ክፉና አስጨናቂ ዘመን ነበር፣ ከላይ ስክበው ከሥር ይናዳል ፣ በሮች ሁሉ ክፍት ሆነው እኔ ስደርስ ይዘጋል … ጌታዬ ሆይ ይህን ንግግር አልጨርሰውም ፤ አንተ ለእኔ መልካም ነህ ፣ ጎደለ ለማለትም ዘመን መጨመር አለበት ። ደግሞም የሰው ጠባይ የማይጨበጥ ሆነ፣ ቁምነገር የሌለው ትውልድ እንደ ምርት ተትረፈረፈ … ጌታዬ ሆይ ይህን ቃል አልጨርሰውም፤ በህልውናህ መታጣት፣ በጠባይህ ወረት የሌለብህ አንተ ከእኔ ጋር ነህ። ደግሞም ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ እንጂ ሁልጊዜ በሰው ደስ ይበላችሁ አልተባለም። ከዚህ ኑሮ የሞተ ይሻላል፣ የሚለቀሰው ለእኛ ነው …ጌታ ሆይ ይህን ንግግር አልጨርሰውም ፣ የሙታንም የሕያዋንም ጌታ አንተ ነህ ፤ የገነት መዓዛም አንተ ነህ ፣ ገነት ያላንተ ሲኦል ናት :: መኖር ያንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም፣ እኔን በምድር በማስቀመጥህ አልተሳሳትህም ፣ አኑረህ አሠራኝ እንጂ ውሰደኝ አይባልም። ሞት ባይለምኑትም አይቀርምና ለሚበልጠው ጸጋ እንትጋ። ተቆርቋሪ ወገን ፣ ደራሽ ዘመድ የለኝም፣ እንደ ምልምል ዛፍ ብቻዬን ቆሜአለሁ… ጌታ ሆይ ይህን ንግግር አልጨርሰውም። ዘመድ ቢበጅ አቤልና አምኖን በገዛ ወንድሞቻቸው በቃየንና በአቤሴሎም እጅ አይሞቱም ነበር። አንተን የሰቀሉህ የገዛ ወገኖችህ ፣ የእናትህ ዘመዶች ናቸው። ዘመድ አንተ ብቻ ነህ! ዘመድ እኔ ብቻዬን ላቁስለው ብሎ ሌላ ሲነካ የሚጣላ ነው።
ብልጥ መሆን ጥሩ ነው፣ ብዙ ትርፍ ያስገኛል፤ ብዋሽ ምናለበት ይህቺን ታህል ሳልበድል እውላለሁ ወይ? ያለ መሰላል መውጣት አይቻልም፣ እገሌን መጠቀሚያ ባደርገውስ … ጌታ ሆይ ይህን ንግግር አልጨርሰውም፣ ከአፌ ወጥቶ ሳያልቅ ቀፈፈኝ ፤ ጤና በብልጠት ፣ ሕይወት በገንዘብ አይገኝም ፤ ባለጠጋ ዘመዱ ይመካበታል፣ እርሱ ግን እየተደበቀ ይኖራል ። የበረከት ምንጭ አንተ ነህ ፣ ለራሴ ከቆረስኩት አንተ ያስብህልኝ በለጠ።
ዕድሌ ጥሩ አይደለም፣ ሙሉ ዕጣ ቢሆን ለእኔ አይወጣልኝም፤ ግንባሬ ክፉ ነው፣ አይሳካልኝም ፤ የሞተ ውሻ ለእኔ ሲሆን ይነሣል ፣ ሰው አይወጣልኝም፣ አገሩ ለእኔ አይሆንም … ጌታ ሆይ ራሴን በቃሌ አላስረውም፣ ይህን ንግግር አልጨርሰውም። የዳዊት ዕድል ፈንታ አንተ አይደለህም ወይ? ከእረኝነት ወደ ንጉሥነት የሚያወጣ ያንተ ዕድል ፈንታ ከሁሉ ይበልጣል። ገመድ ባማረ ስፍራ ትወድቅልኛለች፣ ዕጣዬንም አንተ ታወጣለህ ።
አጥሬ ተደፍሯል፣ ጠላት ያሻውን ያደርግብኛል፣ ከፍታዬ ዝቅ ብሏል የናቅሁት ይረግጠኛል …ጌታ ሆይ ይህን ንግግር አልጨርሰውም ፤ ከጠላት ውጊያ በላይ የእኔ መኖር ይገርማል። በተኩላዎች መካከል እንደ በግ ማሰማራት ክንድህ ይችላል። እስከ ዛሬ ያለሁት በድንቅ ምሕረትህ ፣ በማይዘናጋ ጥበቃህ ነው። ያለ ልብስ ባለ ሞገስ፣ ያለ አጥር ባለ ግርማ ታደርጋለህና ተመስገን :: ደግሞም የሚመጣው ዓመት ምን ይመስል ይሆን? ያው ነው ፣ ቀኑም ቀን ነው ፣ አገሬም አትለወጥም… ጌታ ሆይ ይህን ግግግር አልጨረሰውም:: መኖር ሹመት ነው፣ ንጉሥ እየሞተ ድሀ ይኖራልና። ከአንተ አዲስነት የተነሣ ዛሬ አዲስ ነው። በሥራ ላይ ነህና ዓመቱ ድንቅ ፣ ነገ የተሻለ ነው። ነገ የተሻለ ባልበላ ስለ ሕይወት የተሻለ እውቀት ይኖረኛል።
ጌታ ሆይ ጨርሶ መብላት እንጂ ጨርሶ መናገር መልካም አይደለም። ቃሌን ይቅር በለው፣ በቃልህ መንገዴን አቅናው። በምድራዊና በሰማያዊ በረከትህ የምባረክበት ዓመት ይሁን። ካንተ ጋር ተራራ ቢሆን ሸለቆ ጉዞው መልካም ነው ። አሜን !
ቡሩክ ዓመት ይሁንላችሁ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም.