ጥንት የነበረ
የጥንቶች ጥንት እግዚአብሔር ነው ። ቀዳሚ ቢሉት ተከታይ ፣ መጀመሪያ ቢሉት መነሻ የለውም ። ከእርሱ በፊት የነበረ ፣ እርሱንም የሚተካ ማንም የለም ። ዋናው እርሱ ነው ፣ ምክትል የለውም ፤ በሌለበት ጊዜ የሚፈርም ተጠባባቂ አያሻውም ። የመጀመሪያዎች መጀመሪያ ፣ የመጨረሻዎችም ዳርቻ እርሱ ነው ። ሁሉ ይጀምራል ፣ ሁሉን ይፈጽማል ። መሠረት በእርሱ ይመሠረታል ፣ ጉልላትም በእርሱ ይደመደማል ። ለመጀመር የሚፈሩ ሕይወትን ያስጀመራቸውን አምላክ ሲያዩ ይበረታሉ ። ለመፈጸም መንገድ ላይ የቀሩ ሁሉን በውበት የሚደመድመውን ጌታ እያዩ ይደፍራሉ ። ቃላት ህውልናውን ፣ ባሕርዩን ፣ የተቀደሱት አካላቱን ፣ የአንድነቱን ስምምነት ሊገልጡት አይቻላቸውምና እንዲሁ ጥንት የነበረ እንላለን ። ያልኖረበት ዘመን ፣ የማይኖርበት ጊዜ የለም ። ዓለም ሕልም እልም ፣ ሰውም ታይቶ ጠፊ ፣ ፍጥረት እንደ አበባ አምሮ ረጋፊ ነው ። የሚረግፍ ከሆነ ለምን አማረ ? የሚያምርስ ከሆነ ለምን ረገፈ ? የእግዚአብሔር ጽኑነት ካልታሰበ ሕይወት ምንድነው ( የሚል ሙግት ነፍስን ያራቁታል ። ሁሉ በእርሱ ሆነ ። ሰው ቤት ቢሠራ ሊኖርበት ነው ፣ ራሱ እግዚአብሔር ግን መኖሪያችን ነውና ይህን ዓለም እኖርበት ብሎ አልሠራውም ። ሰው ሎሌ ቢያመጣ እንዲያግዘው ፣ ልጅ ቢወልድ እንዲጦረው ነው ። እመሰገን አይል ምስጉን ፣ እከብር አይል ክቡር የሆነው እግዚአብሔር መላእክትን እንዲረዱት ፣ ሰውን እንዲደግፈው አልፈጠረውም ። የምሰሶዎች ምሰሶ እርሱ ነው ። ቤቱን የተሸከመውን ምሰሶ የተሸከመው እግዚአብሔር ነው ። የአባወራው አባወራስ ራስ ፣ የንጉሡ ንጉሥ እግዚአብሔር ነው ። አባወራም ራስ ያምረዋል ፣ እማወራም የሚያስብላት ያምራታል ። እግዚአብሔር ግን የአባት አባት ፣ የእናትም እናት ነው ።
ጥንት የነበረ ፣ መስጠት የማይታክተው ፣ የሣንቲም ምጽዋት በሚቸግርበት ዓለም ሕይወትን የመጸወተን ፣ በአፉ እስትንፋስ አቁሞ የሚያስኬደን ፣ አለሁ ብሎ የማይፎክር አለሁልህ ብሎ የሚያረጋጋ ፣ አለኝ ብሎ የማይመካ ፣ ጠይቁ ብሎ የሚሰጥ ፣ ዘመኑ በአያት በቅድም አያቶቻችን ዘመን የማይለካ ድንቅ አምላክ ነው ። አንዱን ርስት ስንት ጊዜ ያወርሱታል ፣ ስንት ጊዜ ይወርሱታል ። መሬቱ አያልቅም ስንቱን ያፈራርቃል ። እግዚአብሔር ግን የማይደገም ጸጋና በረከት ይሰጣል ። የአባት እናት ውርስ ጊዜያዊ በመሆኑ ተጠቅመው ያስተላልፉታል ። እግዚአብሔር ዘላለማዊ ስጦታን ይሰጣልና በተራ አይበሉትም ። ሁሉም ከእጁ ይቀበላል ፣ የሻ ሁሉ ያገኛል እንጂ በእግዚአብሔር መንግሥት የበዪ ተመልካች የለም ። አዳም ሲበድል ነበረ ፣ ዛሬም ጸሎታችንን ይሰማል ። ሊያድነን ደጃፋችን ላይ ቆሞ ያንኳኳል ። አንኳኩተን የሚከፍቱ ሐኪሞች በሌሉበት ዓለም ላይ ፈዋሹ በደጅ ቆሟል ። አንድ ጊዜ ለዘላለም ውብ ሥራ ይሠራል እንጂ ለሙከራ ብሎ የሚያበጀው ምንም ነገር የለም ። ለክብር እንጂ ለመጫወቻ የተፈጠረ አንድም ፍጥረት የለም ፣ አንዱን ነዋሪ ሌላውን አኗኗሪ አድርጎ አልፈጠረውም ።
የትላንት ታሪክ የሌለው ሰው ማንም የለም ። የትላንቱ ስህተት ምነው ባልተፈጸመ ብሎ የሚከጅል ብዙ ነው ። ጥንት የነበረው ትላንትን ይክሳል ። የሚኖረው ጌታ ነገን ያበጀዋል ። ዘመን ሲረዝም ጉልበት ይከዳል ፣ መልክ ይረግፋል ፣ እውቀት ይደበዝዛል ፣ ተቀባይነት ይቀንሳል ፣ እንቅልፍ ይሳሳል ፣ ምግብ ቢበሉት በሽታ ይሆናል ፣ ልጅም ይሰለቻል ። ዘመናት ያልተጫኑት ዘመናትን ግን በእጁ ላይ የሚቀምር ፣ ዘመንን የሚያስረጅ ዘመን የማያደክመው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። በእጅ ላይ እንዳለ ሰዓት ሺህ ዘመንን አንድ ደቂቃ ብሎ ይጠራዋል ። እርሱ ብቻ የዘመን ምስክር ነው ። የሠራነው ሥራ ይረሳል ፣ ልጆቻችን ያደረግንላቸውን ሳይሆን ቸግሮን አንድ ቀን የከለከልናቸውን ሲያስቡ ይኖራሉ ። እግዚአብሔር ግን ያደረግነውን በምን ልብ እንዳደረግነው ፣ የሠራነውን በምን ዓይነት ትግል እንደ ሠራነው ያውቃል ። ምስክር እያጡ የሚጨነቁ ብዙዎች ናቸው ፣ የእኔ ሐቅ ይውጣ የሚሉ የሕሊና ታጋዮች አያሌ ናቸው ። ሰው የሰውን ሐቅ ይሸፍናል እንጂ አያወጣም ። እግዚአብሔር ግን የዘመን ምስክር ነው ። ሰው ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ በጎነት ቢኖረን የሚያየው አንድ እጁን ጉድለት ነው ። እግዚአብሔር ግን ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ ተሳስተን አንድ እጅ መልካም ነገራችንን ያያል ።
ጥንት የነበረ ወደፊትም የሚኖር እርሱ እግዚአብሔር ነው ።
ምን ይባላል ? ተመስገን ብቻ ነው !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም.