መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -2

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -2

የዳርቻዎች ፈጣሪ

የዓለምን ጥግ ፣ የፕላኔትን ቍጥር ሰው ገና አላወቀም ። እውቀቱም አጋንንታዊ ሆኖ የተራቀቀ መግደያ የሚሠራ ነው ። ዓለም ክብ ናት የሚለው ግራ ቢገባው ነው ። ሰው የማያውቀውን ዳርቻ እግዚአብሔር ያስተዳድራል ። የዳርቻዎች ዳርቻ እግዚአብሔር ነው ። የጥጎች ጥግ ፣ የምጥቀቶች ጉልላት ፣ የጥልቀቶች መሠረት እግዚአብሔር ነው ። በመታወቁ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ይባላል ፣ ባለመታወቁ ጨለማን መሰወሪያ አደረገ ተብሎለታል (መዝ. 17፡11)። የልብ ወሰን ፣ የመላእክት አእምሮ ከመታወቅ በላይ ነው ። ከዚያ ይልቅ እግዚአብሔር ሩቅ ነው ። ለውቅያኖስ ድንበር የሰጠ ፣ በለጥሁ ብሎ የብሱን እንዳይከድን የከለከለ ፣ በደመና ጀርባ ውኃ አሸክሞ ፍጥረቱን የሚያረካ ፣ በመግቦቱ ሁሉንም የሚያስታውስ እርሱ የዳርቻዎች ፈጣሪ ይባላል ። ዳርቻዎች ይረሳሉ ፣ ብዙ ጊዜም የጦርነት ቀጠና ይሆናሉ ፣ ሁሉን በመሐል እጁ የያዘው ግን የእኛ አምላክ እግዚአብሔር ነው ። ዳርቻው ሰሜን ወይም ምሥራቅ አይደለም ። ለዳርቻው ወሰን የለውም ። በሌለንበት አለ ፣ በሌለንበት ስፍራና ቦታ እኛን ወክሎ ይሠራል ። የታሰረው ወንድማችን ጋ እንልከዋለን ፣ ለሞተው ወገናችን ምሕረት ስጠው እንለዋለን ። ሰማይ መንበሩ ፣ ምድር የእጁ መከዳ መደገፊያው ናት ።

የሠራን ጌታ

ሠሪው እግዚአብሔር ፣ የአካላችን ባለቤት ፣ የህልውናችን መሠረት ፣ ከአባት ከእናታችን በፊት የሚያውቀን ፣ ዓለም ሳይፈጠር ያየን ፣ ዘመንና ስፍራ ወስኖ ያመጣን ፣ ለስሙ ምስክር አድርጎ ያስቀመጠን ፣ ባለቀው ነገር የሚጀምር ፣ ሠርኩን ማለዳ የሚያደርግ ፣ ከፊት እየቀደመ መንገዱን የሚያስተካክል ፣ ለቀኑ ሰው የሚያዘጋጅ ፣ አንዱ ሲከዳን ሺህ ወዳጅ የሚልክ ፣ ሳይቸግረው የሚሰጥ ፣ ሳይታዘብ የሚሸፍን ፣ በደስታችን ደስ የሚለው ፣ ተፈጥሮአችንንና ነፍሳችንን ለመጠበቅ ብሎ ትእዛዛትን የሰጠን ፣ ከአፈር አበጅቶ የክብር ዕቃ ያደረገን ፣ በደሙ ገዝቶ ዋጋችን የሆነልን እርሱ የሠራን ጌታ ይባላል ። እጅግ ሩቅ ነውና አንደርስበትም ፣ ቅርብነቱም ከእስትንፋሳችን ይልቅ ነውና መግለጥ አንችልም ። ያሰብነውን ከማሰባችን በፊት ያውቀዋል ፣ ለኃጢአት ቀጠሮ ይዘን ስንሄድም ከአደጋ ይጠብቀን ነበር ። የሠራን ፣ ሥራችንን የሚሠራልን እርሱ ነው ። እርሱ ቤትን ይሠራል ። ቤት ሕይወት ነው ፣ ቤት ትዳር ነው ፣ ቤት ጓዳ ነው ፣ ቤት ገመና ነው ፣ ቤት አገልግሎት ነው ፣ ቤት አገር ነው ። እግዚአብሔር ቤትን ይሠራል ። የሠራን ሲሠራን ይኖራል ። ታንጸን አናልቅም ፣ ተሠርተን አንፈጸምም ። የሕይወት መሐንዲስ እግዚአብሔር ዛሬም ይወቅረናል ፣ በቃሉ ያንጸናል ። አካላችን የእኛ መገልገያ ፣ የእርሱ ንብረት ነው ። ንብረቱን ለባለቤቱ መመለስ የሕሊና ፣ የሕግ ፣ የሞራል ግዳጅ ነው ። በመፈቃቀድ ላይ የሆነ እንጂ በግዳጅ የሆነ ሕብረት በዓለም ላይ የለም ። እግዚአብሔርም የሰውን ፈቃድ ለሕብረት ይፈልገዋል ። ተቀባዩን የሚያሳንስ ፣ ሰጪውን የሚያስነውር ፍቅር የሌለው ምጽዋት ነው ። እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ ወደደን ፣ ጸጋውን ሰጠን ፣ በመጨረሻም ራሱን ሰጠን ።

እግዚአብሔር ሆይ ዳርቻ ሳይኖርህ ዳርቻን ለፍጥረት ስለ ሰጠህ አንተን ሳመሰግን እኖራለሁ ! አለመቻሌን እወደዋለሁ ፣ ብችል ኖሮ ብዙ አጠፋለሁ ። በመቻልህ ግን ልቤን አሳርፋለሁ ። ተመስገን !
ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ