መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -11

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -11

የገቢህን ምንጭ አትንገራቸው

እጅግም ግልጽነት እብደት ነው። ሳይጠየቁ መለፍለፍም አብሾ ነው። ሰው ከሰው ጋር የሚኖር ፍጡር ነው። ሰው ደግሞ ከራሱና ከእግዚአብሔርም ጋር የሚኖር ፍጡር ነው። ሰው ከራሱና ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖር ነውና  ለሰዎች የማይነግራቸው ነገሮች አሉ። ከራሳችንም ሆነ ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት እግዚአብሔርን ገለል ማድረግ አንችልም። ራሳችንንም ሰዎችንም የሰጠን እርሱ ነውና። ደግሞም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውድድ ያለው እርሱ ነው። ራስህ እና ባልንጀራህ ይላል። ሰው ከራሱና ከባልንጀራው ጋር የሚኖር ፍጡር ነው። ይህንንም ጸጋ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። ሰው ራሱን መውደድ አለበት። በበቂ መተኛት፣ ምግብን በሰዓቱ መመገብ፣ ንጽሕናን መጠበቅ፣ መጦሪያውን ማዘጋጀት አለበት። ራሱን ከጣለ የሚያነሣው የለም:: ለራሱ ክብር ከሌለውም ማንም አያከብረውም። ባልንጀራህን እንደ ራስ መውደድ ለባልንጀራ ማሰብ ነው። ቤት ሠርቻለሁ፣ አንተም ሥራ ማለት ነው።

ጌታችን ፈውስን ሰጥቶ ለማንም እንዳይነግሩ በጥብቅ ያዘዛቸው ሰዎች ነበሩ። እነዚያ ሰዎች ለመዳን ደረሱ እንጂ ለምስክርነት አልደረሱም። ደግሞም ፈውሳቸውን ሊያስተባብሉባቸው ይችላሉ። የሥነ ልቦና ፈውስ እንጂ እውነተኛ ፈውስ አላገኘህም ሊሉአቸው ይችላሉ። ክርስቶስን እኮ ካህናትና ሊቃን ካህናት አልተቀበሉትም፣ ደግሞም ተወግዞአል ፣  እንዴት ተቀበልከው? ብለው ጥላቻን ሊዘሩባቸው ይችላሉ። የክርስቶስ ጠላቶች በክርስቶስ ምስክሮች ላይ የሚያደርሱት ግፍ ክርስቶስን ያገኙ እስኪመስላቸው ድረስ ነው :: እነዚህ ሰዎች ምስክርነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ገና ልጆች ናቸው ። ለአዲስ ክርስቲያን አራት ነገሮች አይታዘዝም፡- ጾም ጾሙ ተብሎ አይታዘዝም ፣ ሕፃናት መቆየት አይችሉምና። ሁለተኛ የአስተዳደር ችግር አይነገራቸውም ፤ በጫጩት ፊት ፈንግል አይወራምና :: ሕፃናት አባታቸው ሁሉን ቻይ ስለሚመስላቸው አባታቸውን ሲያጣጥሉባቸው ይገዳሉ ፣ አዲስ አማኝም አገልጋዮችን ፍጹም አድርጎ ያያል ። ጦርነት ሁሉን ቢጎዳም የበለጠ ተጠቂዎች ሴቶችና ሕፃናት ናቸው ።  ሦስተኛ ምስክርነት ስጡ ተብለው አይጋበዙም፣ ለጋ ዛፍ እንኳን ሊጠልል ጥላ ይፈልጋል። አራተኛ የአባቶች ብርታት እንጂ ድካም አይነገራቸውም ፣ አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል እንዲሉ እንኳን ኃጢአትን ትንሽ ጽድቅን ማየት አይፈልጉምና።

ይህን ያህል ገንዘብ አገኘሁ ብሎ ማውራት አይገባም። ማግኘትህን የሚወድ ሌባ ብቻ ነው ይባላል። እርሱም ሊሰርቅ ነው። በዚህ ዓለም ላይ በኀዘናችን አብረው የሚያዝኑ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል::  በደስታችን የሚደሰቱ ሰዎችን ማግኘት ከባድ ነው :: ይልቁንም በአገራችን ብዙ ሰው  በችግር ውስጥ ስለሚያልፍ አብሮ የሚያዝነው ብዙ ነው። ደስታ የመጣ እንደሆነ ፣ ሥልጣንና ከፍታ ወደሚያውቁት ሰው ሲሄድ ብዙዎች ይታመማሉ::  የማያውቁት ሰው ቢከብር ቢበለጽግ ደስተኛ ናቸው። የሚያወት ሰዉ አንሶ እንዲኖር ይፈልጋሉ። በዚህ በቅናት ምክንያት ንብረት በመያዛቸው፣ ሥልጣን በመጨበጣቸው ምነው በቀረብኝ የሚሉ ሰዎች አሉ። ማንም ይዘን ዕድልን ማጣጣም ይገባል። ከሰው ፍቅርና ከረሀብ ምረጡ ቢባል የሰው ፍቅር የሚል የለም። የሰው ፍቅር ቢያጡ ይኖራሉ፣ እህል አጥቶ ግን መኖር የለም። ለመወደድም መኖር ያስፈልጋል። ደግሞም ዛሬ የጠላ ነገ ይወዳል፣  ዋናው  ይዞ መገኘት ነው። ቅዱስ ነው ሲሉት የነበረው ሰው ትንሽ ሲሳካለት የዛሬ ሃያና ሠላሣ ዘመን ኃጢአቱ ከፍሪጅ ወጥቶ መወራት ይጀምራል:: በድህነቱ ጻድቅ የተባለው አሁን ከፍ ሲል ነውር አለበት ይባላል። ቅናት በሁሉ አገር መንፈስ ነው፣ በእኛ አገር ግን አካል አለው ። ሰዎች የሞተን ሰው ክፉ አይሉትም፣ የቆመን ግን ጥላሸት ይቀቡታል ። ስም ከሰጡህ አለህ ማለት ነው፣  ደስ ይበልህ። ካሞጋገሱህ፣ ሽልማት ከሰጡህ፣ የአድናቆት ቀን ካዘጋጁልህ የለህም ማለት ነው ። በእርግጥም ቀና ሰው ከሆንህ  አንተን ለማወቅ ከሞትህ በኋላ ሰባት ዓመት ያህል ያስፈልጋቸዋል። እንኳን የሩቁ ሰው ሚስትና ልጅህ የሚያውቁህ የቀብር ቀንህ ላይ ሌሎች ስለ አንተ ሲናገሩ ሰምተው ነው። እግዚአብሔር ካወቀህ ይበቃሃል።

ይህን አገኘሁ ብለህ ስታወራ ቸግሯቸው ከሆነ ጌታዬ ምነው በእኔ ላይ ጨከነ ይላሉ::  የድሮ ባለጠጎች ለየት ያለ ልብስ እንኳ የማይለብሱት ከማኅበረሰቡ ላለመለየት ነው። ቀና ቀና ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ ይባላል። የዛሬ ባለጠጋ ቶሎ ታይቶ ቶሎ የሚጠፋው እዩኝ እዩኝ ስለሚወድ ነው።  የዛሬ ባለጠጎች ገንዘብ እንጂ እውቀት አይሰበስቡም፣ አጫዎች እንጂ ሊቅ አይወዱም፣ ብልጠት እንጂ ብስለት የላቸውም። ስለዚህ ቶሎ ይጠፋሉ። አገኘሁ እያሉ ቢያወሩ ሁሉም ሰው ካላበደረን ብሎ ይመጣል። ጎረቤት የገባውን ገቢ እንጂ የወጣውን ወጪ አያውቅምና ይቀየማል። ይልቁንም ቤት ሠራው መርቁልኝ ብሎ መጥራት በላያችን ላይ በገዛ ግብዣችን ጠላት ማደራጀት ነው።

ሁሉ ወዳጅ አይደለም፣ ሁሉም ጠላት አይደለም። ከሰው ጋር ላለን ኑሮ ሁለት ብልሃት አለው። ማስተዋልና ጥንቃቄ፦ ማስተዋል ለነገ፣ ጥንቃቄ ለዛሬ። የገቢህ ምንጭ መንግሥት ከሆነ ከእገሌ ጋር ይገናኛል ብለው ሞት ይጠሩብሃል:: የገቢህ ምንጭ ወዳጅህ እንደሆነ ነገር ሠርተው ያጣሉሃል። የገቢህ ምንጭ የንግድ ስልትህ ከሆነ ስምህን ያጠፉታል። ሰማይ እስክንደርስ በጫካው ዓለም ላይ ብዙ አውሬ እናስተናግዳለን::  ለአንድ ሕይወት ሺህ ፈተና እናስተናግዳለን:: ጌታችን በሰይጣን በቀጥታ የተፈተነው አንድ ጊዜ ነው። በሰው ልጅ ግን ዘመኑን በሙሉ ተፈትኗል። ለዚህ ነው “ከሰዎች ተጠበቁ” ብሎ የመከረን። ያልተጻፈልን የለም፣ ባለ ማስተዋል ግን አጉል ዋጋ እንከፍላለን።

ኮካ ኮላ የቅመማ ምሥጢሩን እስካሁን አላሳወቀም። የአገራችን የመድኃኒት ቀማሚዎች የማይናገሩት ሁሉም ቀማሚ ሆኖ ሰው እንዳያልቅ ነው። በርግጥ ሙያን ለሁነኛ ሰው ማውረስ ሞትን መበቀል ነው።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ