መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -16

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -16

ጉዳትን ቀንስ

“እፍ ያነዳል፣ እፍ ያጠፋል” ይባላል። እሳቱን ለማቀጣጠልም ሆነ ለማጥፋት እፍ ያገለግላል ማለት ነው። መቼም ፈገግታ፣ መልካም ቃል፣ ቀረቤታ፣ ግልጽነት፣ መሥዋዕትነት ከሌለ ፍቅርን መመሥረት አይቻልም። ዘመናዊው እርሻ ላይ እያጨደ እዚያው የሚወቃ ማሽን እናያለን። ፍቅርም መሥዋዕትነትን እየከፈለ እዚያው ዋጋውን ይቀበላል። ነፍስ የተሰጣትን ተልእኮ ፈጽማለችና እፎይ ትላለች። አንዳንድ ጊዜ ውኃ ጠምቶን እንጠጣለን፣ ሌላ ጊዜ ስለ ቀዱልን እንጠጣለ። ታዲያ እንቢ  ያልነውን ውኃ ጨልጠን ስንጠጣ ፣ ደግሞም “ድገሙኝ”  ስንል እንዲህ እንደ ጠማኝ አላወቅሁም ነበር እንላለን። ፍቅርና መሥዋዕትነት አይለያዩም። ስንፈጽማቸው የዕረፍትና የመርካት ስሜት፣ የዘመናት እንቆቅልሽ መልስ ይሰማናል።

ለነፍሳችን ያላወቅንላትን ጥማት ስንፈጽመው ለካ የጎደለኝ ይህ ነበር እንላለን። ነፍሳችን የሕይወት ጥያቄ የሚያመጣባትን ምልክቶች ታስተናግዳለች። የነፍስ ጥያቄ ምን ያህል ተወደሃል ሳይሆን ምን ያህል ወደሃል ? የሚል ነው፤ ምን ያህል ሰብስበሃል ?  ሳይሆን ምን ያህል ሰጥተሃል ? የሚል ነው። እነዚህን ጥያቄዎች ለማዳመጥ መማር ያስፈልጋል። የነፍስ ጥያቄ ምልክቶች መበሳጨት፣ ለምን እንኖራለሁ ማለት፣ ሁሉን ሰው ለተበላሸው ነገር ተጠያቂ ማድረግ፣ አለመርካት … ናቸው። እነዚህን ምልክቶች ለማጥፋት የምንወስደው ሥጋዊ እርምጃ የበለጠ ጉዳተኛ ያደርገናል። ለምን እሰጣለሁ? ለምን ጊዜዬን አባክናለሁ? ለምን ዋጋ እከፍላለሁ? የሚሉ ንግግርችና የሕይወት ዘይቤዎች ለጊዜው ደስ ይላሉ። አጥሬ ጥብቅ ነው ፣ ዘመናዊ ሰው ነኝ ፣ ተምሬ እንዳልተማሩ ሰዎች ለምን እኖራለሁ ? የሚል የልዕልና ስሜት ያመጣሉ። ቆይቶ ግን ብቸኝነት፣ የሚደነግጥልን ሰው ማጣት፣ ውኃ የሚያቀብል ወዳጅ መቸገር፣ በሕመማችን ጠያቂ ማጣት ፣ በጉዳታችን የሚደርስልን ሰው መቸገር ይገጥመናል። የዚህን ጊዜ እንቅስቃሴ ብንጀምርም ሰዎች አያምኑንም። የማታ ወዳጅ ደግሞ በመፈራራት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ስላለው አያረካንም። በድሮ ስማችን፣ በፍቅር ጥሪ የሚጠራን አናገኝም፡ በገባንበት ቦታ ሁሉ አቶ እገሌና ወይዘሮ እገሌ ስንበል ኑሮአችን ሁሉ ቢሮ የሆነ ይመስለናል። ሰዎች ልጅ የሚፈልጉት አቅልሎ የሚጠራቸውና የሚያያቸው ስለሚፈልጉ ነው። ተራራ አድርገው በሳሉአቸው ቁጥር ጭንቀት ይሰማቸዋል። ሁሉም ነገር በሕግና በሥርዓት የተገነዘ ሆኖ ይሳልባቸዋል። ነጻነት አጥተው፣ ለመራመድም ፈሪ ይሆናሉ። ቀለል ያለ የኑሮ ዘይቤና ቀለል ያሉ ሰዎች ሕይወት ያቀላሉ። ደስታም ቅርብ የሚሆነው እነዚህ ሲገኙ ነው።

ፍቅር ያለ መሥዋዕትነት አትገኝም። ራስ ወዳድ ለሌሎች ዋጋ መክፈል አይችልም። ሌሎች ግን ዋጋ እንዲከፍሉለት ይፈልጋል። ኑና ላጫውታችሁ፣ ኑና ልቅሶ ልድረሳችሁ፣ ክፈሉና ላስደስታችሁ ስለሚል ፍቅር መሄድ ነውና አፍቃሪ መሆን አይችልም። ራስ ወዳድ ራሱን የደበቀበት ነገር ብዙ ነው። ሥራ የለኝም፣ ዘመድ የለኝም፣ ሰው አይረዳኝም በሚል መከላከያ ራሱን አጥሯል።

ፍቅር እፍ ይፈልጋል፣ እሳት ነውና መቀጣጠል አለበት። ደረቅ ከሰል ከፍም አጠገብ ሲቀመጥ መያያዝ ይጀምራል። እሳት ሌላውን የማቀጣጠል አቅም አለው ። ፍቅር ልምምድ ነው። ከአፍቃሪ ሰዎች ጋር ስንሆንም ድንጋይ ልባችን መለወጥ ይጀምራል።  መደዋወል የፍቅር የርቀት መጠበቂያ ነው። ፍቅር አበባ ነውና ያለ እንክብካቤ አያድግም፣ ጥላቻ አረም ነውና ባይንከባከቡትም ያድጋል። መጠያየቅ፣ መገናኘት፣ መጨዋወት መልካም ነው። ከዓይን የራቀ ከልብ የራቀ ይባላል። ልብ አድርጉ የምናወራው ስለ አጠቃላይ መንፈሳዊ ፍቅር ነው።

በግንኙነታችን ጉዳትን መቀነስ ተገቢ ነው ። ከሰዎች ጋር ወዳጅነት የምንመሠርተው ራሳችንን አጥተን ሳይሆን ራሳችንን ሆነን ነው ። ልጆችንም ስናሳድግ በጣም ተጎድተን መሆን የለበትም። ልጆቹ አድገው በጉዳታችን ሊያፍሩ ይችላሉ። ሊጦሩን ሲሰናዱ የከረመው ድካም ወደ ሞት ሊወስደን ይችላል። ያሯሯጡት ነገር ዕድሜ የለውም። ጊዜ ያልተሰጠበት ግንኙነት ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው። የዕድገት ሕግን የማይጠብቁ ምግቦች ሰውን ለሞት እያበቁ እንደሆነ ሁሉ ሂደት የሌለውም የወዳጅነት ጉዞም ቶሎ ሊጠናቀቅ ይችላል። ይልቁንም በአሁኑ ዘመን ገንዘብ በዙፋን ተቀምጦ የሚገዛበት፣ የስግብግቦች ዘመን ነው  ። ሰዎች እያንዳንዱን ግንኙነት ከጥቅም አንጻር ሊመዝኑት ይችላሉ። የላይ የላይ ግንኙነት ያለበት ዘመን ሁሉን ነገር ውሸት አድርጎ ሊያሳይ ይችላል ።

በግንኙነት ውስጥ ጉዳትን ለመቀነስ አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ።

የመጀመሪያው መዋደድ እንዳለ መጣላት ይኖራል። ፍቅር የኮንትራት ውል የለውም። ለዘለቄታው ጀምረነው መሐል ላይ ቢቆም ብዙ መደነቅ የለብንም። ምን ጊዜም ከእኛ ጋር ቀሪው ሕሊና ነውና ለሕሊና የሚበጀውን ማድረግ መልካም ነው። ሕሊና ከእኛ ጋር ቢቀርም ለእኛ አይወግንምና  እውነተኛውን ነገር ማድረግ ይገባል። ሰው ተለየኝ ብሎ ማበድ፣ ራስን መጉዳት፣አጥፍቶ መጥፋት ያለ መማር ፣ ያለ ማወቅ ፣ ይህችን ዓለም ያለ መገንዘብ ውጤት ነው። የሄደም ይመለሳልና ራሳችሁን አትጉዱ !

ሁለተኛ ለሰዎቹ ተጨማሪ ጭነት መስጠት የለብንም። የሰዎች አቅም የሚታወቀው ኃላፊነት በተሰጣቸው ጊዜ ነው። ለወዳጆች ኃላፊነት መስጠት መቀያየም ያስከትላል። ውክልና ሲሰጥም መሸጥ መለወጥ የሚልን ማስገባት ውጤቱ የሚጎዳ ነው።

ሦስተኛ ዕቅድ ሁለትን ሁልጊዜ ታሳቢ ማድረግ ጥሩ ነው። ይህ ባይሳካ የማደርገው ምንድነው? ማለት ያስፈልጋል። የተዘጋጁበት ችግር የሥራ ዕድል ነው። አንድ ቀን ችግር ሲከሰት መግቢያ እንዳይጠፋ ጠንቃቃ መሆን ይገባል። ከተቻለ ከወዳጅ ጋር አብሮ መነገድ ቢቀር ፣ ከሆነም በሕግና በንግድ መርሕ ማዋቀር መልካም ነው::

አራተኛ መለያየትን በጨዋ ደንብ ማስተናገድ ይቻላል። ተነጋግሮ ፣ ተማምኖ፣ ዳግም በሌላ ስፍራ በክፉ ላለመነሣሣት ተማምሎ መለያየት ይቻላል።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ