ጌታችን ለምእመናን ከሰጣቸው ስያሜዎች አንዱ “ጨው ናችሁ” የሚል ነው። ጨው በጥንታውያን ሰዎች አነጋገር “ነጩ ወርቅ” በመባል ይጠራል። ብዙዎች ጨው ነግደው ባለጠጋ ይሆናሉና። ጨው ለምግብ ማጣፈጫነት ይውላል። ጨው ለምግብነት የሚውለው ራሱን ሲያሟሟ ነው። ክርስቲያንም በምድር ላይ የጣዕም ተጽእኖ የሚያመጣ ነው። ሕይወት አልጫ አልጫ ያለችባቸው፣ ለመኖር አቅም፣ ለመራመድ ፍላጎት ያጡትን ጨው ሆነን ልናበረታታቸው ፣ ባላዩት ጎን የሕይወትን መልክ ልናሳያቸው ይገባል። ምን ያህል ጠቃሚ ሰዎች እንደሆኑ ልንነግራቸው ይገባል። መኖራቸው አስፈላጊ መሆኑን አስረግጠን ልናሳምናቸው ተገቢ ነው።
በርበሬው የራሱ ጣዕም ቢኖረውም እንዲያወጣው የሚያደርገው ጨው ነው፤ ሁሉም ሰው የራሱ እውቀትና መልካምነት አለው። ካልነገርነው ላያውቀው ይችላል። ጨው ሆነን ልናጣፍጠው፣ የያዘውን ጣዕም እንዲያወጣው ልናግዘው ይገባል። ምድር ያለ ክርስቲያኖች አልጫ ናት። ክርስቲያኖች ባይኖሩ በዓለም ላይ ብዙ መልካም ነገሮች አይኖሩም ነበር። በተለያዩ አገራት የምንጎበኛቸው ጥንታዊ ቅርሶችና መቅደሶች የክርስቲያኖች ናቸው። ኢየሩሳሌም፣ ሮም፣ ግሪክ ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ራሽያ ብንጓዝ የሚጎበኘው የክርስቲያኖች የዘመን አሻራ ነው። በአገራችን ጎብኚዎች የሚጎበኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ነው ። ቤተ ክርስቲያን እየተጠላች እንኳ የአገር እንጀራ ናት ። ዛሬ የሚታየው የቴክኖሎጂ ግኝት እንዲሁም ታላላቅ የእርዳታ ተቋማት የክርስቲያኖች ሀብት ናቸው። የዓለማችን ኃያላን አገራት የሚባሉት ክርስቲያን ናቸው። የኃያልነታቸውን ምሥጢር እየዘነጉ ቢመጡም ይህ ሁሉ የሥልጣኔ ከፍታ የክርስቶስ ብርሃን ያመጣው ነው።
ምድር ያለ አማንያን አልጫ ናት። አልጫ ጣዕም የለውም። ይህች ዓለምም ሰው ሠራሽ በሆነ ደስታ የተሞላች ናት። ሰው ሠራሽ ደስታ ለዛሬ ነገን የሚከፍል፣ ዘላለምን የሚያከስር ነው። ብዙ ባለጠጎች በሚያሳዝን የነፍስ ስቃይ ውስጥ ያልፋሉ። በሰው የተከበቡ ነገር ግን በብቸኝነት ስቃይ የሚያለቅሱ ዝነኞች አያሌ ናቸው። መኖርን ገና ያልጀመሩ ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ ላይ ናቸው። ዘመናዊነት ብልጠትን ሲያስተምር ደስታን ግን የሚነጥቅ ነው። በብልጠት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ፣ ደስታን አጥተው ግን ሕይወትን ላጥፋት ላብራት እያሉ ትግል ውስጥ የገቡ ብዙዎች ናቸው። ለዛሬው ትውልድ የምንመክረው ብልጥ ሳይሆን የዋህ ሁኑ ብለን ነው። አሊያ ዕድሜ ላይረዝም ይችላል።
እያላቸው ድሀ የሆኑትን ባለጠጋ የሚያደርግ ያ ክርስቲያን ነጭ ወርቅ ነው ። ሁሉም ነገር ትርጉም አጥቶባቸው ጥለው ለመሄድ እየታገሉ ያሉትን “ቆይ ገና ነው” ብሎ ጉልበት የሚያበድር ያ አማኝ ነው። ጨው ከቤተ መንግሥት እስከ ድሀ ቤት የሚገኝ ነው። አገልጋይም ለሁሉም ወገን አስፈላጊ ነው። ጨው ጣዕም የሚሰጠው ሲሟሟ ነው፣ አገልጋይም እኔነቱን ሲጥል የብዙዎችን ሕይወት ያጣፍጣል።
ጨው አስፈላጊ ቢሆንም እርካሽ ነው። አገልጋይም በብዙ ንቀት ውስጥ የሚያልፍ ነው። ሥጋዊ ሐኪሙን የሚያከብር ፣ በሚሊየን ለባለሙያ የሚከፍል፣ መንፈሳዊ ዶክተሩን አገልጋዩን ይንቃል። ንስሐውን የደበቀለትን ወዳጁን ያዋርዳል ። የሚገርመው በአገልጋይ የሚጨክን ሌላው አገልጋይ መሆኑ ነው። አገልጋይ በሚያገለግለው ሕዝብ ሳይቀር የተጠላ ነው። የመስቀል ጉዞ መድማት ያለበት ነውና አንተ ዋጋህን በማያውቁ መካከል የምትኖር አገልጋይ ሆይ በርታ! ዘመኑ እያለቀ ነውና ለዚህ እንጥፍጣፊ ጊዜ ከማማህ ላይ እንዳትወርድ በክርስቶስ አምልሃለሁ! ምእመኑስ የውሸትም አይዞህ የሚለው አለው፣ አንተ አገልጋዩ ሺህዎች የከበቡህ ብቸኛው ፣ ጌታ ክርስቶስ አለህ ! የማዋይህ ብለህ ጌታህን ጥራው!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ.ም