለውን ስጋት መጣል ግድ ይለናል። ካልቆረጡ ደግ  መሆን አይቻልም። ደግነት ከሌለም የወደቀ  አይነሣም። ደጉ ሳምራዊ ማን ነው?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ