በስንቱ የሙት ልጅ ላይ ጨለማ ላወጀ ታነጋለህ። ነግቷል ፣ ደግሞ እንበድልህ። ዕድልህ ይገርመኛል ወርቅ ሰጥተህ ጠጠር እንመልስልሃለን። ሲያጣ የወደደህ ሲያገኝ ይጠላሃል፣ ውለታህን ባይመልስ ተመስገን ቢልህ ምናለ! ኧረ ተመስገን ይቅር ጀርባውን ባይሰጥህ መልካም ነበረ። ደኅናውን ብታጣ የተሻለውን ክፉ እየመረጥህ ይሆን? የታመመ በሽተኛን በጦር ጀት ለሚደበድብ ታነጋለታለህ፣ በስንቱ ቤት ላይ ሲያጨልም አንተ ግን በቸርነትህ እንግተህለት ነበር። ሰው ማደሩን ሳያረጋግጥ ነግቶ ለማፍረስ ያቅዳል፣ ደግሞ ታነጋለህ፣ ደግመን እንበድልሃለን።
ቋጠሮው የሚፈታ አይመስለንም ነበር፣ ጸሎቴ ከሰመረ እመንናለሁ ብለን ተስለን ነበር። ችግሩን ባሳለፍከው ቀን ድንግሉ ዘማ፣ ባሕታዊው ሽፍታ፣ መጽዋቹ ቀማኛ ይሆናል:: ደግሞ እንበድልህ፣ አንተም መስጠትህን ፣ እኛም ቀምተን መሮጣችንን አንተውም። ልባችን እያወቀው፣ ውስጣችን እየነገረን በጸጋ የተቀበልነውን በልፋታችን አገኘን እንላለን፤ በራሳቸው የሚያፍሩትን የበለጠ ተስፋ እናስቆርጣለን። ጠግበን ሳይሆን ገና ልንጠግብ ስንል የኃጢአት ቤቶች ይታዩናል፣ በችግራችን ከሸሹን ጋር መጨፈር ያምረናል። ደግሞ እንበድልሃለን፣ እባክህ ቶሎ ስጠን፣ የጸሎት መልሳችንን ለክፋት፣ ከእጅህ የተቀበልነውን የእጅህን ሥራ ለማፍረስ እናውለዋለን።
ሁሉ በተፋን ፣ ዓለም ባገለለን ዘመን፣ እንደ ጉድፍ የት ይጣሉ በተባልን ወራት ተጨንቀን ነበረ፣ የእኛን ተወውና ስለ አባቶቻችን ብለህ ይቅር በለን እያልንህ ነበር። ስናርፍ ሌላውን ለመበጥበጥ፣ ስንተርፍ ሌላውን ገደል ለመጣል አቆብቁበናል። ደግሞ እንበድልህ፣ ምክንያቱም ተነሥተናል። የእኛን ታሪክ በሌሎች ላይ ለመድገም ጊዜ አግኝተናል። በአባቱ በሽታ ቁጭት ሕክምና ያጠና ፣ በአባቱ መጠን ያሉትን ያንገላታል። ተቆጭቶ ሕግ ያጠና፣ ፍርድን በገንዘብ ይሸጣል። ሌሎች ተበደሉ ብሎ የታገለ ሥልጣን ሲይዝ ወደ ግዞት ይልካል። መጠጊያ አጥቶ የተሰደደ ባለ አገር ሲሆን ድሀ ያፈናቅላል። ያስጠጉትን መጠጊያ ያሳጣል፤ የተደረገለትን ዞሮ ለማየት አንገት ያጣል። ደግሞ እንበድልህ፣ አንተን የሚበድልህ የገዛ እጅህ ነው። እጅህ ጠላት የሚያተርፍብህ፣ ልጅህ አዳም ከጠላት ጋር የሚመክርብህ፣ ዕድልህ ምንድነው?
አሁንማ ከበሽታ ድነናል፤ ሌላውን ለማሳመም ወጥተናል። አሁንማ ድህነት አልፎልናል፤ ድሀ ብለን ለመሳደብ ቸኩለናል። ባዶ እግሩን የሚሄድ ሕዝብ ባለ ሰረገላ አድርጎን መልሰን ንቀነዋል። የወጣንበትን መሰላል ገፍትረን ጥለናል። የእኛ ነገር ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ ሆኗል። ብዙ ረድተኸን ሌሎችን ጥቂት መርዳት አንፈልግም። በጸጋህ እየኖርን ሌሎችን በሕግ ይዳኙ እንላለን። ያ ሁሉ የሕሊና ወቀሳ ዛሬ የለም፣ ምሕረትህ አቁሞናል። ከዝሙት ተላቀን በፍርድ ኃጢአት ተይዘናል። አንገት ደፍተን እንዳልኖርን ሌላውን ለማሸማቀቅ ቀጠሮ ይዘናል። የእኛ ተደብቆልን፣ ሌላውን ለማራቆት ቸኩለናል።
ደግሞ እንበድልህ የአሁኑ ጥጋብ የዘላለም መስሎናል፣ ለመጨረሻ ጊዜ የጠጣን ሆኖ ተሰምቶናል። የለበስነውን የማያልቅ አድርገነዋል። ረሀብና ጥጋብ በፈረቃ እንደሚመላለሱ ረስተናል። ነገ ከመሬት በታች እንደምንውል ረስተን መሬቴ እያልን መናገር ደፍረናል። ችግሩ በርግጥ ተሰናብቶን ሳይሄድ ሎተሪ ቆረጥኩ ብለን በጥጋብ አብደናል። ውለታህ ዝቅ ሊያደርገን ሲገባ ሰይፍ እንድንመዝ አድርጎናል።
ደግሞ እንበድልህ፣ ምክንያቱም ከሰው ቊጥር ደምረኸናል። ከጫካ ሕይወት አውጥተኸናል ። ያስጨነቁንን ቀኖች ወስደሃል። በፍርሃታችን ላይ የበላይ አድርገኸናል። ቋሚ ነው የተባለው በሽታችን ጊዜያዊ ነው ተብሏል። እኮ ከዚህ በኋላ ምን አለብን? የምድሩ እንጂ የሰማዩ አሳስቦን አያውቅም። ረሀብን ችለን ጥጋብን መታገሥ አቃተን። በችግር መንነን፣ በምግብ ወደ ዓለም ወጣን። ዘመድ አልረዳኝም ብለን የድሀ ንብረት ለመንጠቅ ተሰማራን ። ካልሰጠኸን ጨዋ ነን፣ ከሰጠኸን አሁንም እንበድልሃለን። አንተም እየበሉ ይካዱኝ ብለሀ አዝነህ ሰጠኸን። እኛም ጎበዝ ነን፣ ደግሞ እንበድልሃለን።
የአብርሃም አምላክ አቤቱ ለውጠን!
ነሐሴ 20 ቀን 2017 ዓ.ም.