ልቤ በሁለት አሳብ ያነክሳል፣ መሐል መንገድ ላይ ቆሞ ወዴት እንደሚሄድ ይጨነቃል:: ሁለት መልካሞችን ወዶ አንዱን ለመምረጥ ይቸገራል። ልቤ ያመነታል፣ መንታ ነገር ገጥሞት፣ አንዱን ካንዱ መለየት አቅቶት ልቤ ተወጥሯል። ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ካልወጣሁ ይላል። አንድ ያልነበረው ሁለት ቤት፣ ሁለት ትዳር ያምረዋል። ሁሉን ለእኔ ብሎ ትዝብት ላይ፣ ሁሉን ላፌ ብሎ መርዝ ላይ ወድቋል። ልቤ በሁለት መንገድ መሄድ እንደማይቻል ቢያውቅም መቁረጥ አቅቶቷል። አንደኛው ልቤ ተቀመጥ አገር አገር ነው ይላል፣ ሌላኛው ልቤ ወገን ከሚያቆስለኝ የማያውቅ ቢንቀኝ ይሻላል ይላል። በዘመድ መካከል እንደ እንግዳ፣ በወገን መካከል እንደ ባይተዋር ከመሆን፣ ባዕድ ቢገዛኝ፣ የሩቁ ቢንቀኝ ይሻላል ይለኛል። አያት ቅድመ አያቴን የሚያውቅ፣ መልኬ መታወቂያ በሆነበት ምድር ማነህ? ስባል ልቤ አንተን ብቻ አውቆ ወደሚንቅህ አገር ሂድ ይለኛል።
አንድ ጥሩ ነገር ያልነበረኝ ሁለት ጥሩ ነገር ሲመጣልኝ ሁሉንም ልያዝ እላለሁ። ቡፌ የሚቀርበው ሁሉን ለማንሣት ሳይሆን የሚስማማንን ለመብላት ነው። ሁሉን አንሥቼ ሁሉም ነገር ያስጠላኛል። ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ ወዳጅ፣ ብዙ መዐርግ፣ ብዙ ሩጫ ጀምሬ መሐል ላይ ይስለቸኛል። አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራልና በቃኝ ባለ ማለቴ ስጨነቅ እውላለሁ፣ ስታክት አድራለሁ። ከሳሽ ማንነት ይጠናወተኛል፣ ያልረካሁት የብቻ ሯጭ፣ የብቻ ትዳር ሠሪ በመሆኔ ነው ይለኛል። ክርስትና ለሰማይ ርስት ብቻ ሳይሆን “ያለኝ ይበቃኛል” ለማለትም አስፈላጊ ነው። ያለኝ አገር፣ ያለኝ ቤት፣ ያለን ትዳር፣ ያለኝ ልጅ ይበቃኛል። የኖረኝ ነገር የመኖር ዋስትና አይሆንም። በሽተኛ ተቀምጦ ጤነኛ ይሞታል፣ እግረ ቀጭን ሳለ እግረ ደንዳና ያልፋል። ያለው እየሞተ የሌለው ይሰነብታል። ያሉ ነገሮች ሁሉ ኑሮን ቢያቀሉ እንጂ ሞትን አያስቀሩም። ማድረግ መቻል መርካት መቻል አይደለም።
ልቤ የሁለት ደብር ቀዳሽ አስቀዳሽ መሆን ይፈልጋል። መስቀል ከሰላጢን ይከጅላል። ልቤ በፖለቲካ ካባ ዕጣን ካላጠንሁ ፣ በካህን ቀሚስ ፖለቲካ ካልቃኘሁ ይላል። ልቤ መምረጥ አቅቶት ይዋትታል። ጥሩ ሰው መሆንና ጥሩ ኑሮ መኖር ሁለቱ ተጋጭተውበት ይታክታል። ሰብአ ዓለም መሆንና መናኝነት ሁለቱ ያንገላቱታል። መልከ ጼዴቅ መሆንና አብርሃም መሆን ያስጨንቁታል። ልቤ ስፍራህ የት ነው? እያለ እዚያ እዚህ መሆን የቱ እንደሚሻል ግራ ገብቶታል። እዚያም አልሄደም፣ እዚህም አልኖረም። ልቤ የቱን ሃይማኖት መምረጥ አቅቶት ይጨነቃል፤ መስቀል አልባ ክርስትናን ይናፍቃል። ሃይማኖት ዋጋው በሰማይ ነው ሲሉት ይማረካል፣ ሃይማኖት በምድር ነውና ባለጠጋ ያደርጋል ሲሉት ይቀላውጣል። ሁሉንም ሳይበላ ልቤ በቅምሻ ደክሟል። አለሁ ማለት እያጠራጠረው እግሩን ሳያነሣ ዓለምን ይዞራል። ልቤ እርጋታ የለውም፣ ያነበበውን ሁሉ ለመሆን ይፈልጋል፤ ያለፈው ሳምንት ሌላ ሰው ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሌላ ሆኗል። የኢየሩሳሌም ነፋስ አሥራ ሁለት ነው እንዲሉ ልቤ ሲለዋወጥ ይውላል። በልብ ሸንጎ ላይ ስከራከር እውላለሁ። የማወራው ባጣ ከራሴ ጋር ስብሰባ እቀመጣለሁ። በማይረዳኝ ማኅበረሰብ መካከል መኖር ከባድ ነው እላለሁ፣ መልሼ ብቸኝነት ያለ ሰው ሳይሆን ያለ እግዚአብሔር መኖር ነው እላለሁ።
ልቤ እንደ ብራና ተወጥሯል፣ መድኃኔ ዓለም እጆቹና እግሮቹ ቢወጠሩ ዓለምን ለማዳን ነው፣ እኔ ግን ራሴን እንኳ ላላድን ተወጥሬአለሁ። የእንጨት ምንቸት (ድስት) ራሱን አያድን ሰው አያድን የሚባለው ደርሶብኝ ወይ ለራሴ ወይ ለሰው አልኖርኩም ያሰኘኛል። ልቤ ያንተ ዕዳ ነኝ እንዲሁ ተቀበለኝ ይልሃል።
በቤትህ ውስጥ ያሉት እጅግ አስፈሪዎች ናቸው፣ ዓለማውያንን እንዳልመርጥ የመንገድ ካርታ የላቸውም። ወርቅ የያዘ በነሓስ አይቀናም። ማር የቀመስ ስኳር አይጣፍጠውም። ልቤ ግን ከማን ጋር ልዋል ? ከማን ጋር ልኑር ይላል። ይህን ካነሣሁልህ እባክህ ኢየሱስ ከኢየሱስ ጠበቆች አድነኝ። በተግባር የሚወድህ ካለ አሳየኝ። ወንድሙን እየጠላ እወድሃለሁ የሚልህ እንዳደከመህ አውቃለህ። በቤትህ ውስጥ ከመሸጉ ምሕረት የለሾች ጋርደኝ።
ልቤ ከሁለት ሥራ አንዱን መምረጥ አቅቶታል፤ ሁሉም ጋ ጥሩ ጎንና መጥፎ ጎን አለና ተቸግሯል። የአደጋ ስጋት በሁለቱም ቦታ ይደውልበታል፣ ላልመጣ ቀን የመጣውን ዛሬ በጭንቀት ያበላሻል።
ልቤ ይቅበጠበጣል። ጠግቦ ይሆን አርግዞ ማወቅ ተስኖቷል። ደጅ ወጥቶ አዲስ ነገር ማየትን ይፈልጋል። እቤት ሆኖ ማረፍም ይፈልጋል። ሁለት ነገር ሲወጥረው ያላሰበው ሦስተኛ ነገር ይወስደዋል። በወንዝ መሐል ልደነቅ ወይስ በሸለቆም ጫፍ ላይ ልረፍ ሲል ልቤ ያላሰበው ጎርፍ ይዞት ይሄዳል። በአልን ወይም አንተን ያህዌን መምረጥ አልቻልኩም፣ በሁለት አሳብ የሚያነክሰውን ሰማርያ ልቤን፣ በኤልያስ ሰይፍ ለየው። የወሰንኩትን መኖር ቢያቅተኝ የተወሰነብኝን እኖረዋለሁ።
ትንሣኤን ማመን አቅቶት ከጥብርያዶስ ተጠርቶ ወደ ጥብርያዶስ ሊሄድ ይፈልጋል። ጴጥሮስ ልቤ ብቻውን አምኖ ሰው ጨምሮ መካድ ይፈልጋል። ካለሁበት ቦታ ካልመጣህ ኢየሱስ ሆይ ወዳንተ መምጣት አይሆንልኝም። የሥጋን ልብ ካልጨመርህልኝ የድንጋዩ ልብ ሞቶ ይገድለኛል። ለማረፍ ሄጄ ሥራ እጀምራለሁ፣ ሥራ ስጀምር መቼ ነው የማርፈው ? እላለሁ። እንደ እርጉዝ እቀበጠበጣለሁ ፣ ሁሉን ካድ ብትለኝ ሁሉን ይዤ መከተል እፈልጋለሁ። ጸሎቴን አቋርጬ ስልክ አነሣለሁ፣ ስልክ ላይ ሆኜ መጸለይ እሻለሁ። በአንድ ጊዜ ሰባኪ ደግሞም ተዋናይ መሆን እፈልጋለሁ። ትዳር ያምረኛል፣ ሳገባ ምናኔ ይናፍቀኛል።
ልቤ መንታ ነው፣ እንኳን ሰው እኔ የወለድኩትም አልለየውም። የምመርጠውን አላውቅም። እያፈቀርሁ ነው እየጠላሁ ? መረጃ የለኝም። አመካከት እንደ አባቴ፣ አጨካከን እንደ እናቴ ብዬ የተኰስኩ እንደሆነ አልስትም፣ የራራሁ እንደሆነ ስሜ እምዬ ነው። እኔ ማን ነኝ? ካንተ ጋር ነኝ ስል ከራሴ ጋር ነኝ። መሣሪያ አውርጄ ቤተስኪያን ደጅ ላይ ለጥ ብዬ እሰግዳለሁ፣ ስነሣ ለመግደል እጓዛለሁ። ጌታ ሆይ አመነታለሁ ፣ አሳቤን አንተው ቍርጥ አድርገው! በዓለም ላይ መገኘት ሳይሆን መኖር እሻለሁ። በአንድ አሳብ፣ ይልቁንም በአንተ አሳብ አጽናኝ እላለሁ። ለዘላለሙ አሜን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም.