መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች » ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች

የትምህርቱ ርዕስ | ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች

ፈሪሳውያን የስማቸው ትርጉም እንደሚያስረዳን ለእግዚአብሔር የተለዩ ማለት ነው ። ፓራሽ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ይመስላል ። ትርጉሙ መራቅ መለየት ሲሆን ፈሪሳዊ ማለትም የተለዩ ማለት ነው ። ራሳቸውን ከመላው ዓለም ብቻ ሳይሆን ከአይሁዳውያንና ከተራው ሕዝብ የተለዩ እንደሆኑ ይቆጥሩ ነበር ። እነዚህ ፈሪሳውያን በቃል ኪዳን ወደዚህ ሕይወት ይገባሉ ። ቃል ኪዳናቸውም ሕጉንና ትርጓሜውን በዘመናቸው ሁሉ ለማጥናትና ለመጠበቅ ሲሆን እርስ በርሳቸውም እንደ ወንድማማች ለመተያየት በሦስት ሰው ፊት ቃል በመግባት ይጀምሩ ነበር ። ፈሪሳውያን አነሣሣቸው ከክርስቶስ ልደት 200 ዓመት ቀደም ብሎ ነው ። ግሪካዊው የመንግሥት ሥልጣን ቦታውን በለቀቀ ጊዜ የግሪክ ቋንቋና ሔለናዊ የተሰኘው የዘመናዊነት ባሕል መላውን ዓለም መግዛት ቀጥሎ ነበር ። አጭር የነበረው የታላቁ እስክንድር ዓለምን የመግዛት ራእይ የቀጠለው በግሪክ ቋንቋና ፍልስፍና ነው ። ፈሪሳውያን አዲሱ ትውልድ በባዕድ ጠባይ እንዳይወረር ማንነታቸው እንዳይጠፋ በጣም ይጨነቁ የነበሩ ስብስቦች አገርን ለመታደግ የጀመሩት እንቅስቃሴ ነው ። እነዚህ ፈሪሳውያን ከሥልጣን የራቁ ሲሆኑ ቤተ መቅደሱ አካባቢ ላሉት ካህናት ጥሩ አመለካከት የላቸውም ። እኛ እናጠብቃለን ብለው ስለሚያስቡ ሌላውን ሁሉ እንደ ሕግ አፍራሽና ግዴለሽ ያዩት ነበር ። ፈሪሳውያን አገራዊ ስሜት ከእኛ ውጭ ለሐሳር ብለው የሚያስቡ ፣ ከእኛ በላይ ፉጨት አፍ ማሞጥሞጥ የሚሉ ነበሩ ። ጌታችን በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ቍጥራቸው ከስድስት ሺህ የማይበልጥ ቢሆንም በጣም ተጽእኖ ፈጣሪዎች ነበሩ ። የጌታችንን ስብከት በማወክ ፣ በመጨረሻ ለሞት አሳልፎ በመስጠት እጃቸው ረጅም ነበር ።

እነዚህ ፈሪሳውያን ሰባት ቡድኖች ወይም ዓይነት ነበራቸው ። ፈሪሳዊነት ጠባይ በመሆኑ በሁሉም ዘመን ያለ ነው ። በአዲስ ኪዳን ከዘጠና ስምንት ጊዜ በላይ በግልና በቡድን የተጠቀሱ ናቸውና ለእኛ ትምህርት ባይሆኑ ይህን ያህል ሽፋን አያገኙም ነበር ። ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች፡-

1- የታይታ ፈሪሳውያን

እነዚህ “የትከሻ ፈሪሳውያን” በመባልም ይታወቃሉ ፣ ሕጉ የተጻፈባቸውን ጥቅልሎች በእጃቸውና በግንባራቸው ላይ በማሰር ይታወቃሉ ። ሕጉ የተሰጠበት ዓላማ እንደ ጌጥ እንዲንጠለጠል ሳይሆን ለሕይወት ለውጥ ነው ። ፈሪሳውያን ግን ሕጉ ከልባችንና ከቤታችን ተርፎ በልብሳችን ላይ ተጽፏል የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ይጥሩ ነበር ። እነዚህ ፈሪሳውያን ረጃጅም ቀሚሶችን በመልበስ ፣ ዘርፋቸውን በማስረዘም መንደር ለመንደር የሚዞሩ ፣ የምስኪኖችን መቀነት የሚያስፈቱ ነበሩ ። ጻድቅነታቸውን ሁሉ ሰው እንዲያውቅላቸው ይፈልጋሉ ። እዩልኝ ስሙልኝ ይላሉ ። በጎ ተግባርን የሚያደርጉት ለሰው እንጂ የተፈጠሩበት ዓላማ መሆኑን ተገንዝበው አይደለም ። ዛሬም በጥቅስ ቤታችንና መኪናችን ተንቆጥቁጧል ። አማኝ መሆናችንን ለማሳየት የመሐላ ብዛት እንደረድራለን ። አንዱ በኢየሱስ ስም ፣ በጌታ ይላል ፣ ሌላው መድዬን እመቤቴን ይላል ። የሰቀልነው ጥቅስ ግን በዕለታዊ ኑሮአችን ላይ ተጽእኖ አያሳድርም ። የኢየሩሳሌም ፣ የግሪክ እያልን እናጌጣለን ፣ በኃጢአት ግን ወይበናል ። “ጠጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” እንዲሉ ከእኛ ይልቅ ልብሱ አማኝ ነው ። ጭንቀታችን ጌጠኛ መስቀል ወይም አይከን በሺህ ዶላር ለማንጠልጠል እንጂ የሕዝብን ስቃይ ለመካፈል ፣ የክርስቶስ የሕማሙ ወዳጅ ለመሆን አይደለም ። የምናገለግለው ሕዝብ በችግር ሰክሮ የምንሰብከውን እንኳ መስማት አልቻለም ። እኛ ግን በዘመናት ሁሉ እንደ ታየው ከሟች ጋር ሳይሆን ከገዳይ ጋር የምንሰለፍ ሆነናል ። የቀረው ልብሳችን እንጂ ጨካኝነት ሙሉ በሙሉ ወርሶናል ። ሕገ ፍቅር ሳይሆን ሕገ አራዊት ሰልጥኖብናል ። ያሸነፈ ብቻ የሚኖርበት ዓለም መሥርተናል ። ግፈኛን ተው ለማለት ግፍን ስላልተውን አፍ እያለን ዱዳዎች ሆነናል ። በዋና ከተማ ላይ እንተራመሳለን ፣ የተወለድንበት መንደር በሁከት ሲናወጥ የመጸለይና ተዉ የማለት የሞራል ልዕልና እንኳ አጥተናል ። “እውነት መናገር ካልቻልህ ዝም በል” ይባላል ። እኛ ግን በቍስል ላይ ጥዝጣዜ ለመሆን ከንቱ ንግግር መናገርን አላቆምንም ። “በየቀኑ በግ የሚያስበላ እረኛ ከተሸለመ ፣ ሸላሚው ቀበሮ ነው” ይባላል ። ይህ ሁሉ ሸብ ረብ ፣ ይህ ሁሉ ውድድር በግ የሚያስበሉትን ከፍ ለማድረግ ነው ።

ወጣቱ ከቀይ ሽብር አንሥቶ ሜዳ ላይ ሲወድቅ እንደሌለ ሁነን አልፈናል ። በየዘመናቱ የፈሰሰው የልጆቻችን ደም ዛሬ የሚበላ ምግብ ተገኝቶ አላስበላ ብሎናል ። በየጎጆው በረሀብ የሚሞቱት ሊቃውንት ረሀባቸው እየተፋረደን በሰላም ቤት ውስጥ ሰላም አጥተናል ። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ሁነን መጡ መጡ ከመባል ውጭ ምንም ትርጉም የማንሰጥ መሆናችን ያሳዝናል ። ቤተ ክርስቲያን የነፍስ ደጃፍ መሆንዋን ባንገነዘብ እንኳ የእንጀራዬ ገበታ ነች ብለን ብናከብራት መልካም ነበር ። አንድ ወጣት ለዚህ ቁመና እስኪበቃ የሚከፈለው ዋጋ ቀላል አይደለም ። ከፅንስ ጀምሮ ፣ በምጥ እስከ መወለድ ፣ በጣር እስከ ማደግ ድረስ ዋጋ የተከፈለበት ወጣት ሲሞት እንዴት በክርስቶስ ፍቅር ያለን ሰዎች ያስችለናል ( ወጣቱ ለማየት ሲያሳሳ ጦርነት ይቆርጠዋል ። ወላድም ቀኑ ጨልሞበት እንዳዘነ ያልፋል ። የዚህ ሁሉ ችግራችን ለባለጠግነት እንጂ ለወንጌል አለመሮጣችን ነው ። ለታይታው ፣ ለእዩኝ ስሙልኝ እንጂ ለእውነት አለመኖራችን ነው ። በዚህ ዘመን ቁመናውን የሚሸጥ አገልጋይ እያመረትን ፣ እየቀደሰ ፎቶ አንሺ የሚቀጥር ቀዳሽ እያበዛን ነው ። ጸሎቱ ባያርግ የሚደንቅ አይደለም ። የተሻለ ካገኘ ለመሄድ በጨረታው የማይገደድ አገልጋይ ሰብስበናል ። የመከረንን ስም ሰጥተን ፣ አላዋቂውን አነሣሥተንበት እናጠፋዋለን ። ግን ወደ ሥራችን ፍጻሜ እየተጓዝን መሆኑን እንዘነጋለን ። ነብር እንኳ ሲሞት ቆዳውን ትቶ ይሞታል ፣ እኛ ለትውልድ ምን ትተን እንሄድ ይሆን ?

አቤቱ በቤትህ ውስጥ የጠፋነውን አግኘን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም .

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ