ክርስትና ብዙ ነገሮችን ለውጧል። አይሁድ ከአሕዛብ ጋር በአንድ መንገድ መሄድ፣ በአንድ ቤት መመገብ፣ በአንድ መቅደስ ማምለክ አይችሉም ነበር። በሕግ ገደብ ፣ በራሳቸውም ጽዩፍነት ይህን ማድረግ አይችሉም ነበር። ክርስትና ግን ሕዝብና አሕዛብን አንድ ያደረገ፣ ቀራጭና አመንዝራን በንስሐ የተቀበለ፣ የጾታ ልዩነትን ወይም ንቀትን ያስወገደ፣ ዓለም አቀፍ ራእይን ይዞ የወጣ ፣ ግንቡን አፍርሶ ድልድይ የሠራ ነው። ሉቃስ ወንጌላዊ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰው ነው። ሉቃስ በክርስትና ውስጥ አማኝና አገልጋይ ለመባል የበቃው በሐዲሱ ሥልጣን ነው። ክርስትና የተራራቁትን የሰው ልጆች አቀራረበ።
በክርስትና ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸው አመለካከትም ተለውጧል። ግሪኮች እግዚአብሔር እጅግ ሩቅ ፣ ስሜት አልባ ፣ ወደ ፍጥረቱ ሊቀርብ የማይችል ኣምላክን ያስቡ ነበር። ይህ አምላክ ሊሰማና ፍጥረቱን ሊረዳ አይችልም። አይሁዳውያን የሕግ ሰዎች ነበሩና የሕጉን ባለቤት እንደ ዳኛ ያዩት ነበር። በእነርሱ ምልከታ ይህ አምላክ ጨካኝ ፣ መቅጣት የሚወድና አስጨንቆ የሚገዛ ነው። በክርስትና ግን እግዚአብሔር አፍቃሪ አባት፣ ነፍሱን ስለ ጠላቶቹ የሚሰጥ ልዩ ወዳጅ መሆኑ ተገለጠ። ሞቱና ትንሣኤውም ተሰበከ ። በሞቱ ፍቅርን፣ በትንሣኤው ኃይሉን ገለጠ። የሚኖርልን በሌለበት ዓለም ላይ የሚሞትልን ተገኘ፣ ሞትም የመጨረሻ ነው ተብሎ የሰው ተስፋ ተገድቦ ነበር ፣ ትንሣኤ የሞትን ግርማ ገፈፈ። በክርስትና ሰዎች ተቀራረቡ፣ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር ኑሮአችንን የሚካፈል ፍቅር መሆኑ ተገለጠ።
ወንጌላዊው ሉቃስ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ክርስቲያን ነው። ወንጌሉንም የጻፈው ለአንድ ሮማዊ ባለሥልጣን ወይም ለአሕዛብ ነው። አሕዛብ ሕዝቦች የሚል ፍቺ አለው። የሚገልጠው ግን አረመኔ የሚለው ነው። አይሁድ ከእነርሱ ውጭ ያሉትን አረመኔ፣ ጨካኝ፣ በምድር በሰማይ ስደተኛ ብለው ይጠሯቸው ነበር ። ወንጌላዊው ሉቃስ ሁለት ሙያዎች ነበሩት፦ የመጀመሪያው ሠዓሊ ነበረ፣ በዚህ ሙያውም የድንግል ማርያምን ሥዕል እንደ ሳለ በመላው ዓለም ይታመናል። ሁለተኛ ሙያው ሐኪም ነበረ። የሉቃስ ወንጌል ሥዕላዊ ወንጌል ነው። ሰሌዳው የሰው አእምሮ ቡሩሹ ቃላት ነበሩ። የሥዕሉ ፍጻሜ ክርስቶስ የሁሉ ወዳጅ ነው የሚል ነው። ሐኪም በሽታን የሚመረምር ፣ ሥራን በጥንቃቄ መሥራት ያለበት ነው ። ሉቃስ የክርስቶስን መዋዕለ ሥጋዌ በጥንቃቄ መርምሯል። የታሪኩ አካል የነበሩትን በቀጥታ በአካል አነጋግሯል። ጥሩ የታሪክ ተመራማሪም ነበር። ከሁሉ በላይ መንፈስ ቅዱስ በዘመናት ለሚነሡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን መልክ የሚያዩበት የሉቃስ ወንጌልን የመሰለ መስተዋት ትቶልናል። የሉቃስ ወንጌል መልክአ ኢየሱስ ነው።
ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ለቴዎፍሎስ ነው። አስቀድሞ በክርስቶስ ያመነና የተማረ ነው። እውቀቱ ሙሉ እንዲሆን ወንጌሉን ጻፈለት። ሉቃስ ለአንዲት ነፍስ ግድ የሚለው የክርስቶስ ተከታይ ነበረ። የአንድን ሰው ዋጋ የማያውቅ አገልጋይ መሆን አይችልም። ሺህ ሰው ካልመጣ ስብከት የማይመጣለት አገልጋይ ምስኪን ሰው ነው ። ለአንድ ኒቆዲሞስ በሌሊት፣ ለአንዲት ሳምራዊት በቀትር ስለ ተጋው ጌታ መናገር አይችልም። ባለ ሥልጣኖችን መጥላት የሐቀኝነት ምልክት እየተደረገ ነው። የዘመናችን ዲሞክራሲ ጥላቻን መግለጥ ነው። ባለ ሥልጣኑም ክርስቶስ ያስፈልገዋል ብሎ እንደ ሉቃስ ማመን ይገባል።
ቴዎፍሎስ የሚባል ሰው የለም ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ቴዎፍሎስ ማለት የእግዚአብሔር ወዳጅ ማለት ነውና ለሁሉም አማንያን የተጻፈ ነው ብለው የሚናገሩ አልታጡም። ነገር ግን ሉቃ .1፥1 በመግቢያው ላይ “የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ” በማለት አንድን ሮማዊ ሹም በማዕረግ ስም ይጠራዋል። ስለ አንድ ግለሰብም ይናገራል:: ክርስትና እኩልነት ያለው የመከባበር ሕይወት ነው። ሁለተኛው “ስለተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ” ይላል፣ ቴዎፍሎስ አስቀድሞ የተማረ ግን ተጨማሪ ማስረጃ የሚያስፈልገው ነው። “በየተራው ልጽፍልህ” በማለት አንድን ግለሰብ አድራሻ ያደርጋል። ቴዎፍሎስ ለሚባል ባለሥልጣንና ግለሰብ ወንጌሉ ተጽፏል። ቴዎፍሎስ ማለት የእግዚአብሔር ወዳጅ ማለት ነውና የመላው አማንያን መጠሪያ ሊሆን ይችላል።
በቤተ ክህነት በጣም የታወቁ ሰባኪ ነበሩ። እኚህ ሰው ጣዕማቸው፣ ስብከታቸው ልዩ ነው። መጨረሻ ላይ መንገድ ዳር ተቀምጠው በሰማንያ ዓመታቸው ሣንቲም የሚጠይቁ ሆነው አልፈዋል። የእኛ ቤት እያለ የሚናገረው የቅን ፍትሕ እንዲሰጥ የተቀመጠው አባት መሆኑ ይገርማል። ሰባኪ ለማኝ ቢሆንም አይደንቀንም፣ መፍረድ የሚችሉት አለቆች “አይ የእኛ ቤት” ብለው ያልፉታል። ታዲያ እኚህ መምህር ወመገሥጽ አባት “እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እግዚአብሔርን የምትወዱት ምእመናን” የሚለውን ሰላምታ ሁልጊዜ ሲቃወሙ ይሰማ ነበር። “እግዚአብሔር የሚወዳችሁ ትክክል ነው፣ እግዚአብሔርን የምትወዱት የሚለው ግን ሐሰት ነው” በማለት ይናገሩ ነበር። ብቻ እግዚአብሔር በጸጋው እንደ ወዳጆቹ ቆጥሮናል (ዮሐ.15፥15) ።
ወንጌላዊ ሉቃስ በመግቢያው ላይ ያነሣቸው ነገሮች ለሕይወታችን ጠቃሚ ናቸው።
በየተራ
ነገሮች ቅደም ተከተል ይፈልጋሉ። የዜማ መሣሪያዎች ቅደም ተከተላቸውን ስለሚጠብቁ ጣዕም አላቸው። ቅደም ተከተል የውበትና የጣዕም መገኛ ነው። የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሆሳዕና በአርያም ይሉ ነበር (ማቴ 21 ፥ 9) ። አእምሮአችንም ቤታችንም እንዳይዘባረቅ ቅደም ተከተል ማወቅ አለብን። መቅደም ያለበት፣ መከተል የሚገባው ነገር እንደ ግለሰብም እንደ አገርም አላወቅንበትም ። የሚቀድመውን አለማወቅ በብዙ ነፍስ ላይ መፍረድን ያመጣል። ጨካኝ ያደርጋል። የሃይማኖት አለቆች ይህን የሳቱ ይመስላል። ያሉት ጌጥ ላይ እንጂ የሚረግፈው ወገን ላይ አይደለም። በዓለም ያለው ሀብት በቂ ነው ፣ የሚቀድመውን ባለ ማወቅ ግን ይባክናል። በሕይወታችን እየሮጥን ያለ ነው ለሚቀድመው አይመስልም። አንዳንድ ሰው ጤናው እያበራ ምልክት እያሳየ ቢሆንም ገንዘብ በማከማቸት ላይ ነው። ላይነሣ ሊወድቅ ይችላል።
ማዘጋጀት
አንድን የተሰናዳ ነገር ማቅረብ ለማሳመንም ይጠቅማል። ሳንዘጋጅ ትውልድ እንደ ጎርፍ መጥቶብናል ። ዘመን የከዳን ምስኪን አገልጋይ እንመስላለን። ሳንዘጋጅ በፉከራ ብቻ ዘመኑን የእኛ የምንደርገው ይመስለናል። በብዙ መንገድ መዘጋጀት ካልቻልን በፍርድ ስብከት ብቻ ሰውን ማትረፍ አንችልም። ጥፋት ሊመጣ እንደሚችል ከጠፉ አብያተ ክርስቲያናት መማር ይገባል። “አልሞትንም ብለን አንዋሽም” እንደተባለው አልተጎዳንም ማለት አንችልም።
ጥንቃቄ
ጥንቃቄ ለኑሮ ወሳኝ ነው። ጥንቃቄ በእግዚአብሔር በጣም ማመን እንጂ አለማመንን አያሳይም። ለራሳችንና ለሰዎች መጠንቀቅ አለብን። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚሠራ ርጉም ይሁን ተብሏልና በጣም መጠንቀቅ አለብን። ከወንጌላዊው ሉቃስ የወንጌሉን በረከት ያገኘነው እነዚህን ሦስት ነገሮች ቢፈጽም ነው።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም