አንተ ብቻ ራስህን የገለጥህ ውብ አምላክ ነህ ፣ የሰው ልጅ ግን መደበቂያ ቅጠል፣ ዋሻና ምክንያት ሲፈልግ የሚኖር ነው። አንተ ብቻ የዋህ ነህ፣ አውቀህ ትምረናለህ ፣ ዓይተህ እንዳላየ ታልፈናለህ፤ የሰው ልጅ ግን ሊሆን ይችላል ብሎ ያማል፣ ገምቶ ይገድላል፣ ጠላቴን አገኘሁ ብሎ ወዳጁን ያጠፋል፣ ለእንጀራ ልጁ የበጠበጠውን መርዝ ልጁ ይጠጣበታል። አንተ ብቻ ገር ነህ ፤ የሰው ልጅ ግን ብልጥ፣ የብልጠት ዳርቻ ፣ እንዴት ልስጥ ሳይሆን እንዴት ልቀበል ? ብሎ የሚያሰላ ነው።
አንተ ብቻ ደጃፍህ የተከፈተ ነው፤ እናትም ሞታ በሯ ይዘጋል፣ የአባትም ኮቴ እየራቀ ይመጣል፣ ወዳጅም ሰልችቶ የለሁም ይላል፤ የሰው ልጅ ልቡን በልቡ ሸሸጎ በጥርሱ ያጫውታል። አንተ ብቻ ደግ ነህ፣ የረሀብ መድኃኒት ፣ የሐሩሩ ጥላ ነህ፤ የሰው ልጅ ግን እንደ አራዊት ቀምቶ አዳሪ ፣ “አትግደለኝ ወንድሜ” እያለው ወንድሙን የሚጨርስ፣ የወደደውን የሚጠላ፣ የጠላውን የሚያጠፋ ነው።
አንተ ብቻ የልብ አዋቂ ነህ ፣ ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን አውቀህ የምትረዳ ነህ ፤ የሰው ልጅ ግን በተለመነ ቁጥር የሚጨክን ፣ መረዳትም መርዳትም ፣ መገንዘብም መስጠትም የማይሆንለት ነው። አንተ ብቻ ነዋሪ ነህ፤ የሰው ልጅ ግን ስሜቱን አገልጋይ ፣ በእውነት ላይ የሚያረፍድ፣ የወደደውን የሚጠላ፣ ቃሉን አጥፎ የገዛ ልቡን የሚከዳነው። አንተ ብቻ መሠረት አለህ፤ የሰው ልጅ ግን ሲፈርስ ሲሠራ የሚኖር፣ ተናውጦ ማናወጥ፣ ስቶ ማሳት የሚወድ ነው። አንተ ብቻ አዋቂ ነህ፣ ያወቅኸውን ሁሉ አትናገርም፤ የሰው ልጅ ግን ራሱ ተፈራጅ ሳለ ይፈርዳል ፣ ተኰናኙ ኰናኝ ነው፣ በማያውቃቸውና በፍርድ ቀን በማይከሰስባቸው ሰዎች አስተያየት ሲሰጥ የሚኖር ነው።
አንተ ብቻ እጀ ሰፊ ነህ ፤ የሰው ልጅ በሌለው ዘመን የመስጠት ምኞት አለው፣ ያገኘ ቀን የስስት ፆር ይዋጋዋል። አንተ ብቻ ያገለገሉህን አትረሳም፤ የሰው ልጅ ግን የሚስቱን እናት እማዬ እያለ እናቱን ይክዳል፣ እንደ ድመት የበላበት ይቀራል።
አንተ ብቻ ቃልህን አክባሪ ነህ፤ የሰው ልጅ ግን ቀኑ ሳይመጣ የተናገረውን ቀኑ ላይ ያጥፋል ፣ ያቀደውን ትቶ ግርግርን ያገለግላል። አንተ ብቻ ለሁሉ ታስባለህ፤ የሰው ልጅ ግን ያሳደገውን ትቶ የካደውንና የጣለውን ወላጅ ይፈልጋል፣ ባለውለታውን ረስቶ ያገሬ ልጅ የሚለውን ሲያገኝ ጥሎ ይሄዳል ። አንተ ብቻ ከኋላ ቀርተህ ትሰበስባለህ፤ የሰው ልጅ ግን ታዛቢ ከሌለ የወዳጁ ቀብር ላይ አይገኝም፣ የጓደኛው ልጆች ሲርባቸው ጓደኛውን አስቦ አይደርስም። አንተ ብቻ ትፈውሳለህ፤ የሰው ልጅ ግን ፈውስን በጨረታ ይሸጣል ፣ አንዱን ጠግኖ ደኅናውን አካል ይሰብራል።
አንተ ብቻ ትገኛለህ፤ የሰው ልጅ ግን አብሮ ውሎ ሲመሽ እንደ ጥላ ይሰወራል፣ ጭር ሲል አልወድም ብሎ ለከዳተኛነቱ ይዘፍናል። አንተ ብቻ ምለህ ታድናለህ፤ የሰው ልጅ ግን ምሎ እንደ ጴጥሮስ ይክዳል፣ እንደ ይሁዳ ስሞ ይገድላል።
ወጌሻም ይሰብራል፣
ሐኪምም ይገድላል፣
ዘብም ይደፍራል፣
ልጅም ይከዳል፣
ዘመንም ያልፋል፤
ተሰሚነትም ያበቃል፣
ጉልበትም ይቀንሳል፣
መልክም ይረግፋል፣
የወለዱት ልጅም ይረሳል፣
ያሳደጉትም ይነክሳል ፣
የሾሙትም ያስራል፣
በርታ ያሉትም ሊያጠፋ ይመጣል፣
ሲያጣ አንገት የደፋ ሲያገኝ ይወጠራል፣
ያስፈቱት ያስራል፣
ያሳመኑት ሃይማኖትን ይነጥቃል፣
እያመሰገነ የመጣ እየተሳደበ ይሄዳል ፤
አንተ ብቻ ….
አንተ ብቻ የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሰው ልጅ ግን ያፈቀረውን ሰው እንደ ሞኝ፣ የረዳውን ሰው እንደ ጅል እያየ ቸር አጥቂ ይሆናል። አንተ ብቻ ትደርሳለህ፣ የሰው ልጅ ግን ያለ ምክንያት አብሮ በልቶ ፣ የልቅሶ ቀን በምክንያት ይቀራል። አንተም አጋዥ ብትሻ ሰውን ወደዱ አልክ! በምኑ ቢሉህ “እንዲሁ” አልክ!
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ልብህ ልባችን ይሁን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም.