ፖለቲካና የዘር ወሬ አታውራ
ፖለቲካ አስተዳደር ነው፣ ጎሣም ሰው የወጣበት ነው። ፖለቲካ ሰዎች የሚመርጡት ነው ፣ ጎሣቸው ግን የተመረጠላቸው ነው። ፖለቲካ የጋራ አገርን በተሻለ መንገድ እንምራ የሚል ብዙ አሳብን ለማስተናገድ ልብ ያለው ነው። ለአገሬ ክፉ ላድርግ ሳይሆን የተሻለ መልካም ላድርግ የሚል ጭንቀት ነው:: የአገሩን ሰላም፣ ፍትሕና ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንዲሆን እቅድ ይዞ የሚመጣ፣ ዕቅዱንም በመሐላና በሥልጣን የሚጀምር ነው። ሥልጣን ከሌለ እቅድ ምኞት ሆኖ ይቀራል፣ ዕቅድም ከሌለ ሥልጣን መንከራተት ሆኖ ያበቃል:: ፖለቲከኞች የአንድ አገር ልጅነታቸውን አምነው ወንድማማች መሆናቸውን መቀበል አለባቸው። ለአገሬ እኔ የተሻለ አሳብ አለኝ ብለው አሳባቸውን ገበታው ላይ ማቅረብ አለባቸው። የተለየ አሳብ ቢኖረውም ያኛውን ወገን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወዳጅ መመልከት አለበት።
ፖለቲካ የወደቀ አገርን ለማንሣት ፣ የተነሣ አገርን ትንሣኤውን ለማስቀጠል የሚረዳ የአስተዳደር እቅድ ነው። ፖለቲካ የአሳብ ስብስብ እንጂ የጎጥ ስብስብ ሊሆን አይገባውም። በልብ ስፋት ሁሉን የሚቀበል እንጂ የማይከተለን ጠላት ነው ማለት የለበትም። ፖለቲካ ያስፈለገው ነፍጥ ጥሎ አሳብን ለማንሣት ነው ። ፖለቲካ አፍ ብቻ ሳይሆን ጆሮም ሊኖው ይገባል። አፍ ብቻ ከሆነ መናገር እንጂ መስማት አይችልምና የደናቁርት ጉባዔ ይሆናል። ጆሮ ብቻ ከሆነም በዕለቱ ትኩስ ወሬ እንጂ ነገን በሚያይ ራእይ መምራት ያቅተዋል። ፖለቲካ የተጻፈና የተቀመረ ርእዮት ያስፈልገዋል። አሊያ ስሜታዊ ወንዝ ሆኖ አገርን ነገ የለሽ ያደርጋታል። መቼም ፖለቲካና ሥልጣን ራስን መግዛት ይጠይቃል:: በራሱ ላይ የበላይ ያልሆነ በሌሎች ላይ ሊሰለጥን አይችልም። ፖለቲካ አስፈሪ ርእስ መሆን አልነበረበትም። በእኛ አገር ግን ስሙ ራሱ አስፈሪ ነው። የተሰጠው ትርጉምም ውሽት የሚል ነው። ይህ መሆን አልነበረበትም። በጋራ አገር ላይ እኔ ብቻዬን አውቅላታለሁ ማለት ራስን መጉዳት፣ ሌሎችን መናቅ ነው።
የሌላውን አሳብ ለመስማት ድፍረቱም አቅሙም ባልዳበረበት ፣ የአሳብ ልዩነት እንደ ጠላት በሚያስተያይበት ፣ የግል ጥቅም እንደ ብሔራዊ ፍላጎት በሚቀነቀንበት አገር ፖለቲካዊ ወሬ ወዳጅነትን ይጎዳል:: ከሁሉ የሚቀድመው ሰው መሆን ነው። ቀጥሎ መቀባበል ነው። የሌላውን ህልውና ሰርዞ እንደ እኔ ያስብ ማለት ተገቢ አይደለም። የዘር ፖለቲካ በሌሎች ተቀምሮ የተሰጠን ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ ነው። ፖለቲካው ከዘረኝነት ጋር ከተጣበቀ አሳቡን ብንቃወም ማንነቴን ተቃወማችሁ ይላል። ፍንጣሪውን እቶን እሳት አድርጎ ያሳድገዋል። ሰው በተፈጥሮው ሳይሆን በምርጫው ሊዳኝ ይገባዋል። ወደዚህ የአሳብ ልዕልና እስክንደርስ የፖለቲካ ወሬን መቀነስ ከሰው ጋር ላለ ግንኙነት ወሳኝ ነው:: ብሶት ፖለቲካ ሲሆን ተበቃይ ይሆናል። ፖለቲካ በእርቅና በወዳጅነት፣ ሌላውን በመቀበል መጀመር አለበት።
ዘረኝነት በምድር ላይ ካሉ በሽታዎችና ወረርሽኞች ቀዳሚው ነው:: እግዚአብሔር በሰጠን ጎሣና ቋንቋ ማፈር ኃጢአት ነው። ከእግዚአብሔር እጅ የምንቀበለው ተራና ትንሽ ነገር የለምና። በተሰጠን ጎሣና ቋንቋ መመካትና ሌላውን ማሳነስ እግዚአብሔርን ትንሽ ፍጡር አስቀምጠሃል ብሎ እንደ መሳደብ ነው። በአገራችን የዘረኝነት ስሜቶች፣ የመናናቅ ባሕሎች የኖሩ ናቸው፡ እነዚህን በእውቀት ፣ በመቀባበል፣ በማስተሳሰር ማስወገድ ይገባናል። ሰው ከተወለደበት ስፍራ መንቀሳቀስ ሲጀምር ያንን ወገን እየወደደው በጋብቻ እየተጋመደ ይመጣል። ጥላቻን መሠረት ያደረገ የዘር ፖለቲካ ያፈረሰው እንጂ የገነባው አገርና ሕዝብ የለም። ሰው በቂ እውቀት ከሌለው የሚደበቀው ማንነቴ ብሎ የሚጠራው ጎሣ ውስጥ ነው። መኖር የማወቅ ዕድል ነው፣ ማወቅ ዛሬም ይቻላል ። ሁሉን ማወቅም አይቻልም፣ መጠየቅ ጨዋነት ነው። ዘረኝነት ጠንሳሹን ሳይቀር የሚገድል ክፉ መርዝ ነው። የእውቀትና የሥልጣኔ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ የሰውነት ልዩነት ግን በዓለም ላይ የለም። ለአጥቢያ ሳይሆን ለመላው ዓለም ድምፅ የምንሆነው ሰው ነኝ ብለን ስናስብ ነው። ሰውነት ሰፊ መስክ ነው።
ጎሣን መሠረት ያደረገ ወሬ፣ ጨዋታ ፣ የጥላቻ ንግግር፣ የባሕል ነቀፌታ በፍጹም አያስፈልግም። ሰውን ባወጣንለት ስም ሳይሆን ስሜ ይህ ነው ባለው መጥራት ተገቢ ነው። ስለዚህ የሚወደውን መጠሪያ እንዲህ ብለህ ጥራኝ ባለው መጥራት ይገባል። ፖለቲካ ዕለታዊ ርእስ መሆን የለበትም፣ ዘረኝነት መቼም ርእስ መሆን የለበትም። ስለ አሳብ ሲወራ የጎሣ ጆሮ ይዞ መስማት ተገቢ አይደለም። ግፈኛ የሚወገዘው የማንም ጎሣ ቢሆን ነው። የቅን ፍርድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ መባ ነው። ክርስቲያን ክርስትናው አንሶበት እኔ ከእገሌ ጎሣ ነኝ ማለት የለበትም።
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የፖለቲካ ወሬን መቀነስ፣ የዘረኝነት ድምፅን ማጥፋት ይገባል ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም.