አድንቃቸው
እግዚአብሔር አድናቂ አምላክ ነው። እያንዳንዱን ፍጥረት ከፈጠረ በኋላ መልካም እንደሆነ አየ ይላል፣ ሰውን ከፈጠረ በኋላ ግን እጅግ መልካም ነበረ ይላል።
ሰው መልካም ብቻ ሳይሆን እጅግ መልካም ነው። አንድ ዜጋ መልካም ነው ሲልና አንድ ንጉሥ መልካም ነው ሲል መጠኑ የተለያየ ነው። አንድ ያልተማረ ሰውና የተማረ ሊቅ መልካም ነው ሲሉ ክብደቱ ለየራስ ነው። እግዚአብሔር መልካምነው ሲል ከዚያም አልፎ እጅግ መልካም ነው ሲል ከሰው መረዳት በላይ ነው። ሰዎች አድናቆትን ይፈልጋሉ። ያላቸውን የተዋበ ነገር ከእኛ አንደበት ሲሰሙት እርግጠኛ እየሆኑ፣ ኃይላቸው እየጨመረ ፣ ውስጣቸው ከፍ እያለ ይመጣል። የሚያደንቃቸው ሰው አለና የበለጠ ለመሥራት ይነቃቃሉ። ጥሩ ልብስ ለብሰው እኛ እንድናደንቅላቸው ይፈልጉናል። ተኝተን እንደሆነ እስክንነሣ ጠብቀው አምሮብኛል ወይ ? ይሉናል። የእጅ ጽሕፈታቸው እንደሚያምር ስንነግራቸው ከኮምፒዩተር በተሻለ መጻፍ ይጀምራሉ። የፈጠራ ሥራቸውን ስናደንቅ ለዓለም የሚበጅ ነገር ያቀርባሉ።
የሰው ልጆች በአብዛኛው እናታቸውን የሚወዱት ስለምታደንቃቸው ነው ። ትንሹን ተግባራቸውን ትልቅ አድርጋ ታያለች። የእኔ ልጅ እንዴት ጎበዝ ነው ? ትላለች። ያ ልጅ ከአባቱ የሚርቀው አባቱ የአሁኑን ትንሽ ተግባር ነገ ላይ ትልቅ ይሆናል ብሎ ማየት ስለሚያቅተውና ስለሚነቅፈው ነው። “ይልቁንስ ትምህርትህን በደንብ ብትከታተል ይሻልሃል” በማለት ራእዩንና የፈጠራ ችሎታውን ሲያጣጥልበት እየራቀው ይመጣል። የሰለጠኑ አገራት የልጆችን አካሄድ በማጥናት ያግዙአቸዋል። በዚህ ምክንያት አገራቸው ታድጋለች። የነገ አገር በዛሬ ልጆች ትከሻ ላይ ተሳፍራለች።
ብዙ ባሎች በቤታቸው ደስተኛ የማይሆኑት ሚስታቸውንና ተግባሯን ማድነቅ ባለመቻላቸው ነው። በቀጣዩ ቀን ጣፋጭ ምግብ የሚያገኙት ባደነቁ መጠን ነው። ስለማያደንቁ አልተደሰቱም በማለት የነበረው እንክብካቤ እየቀነሰ ይመጣል። ባሎች የሠሩትን ሥራ፣ ያገኙትን ገንዘብ እቤት ድረስ ይዘው የሚመጡት ሚስታቸው እንድታደንቃቸው ነው። ምንም ስሜት የሌላት መሆኗን ሲያዩ የሥጋ ቤተሰባቸውን መፈለግ ይጀምራሉ። እያደገ ሲመጣ ሌላ ሴት ይፈልጋሉ። በፍቺአቸው ሰዓት:— “ያን ሁሉ ሥራ ስሠራ አታደንቀኝም ነበር፣ ብቻዬን የሮጥኩበትን ሀብት አሁን አትካፈልም እያሉ ይናገራሉ። አለማድነቅ ቀጣይ ላለማግኘት መወሰን ነው። አለማድነቅ መሰለቻቸትንና መለያየትን ያመጣል።
ዛሬ ላይ ጠላት ቢሆኑን እንኳ ያደንቁን የነበሩ ሰዎችን እንወዳቸዋለን። የእነርሱ አድናቆት የዛሬ ከፍታ ላይ እንዳደረሰን እናስብና ከልብ መጥላት ያቅተናል። አድናቂ ሰው ባለ ውለታ ነው። ብዙ ሰዎች በውስጣቸው የከበረ ነገር፣ ለዓለም መልስ የሚሆን ምሥጢር ይዘው ነበር ፤ በማጣጣል፣ በመንቀፍ፣ ዝም ብለህ ነው፤ አጉል አትፈላሰፍ በማለት ቀብረናቸዋል ። ማድነቅ ሰውን ከገጠርና ከትንሽ መንደር አውጥቶ ከፍ ያለ ቦታ ያደርሰዋል። ኳስ ተጫዋቾች ፣ ሯጮች ለሥራ፣ ለጤና ብቻ ሳይሆን ለአድናቂዎች ብለው ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው። በባሕላችን አድናቆትን በልባችን ፣ ነቀፋን በአፋችን እያደረግን ነውና ያሳዝናል። በርግጥ የዕድሜ ባለጠጎቹ ጎሽ የእኔ ልጅ ፣ ጎበዝ፣ አንተ እኮ በልጅነትህም ብልህ ነበርህ ይላሉ:: አንዳንድ ሰዎች የሚያደንቁት የሚፈልጉት ነገር ስላለ አደንዝዞ ለመቀበል ነው ። እውነተኛ ሰዎች ግን ከቅናትና ከጥቅም ፍላጎት የተፈቱ ናቸውና በእውነት ያደንቃሉ።
በቤተ ክርስቲያን በቅኔ ማኅሌት፣ በ0ውደ ምሕረት ቅኔው ሲቀርብ አድናቆት ይቸረዋል። ድንቅ ነው፣ ግሩም፣ ረቂቅ ነው ፣ እንኳን ለሌላው ለሊቃውንትም የከበደች ናት ይባላል:: ጳጳስ ፣ ፓትርያርክ ሲሾም ይደልዎ – ይገባዋል ይባላል። በትእዛዝ ቃልም አክዮስ ይደልዎ ይበሉ ይላል። ይገባዋል፣ ሹመት ያደብር ማለት ነው፡ የሚሾመው ሰው ይህን ሲሰማ የወገኑን ይሁንታ አግኝቷልና ደስ ይለዋል፤ ኃይል ያገኛል። ነቢዩ ዳዊት ራሱን አድንቋል፦ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” ብሏል (መዝ. 138 ፥ 14):: ስለ ተፈጥሮአችን ማሰብና ማድነቅ ይገባናል። በእውነት ድንቅ እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ ? ዋጋ የማይተመንለት አካል ባለቤት ናችሁ ! እናንተን የሚመስል በዓለም ላይ የለም ! ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር እናንተን ሲያይ እጅግ ደስ ይለዋል!
ሥላሴ ወደ አብርሃም ቤት የሄደው የአብርሃምን እንግዳ ተቀባይነት ለማድነቅ ነው ።
ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ። አሜን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም.