በርትታ ካላማጠች የእርስዋም ሆነ የልጅና ሕይወት አደጋ ላይ ነው። ዘጠኝ ወር ሙሉ ስትቸገር የከረመች ሴት በመጨረሻ ምጥ ይገጥማታል። አልቃሽ:— “ታሞ ታሞ ፣ ሞት አለ ወይ ደሞ ?” እንዳለችው መግለጽ በማይቻል ስሜት ውስጥ ያለፈችው እርጉዝ አሁን ደግሞ ምጥ ይገጥማታል። ምጡ በትንሹ እየጀመረ ይፋፋማል። ሙሉ አቅሟን ሳትሰስት ታወጣለች። ልጁ ሲወለድ በደጅ ያለው ያዜማል፤ አባት ጥይት ይተኩሳል። ዘመድ አዝማድ እልል ይላል። የልጁ ድምፅ በንግግር፣ በሳቅ ሳይሆን በልቅሶ ይገለጣ። አራስዋ ግን ፍጹም ድካም ይሰማታል። እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሊድ ፈቃድ አዘጋጅቶ ነበር፤ ወንድ ልጅ ከወለደች አርባ ቀን፣ ሴት ከወለደች ሰማንያ ቀን ከቤትዋ አትወጣም፣ ማኅበራዊ ግዳጅም የለባትም። ይህ የወሊድ ፈቃድ የተሰጣት ለድካምዋ ካሣ እንዲሆን ነው።
ታዲያ ቀረብ ቀረብ የሚሏት ከዚህ በፊት መውለድን የሚያውቁ እናቶች ናቸው። የምጥን ነገር ያማጠ ያውቀዋል። ከአጠገብዋ ፍጹም አይለዩም። ሴት ልጅ ከወለደች በኋላ የሚገጥማት ጭንቀት፣ የመጣልና የብቸኝነት ስሜት አለ። ያንን የተረዱ እናቶች አይለዩአትም። መታጠቢያ ቤት እንኳ ብቻዋን አትሄድም። በዓለም ላይ ብዙ አራሶች ራሳቸው ላይ አደጋ ያደርሳሉ። ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ስለሚያልፉ ዘመናዊው ዓለም አራሶችን አትለዩ እያለ ነው። የልብ ብርሃን የተሰጣቸው የአገራችን እናቶች ግን ይህን ቀድመው አውቀውታል።
ከምጥ በኋላ ትልቅ ድካም ይገጥማል።ኑሮም ምጥ ነው። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ ጠባያችንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል፣ የቤታችንን ጉድለት ለመሙላት ባለን ሩጫ በምጥ ውስጥ እናልፋለን። ይህ ዘመን ወንዱም ሴቱም ፣ ባለጠጋም ድሀም እኩል የሚያምጡበት ዘመን ነው። ሴቶች ወንዱን “በርታ እንጂ” እያሉ የሚያረጋጉበት፣ ባለጠጎች ከድሆች ምክር የሚፈልጉበት ዘመን ነው። ሰው ስለ ራሱና ስለ ቤቱ ያለውን ውስጣዊ ምጥ ማንም አያውቅለትም። አምጣ ባይ አይቸግረውም፣ አምጣ የሚባለው ግን በውስጡ ቁና ይተነፍሳል። አሥራ ሁለት ልጅ እያለ አሥራ አንዱና አባት እናት አንዱን ልጅ አምጣ እያሉ ያጠቁታል። አሥራ አንዱ ባለማፈር ለሁላችን ያለው እርሱ ነው እያሉ ይፖተልካሉ። እርሱም ያለሁት እኔ ነኝ እያለ ይባክናል። ዕድሜው ያጠረ ቀን ለራስህ አላውቅበት ብለህ ነው እያሉ ያለቅሱለታል። የደግነቱ መጨረሻ የወቀሳ ልቅሶ ይሆናል። ዕረፍ እስቲ አሁን እኛ አለን ያላሉ፣ በአሳብ ያልደገፉ፣ ሁሉን ለእኔ ሲሉ የኖሩ አሁን በዜማ ያለቅሳሉ።
በዚህ በምጥ ዓለም ላይ አልጋ ገዝተዉ እንቅልፍ ያጡ፣ ቤት ሠርተው ሰላም ያጡ፣ የገዛ ወገኖቻቸው ያለ ርኅራኄ የሚያቆስሉአቸው ብዙ ምስኪኖች አሉ። በርግጥ ሰዎች የሚያውኩን እንዲያውኩን በፈቀድንላቸው መጠን ነው። ለሰላማችን አጥር ያላበጀነው እኛው ነን። ክፉዎች በመያዣ ያሰቃዩናል። አባት እናት መያዣ ተደርገው የሚንገላቱ ብዙዎች ናቸው። “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” በሚል ደግነት የተተው አያሌ ናቸው።
ዓለም ሙሉ አይደለም። ታዲያ ልመናችን መልስ ሲያገኝ ለዓመታት ጸልየን ሳለ ለአንድ ቀን ማመስገን ያቅተናል። ለአንድ ቀንም እንኳ ቃል አውጥተን ከማመስገን ዝምታና መደመም ይገዛናል። አንተ ይህ ሁሉ ተደርጎልህ ዝም ትላለህ ወይ? ብሎ ውስጣችን ሲጠይቀን መልስ እናጣለን። እንደውም ድካም ይሰማናል፣ ማረፍ ያምረናል። ይህን ካየሁ ይበቃኛል የሚል እርካታም ይመጣል። ከምጥ በኋላ ድካም እንዳለ የታወቀ ነው።
የምጥ ዓለምን ስንፈጽም ለሰማዩ ዓለም እንወለዳለን።
እግዚአብሔር በተንገላታችሁበት ነገር ዛሬ ዕረፍት ይስጣችሁ!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም.