እግዚአብሔር በድንቅ አሠራሩ ካሰኝ፣ በማትመሽ ቀኑ ደረሰልኝ ለማለት አብቃኝ። እኔም እንደ ሰዉ ተራው ይድረሰኝ ። ለስእለቴ አብቃኝ! አምላክህ የት ነው? ያሉኝ የስጦታህን ተአምር በእኔ ይመልከቱ ፣ አምላኬ ትቶኛል ያለው ልቤ “እግዚአብሔር ለካ ለዘላለም አይጥልም” ብሎ ይዘምርልህ። የበዪ ተመልካች እንዳልሆን፣ እንዴት ሆነ ያንተ ጉዳይ? የሚሉኝ ቍስሌን እንዳይቀሰቅሱብኝ፣ አልነጋም ወይ? የሚለኝ ልጄ ብርሃን እንዲያይልኝ እባክህ ለስእለቴ አብቃኝ። ለትዳሬ ሁሉን አለመንገሬ፣ የችግሩን ጥልቀት ቢያውቁ ይሰበራሉ ብዬ ነው ፣ ለትከሻቸው አስቤ ዝም ስል ድብቅ ይሉኛል። እንዲበሉ ብዬ በልቻለሁ ስል ሌላ ቤት ይዟል ብለው ይጠረጥሩኛል። የልብ አውቃ አንተ ብቻ ነህ።
ለስእለቴ አብቃኝና እኔም ለአምላኬና ለሰው የገባሁትን ቃል ለመፈጸም አብቃኝ። ከራሴ ጋር ያለኝ ክርክር ማብቂያ ሲያጣ፣ ትግሉም ገላጋይ የለሽ ሲሆን፣ ጥርስ እየሳቀ ልብ ሲያር አቤቱ ለስእለትህ አብቃኝ። የምትሠራበት ቀን፣ ለእኔ የምትፈርድበት ሰዓት ቢርቅብኝ ሰው ነኝና ተረዳኝ። ሥጋ ነከስኩ ብዬ ቀንድ ስነክስ ጥርሴን እሰብራለሁ። ዓሣ ለመንኩ ብዬ እባብ አዘንባለሁ። ዳቦ ጠየቅሁ ብዬ ድንጋይ እይዛለሁ። አቤቱ ፍለጋ ያደከመኝን እባክህ ለስእለትህ አብቃኝ።
ቀኑ መሸ ብዬ ተስፋ እንዳልቆርጥ በገባዖን ለኢያሱ ፀሐይ ማቆምህን ልቤ ይወቅ። ለመሻገር ባሕሩ ጥልቅ ነው ብዬ ስፈራ ቀይ ባሕርን የከፈለ ያንተ ሥራ ከእኔ ጋር ይሁን። ደርሰው የማያኩት የቋንጃ እከክ ሲሆንብኝ፣ ነገሩ ሁሉ ድፍን ቅል ሆኖ ሲያስጨንቀኝ ፣ የሰው ልብ የመንፈቅ መንገድ ያህል ቢጓዙ አልታወቅ ሲል ፣ የተዘጋው ከተማ ሲያውከኝ ኢያሪኮን ያፈራረሰው ያ ክንድ ዛሬም አለሁ ይበለኝ።
ላታመልጠኝ አታሯሩጠኝ እያለ ሲያሳድደኝ ጠላቴ፣ ላልመለስ ወደ ኋላ ጉዞዬ ይሁን ካንተ ጋራ። አቤቱ ለስእለትህ አብቃኝ አዲስ ነገር መናፈቅ ደከመኝ፣ ተስፋ የሚሰጡኝ እየሸነገሉኝ ሆኖ ተሰማኝ። ሁሉን ተለማማጭ ሆኜ የምታኖረኝን እንዳልረሳ፣ የሰው ፊት በራ ጠቆረ ብዬ ከፍ ዝቅ እንዳልል አቤቱ ለስእለቴ አብቃኝ። ለልመና ከመጣሁበት ደጅህ ለምስጋና መልሰኝ።
ይህ የመጨረሻዬ ነው ብዬ ብዙ ለምኜሃለሁ ፣ ሰጥተህ የማትሰለች መሆንህን ረስቻለሁ። ካንተ እጅ ሲቀበሉት አያሳቅቅም። በልኬ ሳይሆን በልክህ ትሰፍርልኛለህ። ከእኔ እንጂ ካንተ አይጎድልም። ማጣት ጨዋ ቢያደርገኝ፣ ማግኘት ያባልገኛል። ጌታዬ ሆይ ያለ እጅህ በረከት እንዴት እኖራለሁ? ካንተ ደጅ በቀር የማንኳኳው ሌላ በር የለም። ናፍቄአለሁ ለስእለትህ አብቃኝ።
እኔንም ወገኔንም ከነሽክማችን እንዳንሻገር ፣ ወልድ ሆይ መስቀል በመሸከምህ የነጻነት ዓመት ስጠን። የሞቱት በኃጢአታቸው ፣ የቆምሁት በጽድቄ አይደለም። ዕድሜዬን ለበጎ ሥራ እንዳውለው አንተ እርዳኝ። ከዘመኑ በፊት እኔ ልለወጥ። ለስእለቴ አብቃኝ ስከተለው የሸሸኝ ዕድል ፈልጎኝ ይምጣ። በሚራራው ልብህ አሜን!
#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
ጳጕሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም.