ከባቴ አበሳ (ጉድን ሸፋኝ )
በደልን ሰዋሪ፣ የሌላውን ሸክም ተሸካሚ፣ ያየውን ሁሉ የማይናገር፣ የተነገረውን ክፉ ደግሞ የማያወራ ፣ የአምላክን ጠባይ የያዘ፣ ራሱን በቅጡ የሚያውቅ፣ በወደቀ ሰው የማይሳለቅ ፣ እርሱን ጣሉት ሳይሆን እንደ ነቢዩ ዮናስ እኔን ጣሉኝ የሚል ነው። ከእግዚአብሔር የሙገሳ ስሞች አንዱ ከባቴ አበሳ – በደልን የሚሸፍን የሚለው ዝነኛ ነው።
የአማርኛው ጉድ በፈረንጅ ጥሩ(good) ማለት ነው። በዚህ ዘመን የሰውን ጉድ የምናወራው እንደ እንግሊዝኛው ጉድ ነው ። የትልቅ ሰው ልኩ የሚያውቀውን ሁሉ አለመናገሩ ነው። እንኳን የሰውን ጉድለት ይቅርና የሰውን መልካምነትም ሁሉን መናገር አይገባም። አንድን ሰው በጣም እወደዋለሁ እያሉ ለሁሉ ማውራት ተገቢ አይደለም። ቅንዓት ያደረባቸው ሰዎች ያንን ሰው አጥምደው በመያዝ በእኛ ላይ ጠላት አድርገው ያነሣሡታል። አሊያም የዚያን ሰው ሐሜት በማምጣት በዱቄቱ ላይ አሸዋ፣ በማሩ ላይ እሬት ይጨምሩበታል። መውደዳችንን ለባለቤቱ ብቻ መንገር ይገባል። ሰዎች በእነርሱ ልክ ያንን ሰው እንደምንወደው ሲያውቁ ይረጋጋሉ። ቅዱስ ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍን ከወንድሞቹ በላይ ስለሚወደው ዮሴፍ ጥላቻን አተረፈ። አልበደለም፣ ግን ለምን ተወደድህ የሚል ጠላት መጣበት። ሽማግሌው አባት ወዶት ጠላት የሆኑት አሥር ወንድሞቹ ናቸው። ያዕቆብ አንዲት ውብ ቀሚስ ቢሸልመው ሕይወቱን ለመንጠቅ ወንድሞቹ ማሴር ጀመሩ። ዮሴፍ ከተሸለመው ቀሚስ በላይ የሆነ መከራ መጣበት። ከልጆችም አንዱን በተለየ ሁኔት መውድድ ያንን ልጅ የ ጠላት ዓይን ውስጥ መክተት ወይም ለዚያ ልጅ የወንድም የእኅት ጠላት መግዛት ነው። እንኳን የሰውን ኃጢአት ጽድቁንም ስናወራ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እገሌ ይህን ሰጠኝ ብለን ስናወራ ለእኔ ለምን አልሰጠኝም? የሚል ጠላት እናስነሣበታለን:: ለራሳችንም ዳግም እንዳናገኝ በገዛ ምላሳችን ጠላት እናመርታለን። እነዚያ ጠላቶች ሄደው ለእገሌ ለምን ሰጠኸው ? ሙሉ አካል አለው፣ አንተ የተቸገርህ ጊዜ መቼ እየህ? ደግሞስ ይህና ይህ አለው አይደለም ወይ ? በማለት ደጉን ሰውና ወዳጃችንን ያከፉታል። ክፉ ሆኖ የተፈጠረ የለም፣ ክፉዎችን የምንፈጥር እኛ ነን። ጌታችን ምጽዋታችንን በስውር እንድናደርግ ያዘዘን ፣ ምጽዋታችንን ሚስትም ባልም ማወቅ የሌለባቸው ከዚህ ጥፋት ሊጠብቀን ነው (ማቴ. 6፥ 3-4 ) ። ጌታችን ስለ ራሱና ስለ አባቱ ነገረን እንጂ ሁሉንም አልነገረንም። ሁሉን ቢነግረን መሸከም አንችልም። ነገረ እግዚአብሔር መልካም ብቻ ሳይሆን ሕይወትም ነው። በአቅም እንጂ ሁሉም አይነገርም። ሰዎችን ስናውቃቸው ያወቅነው ጥቂቱን ነው ፣ የማናውቀው ነገራቸው ይበዛል። ስለዚህ አወቅሁሽ ናቅሁሽን ማራቅ ይገባናል።
ሰዎች ከምናውቀው ስህተታቸው ጀርባ የማናውቀው ጽድቅ አላቸው። እኛ ስለ ተገለጠው ኃጢአታቸው ስንከሳቸው የማናውቀው የንስሐና የእንባ ሕይወት አላቸው። እግዚአብሔር በምድር ፣ ክርስቶስ በአካል የሚባል ሰው አለ። እርሱም፦ የሰውን ኃጢአት የሚሸፍን ነው። ተሠርቶ ያላለቀ ሕንፃ ሸፍነው ይሠሩታል። ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል ተብሏል( 1ጴጥ . 4፥ 8 ) የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈን ውስጣችን በእግዚአብሔር ፍቅር መሞላት አለበት። በጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር እንኳ የማይታይ የሰውን ጉድ የሕዝብ ማጫወቻ አሻንጉሊት ማድረግ ክርስቲያን ያለ መሆን ውጤት ነው። ፍቅር ሸፍኖ ያስቀምጣል ማለት ሳይሆን ጋርዶ ይሠራል ማለት ነው። ሕንፃ ሥላሴ የሆነው ሰው ተሠርቶ ያላለቀ ነውና። አንድን ሰው ስንሸፍንለት ቢበድል እንኳ በፍርሃት እንጂ በድፍረት አይደለም። ኃጢአቱ ከተገለጠ ግን ነጻነት አግኝቶ ተጠቃሎ ይገባል። ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስ ናትና ኃጢአትን ትሸፍናለች።
እግዚአብሔር ሊያወርሰን የሚፈልገው ጠባዩ ከባቴ አበሳ መሆንን ነው። ልብስም ይከድናል፣ ቤትም ይሸፍናል። ትዳርም ገመና ነው፣ የሥነ ልቡና አማካሪም በመሐላ የሰውን ምሥጢር ጠባቂ ነው። ክርስቲያን ከእነዚህ ካነሰ ክርስቲያንነቱ ምን ላይ ነው?
እግዚአብሔር ከባቴ አበሳ – ጉድን ሸፋኝ ነው። እንደ እርሱ የሚያውቅ እንደ እርሱ የሚሸፍን የለም። በዚህ ዘመን የሰውን ጉድ እንደ ጥሩ ዜና እናወራለን። ስለማናውቀው ሰው የማውራትና የማስተጋባት ድፍረት አለን። እኔን ይመለከተኛል ወይ ብለን ራሳችንን አንጠይቅም። የምናወራበት ዓላማ ግልጽ አይደለም። ቆሽሾ ማቆሸሽ እንወዳለን። የሰውን አእምሮ በመጥፎ ወሬ እንበክላለን። እንደ ዝንብ ቆሻሻ ቦታ እንጂ ንጹሕ ቦታ አንውልም። የሌላውን ጉድ ማውራት የራስን ጉድ ማስወገድ አይደለም። በሸክም ላይ ሸክም መጨመር ነው። ራሱን በትክክል የሚያውቅ ስለሌላው አያወራም። የራሱን ኑሮ የሚኖር ጊዜ ተርፎት ስለሌላው አያወራም። ደግሞም ተሸፍኖለት የሚኖር የሌላውን ስህተት ካልገለጥሁ አይልም። በማን እንደ ቆመ የሚያውቅ በሌላው ውድቀት አይሳለቅም። እኔን አድነኝ ብሎ ይጸልያል። ከፍተኛ የአእምሮ ክስ ያለበት ሰው ስለሌላው ካላወራ ስቃዩ አይታገሥለትም። ኃጢአቱ ያስጨነቀው ዓለም ወደ እኛ የሚመጣው ሸፋኝ ስንሆን ነው። ዓለማውያን እንኳ አብረው የሠሩትን አያወሩም። ፖለቲከኞች የአሳብ ክርክር እንጂ የሰውን ግላዊ ማንነት የማጥቃት አካሄድ አይታይባቸውም። የቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ለምሕረት የተከፈተ ነውና ሰዎችን ለንስሐ መጋበዝ ይገባናል። የንስሐ ሰባኪ እኔም ካንተ የባስሁ ኃጢአተኛ ነኝ፣ እኔን የተቀበለ ጌታ አንተንማ በደንብ ይቀበልሃል የሚል ነው። የእግዚአብሔር ሰው ይገልጣል እንጂ አያጋልጥም። ካህንና ፖሊስ ግብሩ ለየራስ!
ስለ ሰዎች ኃጢአት ለመናገር ውክልና የሰጠን ማንም የለም። የምናወራው ሰውዬው እስካፈረ ድረስ ብቻ ነው። ምን አገባችሁ ? ሲለን ዘላለማዊ ፀጥታና ሐፍረት ውስጥ እንገባለን። እንኳን ለማዋረድ ለመምከርም የሰውዬውን ፈቃድ ማግኘት አለብን። ባለቤቱ ክርስቶስ እንኳ ልትድን ትወዳለህን ? የሚል አስፈቅዶ የሚያድን ነው። ሰው ስለ ሰው ቢዚ የሆነበት ብቸኛ አገር የእኛ አገር ነው። በጨዋ ቤት ያደገ አየሁ አላየሁም፣ ሰማሁ አልሰማሁም የሚል ነው። ነገሩ ጥሩ ሆኖ እንኳ ባለቤቱ እንዲነገርበት ካልፈለገ መሰወር ተገቢ ነው። አባት ክፉ ቢሆን ለልጁ አእምሮ ደግ ደጉን መንገር፣ እናት ክፉ ብትሆን ለልጇ ግን ደግነቷን ማውራት ትውልድን ማዳን ነው።
እግዚአብሔር ሸፋኝ ነው። እናት ሸፋኝ ናት። በመሸፈኗ ሕግ አፍራሽ የሚላት የለም ። ሰይጣን ከሳሽ ነው ፤ ከሳሽ ትልቁ ተከሳሽ ነው። ሰይጣን ትልቅ ተከሳሽ ሳለ ይከሳል። እግዚአብሔር ግን ይሸፍናል። ተከሳሹ ከሳሽ!
አበሳችንን ስለሽፈንህልን ተመስገን ! ቆመን የምንሄደው በደላችንን ስለ ከደንህልን ነው።
ይቀጥላል
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም .