ካልነገሩህ በቀር ምሥጢራቸውን አትጠይቅ
ሰዎች ቶሎ ተዋደው ቶሎ የሚጣሉት ፣ ቶሎ በረው ቶሎ የሚያርፉት ምሥጢራቸውን በሙሉ በመጫወታቸው ነው። የተማረ ሰው ባወቀ መጠን ያን ሰው እየወደደው፣ እያከበረውና የእኔ ዕዳ ነው ብሎ እየተሸከመው ይመጣል:: ችግሩንም የጸሎት ርእሱ ያደርገዋል እንጂ አይርቀውም፣ በዚህም ደጉ ሳምራዊን ይመስላል። ያልተማረ ግን አወቅሁሽ ናቅሁሽ ውስጥ ይገባል። ምሥጢር ሰውን የማይታወቅ የሚያደርገው፣ በልቡ መዝገብ ተሰውሮ የተቀመጠ፣ ለፈቀደው ሰው ብቻ የሚነግረው የግል ጉዳዩ ነው። በዚህ ዓለም ላይ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ። ፍጹም ድብቅ የሆኑ፣ ፍጹም ግልጥ የሆኑና መጥነው የሚያወሩ ናቸው:: ፍጹም ድብቅ መሆን በቀላል ጉዳይ መሰቃየትን ያመጣል። የሰው መድኃኒቱ ሰው ነው። ችግሩን የሚናገር መፍትሔ አያጣም። ፍጹም ግልጥ መሆን ባለቤቱን ነጻ ቢያደርገውም ክብርን እንዳያገኝ ያደርገዋል። መጥነው የሚናገሩ፣ ሰውና ቦታ እንዲሁም ጊዜን ለይተው የሚያወሩ የተደነቁ ሰዎች ናቸው። ዝምታ አያስከብርም፣ ዝምታ ጨዋነት አይደለም ፣ አንገት ደፉ አገር አጥፊ ነው። በዝምታችን ሰዎች እያከበሩን ሳይሆን እየፈሩን ይሆናል:: ይህ ሰው ዝም ይላል በራሱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ብለው እየሰጉን ይሆናል ። ለራሱ የማይሆን ለእኛም አይሆንም እያሉ ነው። ዝም ማለት፣ ደርባባ አቡን መስሎ መቀመጥ ለጊዜው ትልቅ ያስመስላል፣ ቆይቶ ግን ያስንቃል። ሲከፍቱት ተልባ ያሰኛል።
ክብር እንደ ጥላ ናት። ሲከተሏት ትሸሻለች። ዛሬ የምናከብራቸው ጻድቃን ሰማዕታት ክብርን የናቁ ናቸው። ክብር በዝምታ አይገኝም፣ ውስጡ አይታወቅም ተብሎ ግን ሰው ሁሉ ያንን ዱዳ ሰው ይፈራዋል:: ሁልጊዜ መናገር ፣ ሁሉን መናገር ተገቢ አይደለም። ሁሉም ሰው ወዳጅ አይደለምና። አገር ምሥጢር ከሌላት ትወድቃለች፣ በጦርነት ውስጥ ድል ያለው ምሥጢር በመጠበቅ ነው።
ዛሬ በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች የተሰበረ የመንገድ ፍሳሽ ፣ ሜዳውን እንደሚሞላው የሰዎች ምሥጢር እየወጣ ነው። ጨዋ የሚመስሉ ሕዝቦች ማኅበራዊ ሚዲያው እያጋለጣቸው ነው:: ሰዎች ሁለት ሆነው ያወሩትና ያሳለፉት ምሥጢር አይወራም። ምክንያቱም የራሳቸውም ታሪክ ነውና። የሥነ ልቡና አማካሪ፣ የትዳር መማክርት ፣ ንስሐ አባት የተዘጋጀው በአደባባይ የማይነገሩ ነገሮች ስላሉ ነው። ግላዊ ጭንቀትን ለሥነ ልቡና አማካሪ ፣ የባልና የሚስትን ጉዳይ ለትዳር ዐቃቢያን፣ የግል ኃጢአትን ለአበ ነፍስ መናገር ተገቢ ነው። አንድ ማኅበረሰብ ሙያን፣ ጥበብንና መንፈሳዊ ባለ አደራነትን ሳያገናዝብ ምሥጢሩን አደባባይ ከዘራው ፈርሷል ማለት ነው። ማኅበረሰብ ቢሰማ ሊማር፣ ሊፈራ፣ ሊጠነቀቅ ይችላል። ከዚያ አልፎ ግን ብልግናን ማለማመድ ሊሆን ይችላል። የግልና የትዳር ምሥጢር፣ ሁለት ሰዎች ብቻ የሚያውቁት ንግግር አደባባይ አይወራም። ዘመኑ በአደባባይ መራቆትን እያበረታታ ነው። እገሌ ማን መሆኑን ሰው ይወቀውና ይጠንቀቀው፣ ስለ እርሱ የምታውቀውን ተናገር በማለት እያውጣጣ ነው። ማኅበረሰቡ ግን የራሱ የኑሮ ትግል አለው። ከዚያ ሁሉ በላይ የሰው ገመና ቡና መጠጫ ሲሆን ያሳዝናል። እኛስ ነገ ላይ በደል ቢደርስብን የመናገሪያ ቦታውን አውቀን ይሆን? ለእግዚአብሔር ትቼዋለሁ የሚሉ ሰዎች አሉ። እግዚአብሔር ብቻ ሊሰማው የሚገባ ምሥጢር አለ ማለት ነው። በአደባባይ ወጥቶ የሰውን ምሥጢር ማውራት ዘመናዊ ብቀላ ሆኗል ነው :: ኮምፒዩተርና ስልካችን የመቆለፊያ ኮድ አለው። ሰው ራሱ ከሠራው ዕቃ እያነሰ ነው:: ስልኩን እየቆለፈ፣ ራሱን እየከፈተ ነው::
ወዳጅነት እያደገ የሚመጣ ነው። በዕለቱ ያወቅነውን ምሥጢራችንን አንነግረውም፣ ቤታችን ይዘነው አንመጣም። የመጀመሪያው ትውውቅ ከስም ይጀምራል፣ ከስም ቀጥሉ ያሉ ነገሮችን ባለቤቱ ወዶ ፈቅዶ ካልናገር በቀር መጠየቅ ተገቢ አይደለም። የሚጠየቁና የማይጠየቁ ነገሮች አሉ። አዋቂ እንደሆነ ለመፈተን ሳይሆን ለመገንዘብ መጠየቅ መልካም ነው። ሊቅ ገንዘቡ ሳይሆን እውቀቱ ይዘረፋል። የሊቅን እውቀት ስንዘርፈው እርሱም ይደሰታል፣ እኛም አንኰነንም። የጋራ ስለሆነው ስለ አገር መጠየቅ፣ መጠያየቅ ተገቢ ነው። የሰውየውን የግል ኑሮ ግን መጠየቅ ተገቢ አይደለም። ምን ትሠራለህ? ማለት ተገቢ አይደለም:: ይህ ሰው ሥራ ፈትቶ ሊሆን ይችላልና ልንጎዳው እንችላለን። ትዳር አለህ? ልጆች አሉህ ? ብሎ መጠየቅም ያንን ሰው ማቁሰል ሊሆን ይችላል። ለምሰማው ነገር የእኔ ድርሻ ምንድነው ? ካልን መጠየቅን እንፈራለን። አሊያ እየቆነጠጡ ማስለቀስ ይሆንብናል።
ሰዎች እምነት ሲጥሉብን ምሥጢራቸውን ይነግሩናል፤ ወደ ቤታቸው ይወስዱናል፣ አደራ ይሰጡናል። ስሞት እንዲህ አድርግ ብለው ኑዛዜአቸውን እኛ ጋ ያስቀምጣሉ:: ምሥጢራቸውን ማወቅ በፈለግን ቍጥር እየሰወሩብን ይመጣሉ:: ሊጠሉንና ሊንቁን ይችላሉ። መንፈሳዊ አማካሪም ቢሆን እንደ መርማሪ ፖሊስ ማውጣጣት አይገባውም። ሰውዬው ውስጡ ተናገር ያለውን ብቻ እንዲናገር መፍቀድ አለበት። ያለ ፈቃዳቸው የሰዎችን ምሥጢር መፈልቀቅ ወንጀል ነው። ሰዎች ያለ መናገር መብት አላቸው:: ያለ ፈቃዳቸው የሚወጣ ምሥጢራቸው ታላቅ ኀዘን ውስጥ ሊከታቸው ይችላል፣ የሰውነት ክብራቸውም እንደ ተደፈረ ሊቆጥሩት ይችላሉ። የሰዎችን ምሥጢር ለማወቅ መፈለግ የመጀመሪያው በወሬ ጥማት የሚመጣ ነው። ሁለተኛው በውድድር ስሜት የሚመጣ ነው። ከእኔ በምን ይበልጣል? በማለት ያንን አውቆ ለመረጋጋት ነው፤ ግን ይህ አያረጋጋም:: ሦስተኛ የስላላ ሠራተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። አራተኛ መርማሪ ፖሊስ ሊሆኑ ይችላሉ:: አምስተኛ ሥራ ፈትነት ፣ የራስ ሲያር የሰውን ካላማሰልኩ የሚል ስሜት የወለደው ሊሆን ይችላል ።
ሰዎች እንደ አንተ ፣ አንተም እንደ ሰዎቹ ነህ :: የሌሎችን ምሥጢር ባትቆፍርም የሰዎች ኑሮ ተመሳሳይ ነው:: አንዳንዴ መሸከም የማትችለውን ነገር ልትሰማና ልታይ ትችላለህ። ዐርፎ መቀመጥ ከጉድ ያወጣል። አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳል / ያረዱታል የሚባለው ይደርስብሃል :: ያልነገሩህን ምሥጢር አትጠይቅ፣ የነገሩህን በልብህ ጠብቅ:: ሆድ ብዙ ይችላል ፣ የሰውን ምሥጢር እስከ ዕለተ ሞትህ ድረስ ጠብቀህ ኑር። የሰማኸውንም አልፈየድከውምና ሌላ ለመስማት አትሞክር። የሌሎችን ምሥጢር ስታወጣ በተመሥጦ የሚሰሙህ ሰዎች በልባቸው እየታዘቡህ ነው:: ምሥጢሩ ከወጣበት ፣ ምሥጢር ያወጣው ሰው ጽዩፍ ተደርጎ ይታያል። በእውነት የሰውን ብዙ ምሥጢር እያወቁ ዝም ያሉ ካህናትና አገልጋዮች መደነቅ ይገባቸዋል።
ከሰዎች ጋር ባለ ግንኙነት ወደው ፈቅደው ካልነገሩህ ምሥጢራቸውን ለወሬ ጥም ማርኪያ አትበርብር።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም.