ውደዳቸው
ሌላውን የሚወድ ሰው ራሱን የሚወድ ነው። በዓለም ላይ ያለው የሞራል ሕግ “ባንተ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን ክፉ ነገር በሌላው ላይ አታድርግ” የሚል ነው። የክርስትና መርሕ ግን:— “ሌሎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን አንተም አድርግላቸው” የሚል ነው ። ሌሎች እንዲወዱህ ትፈልጋለህ? ውደዳቸው። ሌሎች መልካም እንዲያደርጉልህ ትሻለህ? መልካም አድርግላቸው።
ሲወዱህ ጠብቀህ መውደድ ከፈለግህ ዕድሜ ልክህን የሚወድህ ሰው አታገኝም። ቀድመህ ውደዳቸው፣ ከዚያ ይወዱሃል። ፍቅር እስትንፋስ ነው፣ ያለ ፍቅር ሙት ፣ በድን ፣ የደረቀ ቅጠል ነህ። ሰዎችን የምትወዳቸው ስለሚገባቸው ሳይሆን ላንተ የሕይወት ነጻነት ፍቅር አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ፍቅር የሌለው ሰው ትልቁን እስር ቤት ሲኦልን ተሸክሞ የሚዞር ነው። በእውነት ለመውደድ ወይም ለመወደድ ካልሆነ በቀር በዚህ ዓለም ላይ የምንኖርበት ሌላ ምን ምክንያት አለን?
በወደድካቸው መጠን ሰዎች ላይወዱህ ይችላሉ። ስላንተ ግድ የሚለው ሰው ያለ መስሎ ላይሰማህ ይችላል። ሽቶ ስትቀባ ንቦች ይፈልጉሃል ፣ ከዚህ ሰው የሚቀሰም ነገር አለ ብለው ያስሱሃል። የሞተ ነገር ስትነካ ፣ የሚሸት ሥጋ ስትይዝ ዝንቦች ይጠጉሃል:: ፍቅር ሽቱ ነው። የተጠጋህን ሁሉ ደስ ያሰኛል። በጥላቻ ካለህ ሰይጣን ያለ ቁልፍ ወደ ቤትህ ይገባል። ሽቱ የቀረበህን፣ በአጠገብህ የሚያልፈውን፣ አብሮህ የተቀመጠውን ሁሉ ይሽተዋል እንጂ ሰው አይመርጥም። ፍቅርም ለሁሉ የሚሰጥ ነው:: ሸቱ የምትቀባው ለራስህ ነው፣ ሌላውን የምትወደው ለራስህ ብለህ ነው። ሽቱ የሚያውደው አጠገብህ ያለውን ነው፣ እውነተኛ አፍቃሪም አብረውት ለሚኖሩት ፣ ለሚወዱት ዋጋ የሚሰጥ ነው። እኔ ሰውን ሁሉ እወዳለሁ የሚሉ ሰዎች አሉ። ፍቅር ግን አንድን ሰው መውደድና ለእርሱ ዋጋ መክፈል ነው። ማንንም አልጠላም ማለት ፍቅር አይደለም፣ እንደውም ስለ ማንም ግድ የለኝም ማለት ነው::
እግዚአብሔርን የማይወድ ወደ መንግሥቱ አይገባም። ወንድሙን የማይወድ፣ እግዚአብሔርን አይወድም። ፍቅር የሌለው ሰው ኑሮው ደስታ፣ ሞቱ ተስፋ የለውም። ለእግዚአብሔር ያለህን ፍቅር የምትገልጥበት ጎረቤትህ በመገኘቱ ዕድለኛ ነህ። ፍቅርን ከመቀበል መስጠት ደስተኛ ያደርጋል። ብቻ ሰውን ውደድ። የእግዚአብሔር ፍቅር ህፀፅ የለበትምና እንኳን ለሰው ለእንስሳትና ለእጽዋትም ይተርፋል። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ሁሉን ይወዳል። ፀሐይን ሲያይ በደስታ ይዘላል፣ ጨረቃን በስስት ያያታል፣ የአበቦች መዓዛ ይመስጠዋል ። አራዊት ሰውን አፍረው ሌሊት መውጣታቸው ይገርመዋል። ዘነበ ብሎ አይነጫነጭም ፣ ከተፈጥሮ ጋር ታርቆ ይኖራልና ደስታው አይቋረጥም።
ውቅያኖስ ላይ የተተከሉ ማማዎች ለመርከቦች በጨለማ መብራት ይሰጣሉ:: በዚህ ማማ ላይ መብራቶቹን ሌሊት ላይ የሚቆጣጠር ሰው በዓመት በሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል ፣ ቀን ዓሣ ሲያጠምድ መዋል ይችላል ፣ የሚላተመው ማዕበል ግን ከባድ ጭንቀት እየፈጠረበት ይመጣል ። ይህ ሥራ በዓለም ላይ ካሉ ሥራዎች ከባዱ ነው። ምክንያቱም አጠገቡ ሰው የለምና። የሚሊዮን ዶላር ክፍያን እምቢ ያልከው ሰው ስለምትፈልግ ነው ። ሰው መድኃኒት ነው። የግለኝነት ምንጩ ሰይጣናዊ ዕድገት ነው ። ያለ ሰው ባለጠጋ ከመሆን ከሰው ጋር ድሀ መሆን ይሻላል። ሰርጉም ልቅሶውም ያለ ሰው አይደምቅም። አንተ ለሰዎች ከምታስፈልጋቸው በላይ ሰዎች ላንተ ያስፈልጉሃል።
ልጄ ሆይ እባክህ ሰው ውድድ !
ይቀጥላል
ክፍል 1
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም.