ማቴ. 7፥7
በቤታችን ደስታ አልተሰማን ከሆነ የልባችንን የሚፈጽምልን ሰው አጥተን ነው። በሥራችን ቦታ ደስታ ያልተሰማን የልብ አድርስ የሆነ ሠራተኛ ተቸግረን ነው ። በአገራችን ሥራ ነው የሌለው ወይስ ሠራተኛ ? ብለን መመርመር ያስፈልገናል። ያዘዝነው ባለሙያ ትእዛዙ ላይ ተኝቶ የሚያበሳጨን ጊዜ ጥቂት አይደለም። ልጆቻችን በፍላጎታችን መንገድ አልሄድ እያሉ ልባችንን ይሰብሩታል። አካሌ የምንላቸው ብሽሽቅ ውስጥ ገብተው የማንወደውን ያደርጉታል። የልብን መሻት ፈጽሞ የሚያረካ አንድ አለ፦ የልባችን ልብ ፣ የሕይወታችን ሕይወት፣ የመንገዳችን ብርሃን፣ ቀሪ ገንዘባችን፣ ተዘናግተን የሚያይልን ፣ ተኝተን የሚጠብቀን አንድ ስመ መልካም አለ ። እርሱም የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ነው። ለዚህ ነው ነቢዩ፦ “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” ያለው (መዝ 36፥ 4 ) ።
የልብን የሚያውቅ የልብ አምላክ ፣ የተሰወረውን ምኞት የሚያነብ የነፍስ ወዳጅ እግዚአብሔር ነው። በዚህ ምድር ላይ የምንኖረው መሻቱን ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን የእኛንም መሻት ሊፈጽምልን ነው።
መጽሐፍ፦ “ፈልጉ ታገኙማላችሁ” ይላል። የጠፋብንን ነገር ለመፈለግ ከእንቅልፍ እንነቃለን፣ አልጋውን ገልብጠን እናቆመዋለን፣ ካገኘሁ በኋላ አስተካክለዋለሁ ብለን ቤቱን በአንድ እግሩ እናቆመዋለን፣ ወረቀቶቹን በትነን የዘመናት ሰነድን እናገላብጣለን። ከምንፈልገው ውጭ ሌላ ማግኘት አያስደስተንም፣ ሁሉንም አሁን አታስፈልጉኝም ብለን እንገፋቸዋለን። ልባችን በእልህ፣ እንዴት? በሚል ሙግት፣ የት ሊሄድ ቻለ ? በሚል ቍጣ፣ ማን ገብቶ ነበር? በሚል ጥያቄ የሚፈልገውን ነገር ይበረብራል። ብርሃኑ አነሰብኝ ብሎ ባትሪ ያበራል ፣ ቤተሰቡ አብሮ ይዋትታል። ፈላጊው ቢቆጣም ማንም መልስ አይሰጠውም፣ ቆይ ተረጋጋ ይሉታል። ባገኘው ጊዜ ደስ ይለዋል፣ ልበ ቢስነቱን ይታዘባል፣ ይቅር በለኝ እገሌን ጠረጠርሁ ይላል፣ የተቆጣቸው ቤተሰቦቹ ያራሩታል። ከማግኘት በፊት ብርቱ ፍለጋ ሲኖር ባገኘ ጊዜ ደስታ፣ ንስሐ፣ ከእኔ ጋር ተደሰቱ የሚል ግብዣ ይኖራል።
መፈለግ የሚፈልጉትን ነገር ማወቅን ይጠይቃል። በትክክል የምንፈልገውና የሚያስፈልገን ነገር ምንድነው? እርሱን ካላወቅን ዘመናችን በመባዘን ያልቃል። ያለኝ ይበቃኛል አለማለት፣ ስግብግብነት፣ በመጠን አለመኖር የምንፈልገውን ባለማወቅ የሚመጣ ነው። ይህ ደስታ እያሳጣን፣ እያቅበጠበጠን ፣ ትዳርና ኅብረታችንን እንድናፈርስ ያደርጋል። የሚፈልጉትን ለማግኘት የሚፈልጉትን ማወቅ ተገቢ ነው። ሁለተኛው አስፈላጊ ቢሆኑም ሌሎች ግኝቶችን መተው ይገባል። የምንፈልገውን የማንፈልገው ነገር እንዳያስረሳን መጠንቀቅ ግድ ይላል። ብዙ ሰው መንገድ ላይ የቀረው በዚህ ምክንያት ነው። ለምንኩስና ወጥቶ ሥልጣን ላይ ፣ ለትምህርት ወጥቶ ቁማር ላይ የቀረው በተላላነቱ፣ ያየውን ብቻ ለመከተል አለመፍቀዱ ነው። ሦስተኛው ያለው ብርሃን በቂ ስለማይሆን ተጨማሪ ብርሃን፣ የቃሉን ፓውዛ ማብራት ይገባል። ብሩህ አእምሮ ብቻውን በቂ አይደለም፣ መንፈሳዊ ምሪት ያስፈልጋል። አራተኛ የቅርብ ቤተሰቦችን አፋልጉኝ ብለን መጥራት ፣ ምክር መጠየቅ ይገባል። አተርፍ ባይ አጉዳይ የሆነ፣ ሁሉን እይዛለሁ ብሎ ሁሉን ያጣ ፣ ምክር አያስፈልገኝም ብሎ ገደል የገባ ብዙ ነው።
“ፈልጉ ታገኙማላችሁ” ማለት ተኝታችሁ ተመኙ የተባለ መስሎት ብዙ ሰው ስቷል። መፈለግ መነሣት፣ ማሰስ፣ መድከም፣ ለዚያ ነገር ትኩረት መስጠት፣ ለምን እና እንዴት ብሎ መጠየቅ ፣ አግዙኝ ብሎ መጥራት ያለበት ነው። ለሚፈልግ ሰው ነገሮች ቅርብ ናቸው። ፈልጉ ታገኛላችሁ የሰውን ንብረት መመኘት፣ ወላጅ ሳይሞት ሞቶ በወረስሁ የሚል ጭካኔ አይደለም። መፈለግ የራስን አእምሮና ጉልበት መጠቀም ፣ የሌላውን ልፋት አለመከጀል ነው ። መፈለግ እግዚአብሔርን ይዞ ጉዞ ማድረግ ፣ አምላኬ ሰጪዬ ነው ብሎ ማመን መታመን ነው።
ብዙ ቅዱሳን አባቶች እግዚአብሔርን ለማገልገል ፈለጉ፣ ከወላጅ ቤት ርቀው ለትምህርት መነኑ ። የሚፈልጉት ጋ ለመድረስ ዋጋ መክፈልን አልፈሩም። ልጆቻቸውን አገልጋይ ለማድረግ ፈለጉ፣ ገና በጠዋቱ ወደ ቤተ እግዚአብሔር አመጡ ። ምክረ ሥላሴን ለትውልድ ለማቆየት ፈለጉ ፣ ጀርባቸውን አጉብጠው መጻሕፍትን ጻፉ። ከአራት ሺህ እስከ ስምንት ሺህ መጻሕፍትን በግለሰብ ደረጃ የጻፉ አባቶች አሉ።
የምንፈልገው ምንድነው ? መፈለግ አሁን መነሣት ይፈልጋል። ቀጠሮ የሚያበዛ ሰው የተመኘውን አያገኝም ። መፈለግ እንቅስቃሴ ነው ። ቤቱ ሊተራመስ ይችላል። ፍላጎታችን አንዳንዴ ቤተሰባችንን ሳይቀር ሊያሳጣን ይታገለናል። የተመኙልንና የምንፈልገው ሲጣላ ሙግት ውስጥ እንገባለን። መፈለግ አሁን የማያስፈልጉንን ነገሮች ወደ ጎን እንድናደርግ ያስገድደናል። መፈለግ ቁልፍ ለመስበር፣ በር ለመክፈት ሊያበቃን ይችላል። መፈለግና መከጀል ትልቅ ልዩነት አለው። ዛሬ የሚከጅል ትውልድ ፣ ከመኝታው የማይነሣ ፣ የማይጠቅመውን ነገር ሲያገላብጥ የሚውል ወገን እያፈራን ነው ። “ፈልጉ ታገኙማላችሁ” እንዲህ ያለውን አይመለከትም። ሰባኪ ለመሆን የሚፈልግ ማንበብ፣ የሰባኪዎችን ትምህርት ቀን ከሌሊት መስማት፣ መለማመድ ፣ ሰው ቢያጣ ዛፎችን እንደ ሰው ቆጥሮ ማስተማር ፣ የመምህራን እጅ አስታጣቢ መሆን ይገባዋል። መፈለግ ያለ መሠዋዕትነት አይሆንም።
የሚፈልግ ያገኛል! እንኳን እግዚአብሔር ስንቱ ሊቅ እውቀትን ሊያወርስ የሚፈልግ ሰው እያሰሰ ነው። ባለጠጎች ራእይ ያለው ሰው፣ እውነተኛ ወገን ይፈልጋሉ። እግዚአብሔርም ጸጋውን ለመልቀቅ የሚፈልግ ሰው እያማተረ ነው። በመፈለግ በልጽጉ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም.