የዳዊት ጉልበት
እስራኤል ከጠላት ከሚወረወሩ ፍላፃዎች ለመዳን የተለያዩ የማምከኛ መሣሪያዎች እንዳሉአት ይናገራል። ከእነዚያም ውስጥ አንዱ “የዳዊት ወንጭፍ” ተብሎ ይጠራል። በዝቅተኛ ከፍታ ላይ ያሉ ሚሳኤሎችን ለመከላከል የሚውለው መሣሪያ ዳዊት በጎቹን በጠበቀበት፣ ጎልያድን በጣለበት ስም መሰየሙ ይገርማል። የዳዊት የወንጭፍ ኃይል እምነት ነበረ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ተራራን ትደለድላለች ፣ በእምነት የተወረወረች የዳዊት ወንጭፍም ትልቁን ጎልያድ ጥላለች። በትንሽ እምነት ፊት ትልቅ ችግር መቆም አይችልም። የሚያሳስበው የችግሩ ትልቅነት ሳይሆን የእኛ እምነት ማጣት ነው። ወንጭፍ ደግሞም የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት የለንም። እምነት አልባ ግን አይደለንም። አለማመኔን እርዳው ማለትም እምነት ነውና።
ነቢዩ ዳዊት:- “አቤቱ ጉልበቴ ሆይ እወድድሃለሁ” አለ። የዳዊት ጉልበት እግዚአብሔር ነበረ። እህል የሰውን ጉልበት ያጠነክራል። እህል ቢበሉት ጉልበት ነው፣ ቢያዩት ቢተርኩት ግን ጉልበት አይሆንም። ነቢዩ በሌላ ስፍራ እግዚአብሔርን ቅመሱት ይላል። እግዚአብሔርን የበላ የጠጣ ነውና ጉልበት ሆነለት። መብል ከሰውነት ይዋሐዳል። ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ኅብረትና ጥምረት ያለው ሰው እንደ ካሌብ በ80 ዓመቱም ጉልበታም ነው። በዳግማዊ ምኒልክ ጋሻ ላይ፦ “የምኒልክ ኃይል እግዚአብሔር ነው” የሚል ጽሑፍ ተቀርፆነት ነበር። ዳዊት ያለ ስንቅና ትጥቅ ተደራጅቶ የመጣውን ዓለም አቀፍ የጦር ሰው ጎልያድን አሸነፈው። ዳዊት እረኛ ነው፣ ጎልያድ የጦር ጀነራል ነው። ዳዊት በቤተሰቦቹም የተናቀ ነው፣ ጎልያድ ንጉሥ ሳኦል ሳይቀር የሚፈራው ነው ። ዳዊት ምን ልትሠራ እዚህ መጣህ? ብለው ወንድሞቹ የተቆጡት ነው፣ ጎልያድ ግን እየተዘፈነለት የወጣ ወራሪ ነው። ምኒልክም ከጣሊያን አንጻር ሲታዩ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ መሪ ናቸው። ይዘው የዘመቱት ገበሬውን ሲሆን ጣልያን ግን የመጣው የሰለጠነ ሠራዊት ይዞ ነው። ዳዊት ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ወንጭፉን ወረወረ፤ ምኒልክም ጦርነት ተጀምሮ ቅዳሴ እስኪፈጸም ቆመዋል። ጦርነቱም ያለቀው በጥቂት ጊዜ ነው። የዳዊት ወንጭፍ ዛሬም ትጠራለች፣ የአድዋ ድልም የጭቁን ሕዝቦች ድል ሆኖ ሲነገር ይኖራል። ያለ ኃይል መመጣጠን ድል እንዳለ፣ ድልም ስጦታ እንደሆነ የዳዊት ወንጭፍ ሲናገር ይኖራል ፣ አፍሪካውያንና የእስያ ሕዝቦች ሌሎች ጭቁኖችም ቅኝ ገዥዎችን ማሸነፍ እንደሚቻል ልብ ያገኙት ከአድዋ ድል ነው። የአድዋ ድል የቅኝ ገዥዎች ተስፋቸው የተቀበረበት ነው። የአድዋ ድል ለእኛ ኩራት ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን በምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ የገባችበት ነው። ጣጣው እስካሁን ይከተለናል። ከድል ማግሥት ያሉ ነውጦችን ማሰብ ያስፈልጋል። የዚህ ሁሉ ምሥጢሩ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን ማመን ነዉ። እግዚአብሔር የዳዊት ጉልበት ነው፤ ወንጭፉ ጫፍ ላይ የተቀመጠች የጌታ ጣት ናት።
ለመነሣት፣ ለመራመድ፣ ለመሸከም፣ ተራራ ለመውጣት፣ ለመኖር ፣ ለማፍቀር ፣ ይቅር ለማለት፣ — ጉልበት ያስፈልጋል። የመንፈስ ጉልበት ከሌለ ሥጋ ብቻውን መኖር አይችልም። በግድ የሚኖር፣ በግድ የሚስቅ፣ በግድ ይቅርታ የሚያደርግ፣ በግድ የሚሸከም ብዙ ሰው አለ። ይህ ሰው ግን ከነገ እየተበደረ የሚኖር ነው። ለመነሣት ጉልበት ያስፈልጋል። ብዙ ሰው በድንዛዜ ውስጥ ነው ያለው። ድንዛዜ ያለበትን ሁኔታ ለምዶ መቅረት ነው። አንድ ነገር ላይ አፍጥጠው ሲቀሩ አዚም፣ ተቀምጠው ሲቀሩ ድንዛዜ ይባላል:: አንድ ሰው ላይ ፈዞ መቅረት ፣ ከሄደ ሰው ጋር ራስን አቆራኝቶ መቅረት ተገቢ አይደለም። የጥንት የአገራችን ፍርድ ሌባው ተቆራኝቶ ከተሰራቂው ጋር ይሄድ ነበር። ተሰራቂው ከሄደበት ሌላው አብሮ ይሄድ ነበር። ያ ልማድ ወደ ውስጣችን ገብቶ ቅንነትን ከሰረቁን ሰዎች ጋር ተቆራኝተን እንኖራለን። የጠላንን በምናስብበት መጠን የወደደንን ጌታ ማሰብ አልቻልንም። ዐረቦች:- “ሲመርቁ እንደ ጠላት ያስተሳስባችሁ” ይላሉ። የልጅነት እጮኛዬ ከድቶኛል ሌላ ሰው አላይም ማለት ተገቢ አይደለም። ጌታም ጴጥሮስና ይሁዳ ነበሩት ። ሁለቱም ግን ይበድላሉ። አንዱ ይመለሳ፣ ሌላው በበደሉ ይጸናል። አንድ ቦታ ላይ ደንዝዘው የሚቀሩ፣ ዕድገታቸውን የቀበሩ ብዙዎች ናቸው። እግዚኣብሔር ገፊ የሚያስነሣብን ከድንዛዜ ሊያድንን ነው ። ያለ ገፊ ማደግ የለም። ገፊዎች ሲገፉን ቦታህ እዚህ አይደለም፣ እልፍ በል፣ በደረጃህ ዋል እያሉን ነው። ስለ ክፉ አከራዮቻችን፣ ስላሳደዱን ሰዎች እግዚአብሔር ይመስገን። እግዚአብሔር ሁሉን ወደ በጎ መለወጥ ይችላል። ለመነሣት ጉልበት ይፈልጋል። የመነሣት ጉልበታችን እግዚአብሔር ነው።
ወላድ በድባብ ትሂድ ይባላል። ድባብ ለትልቅ ሰው፣ ለታቦት የሚዘረጋ የክብር ጥላ ነው። የማይታጠፍ ጥላ ነው። ወላድ ትክበር ማለት ነው። እግዚአብሔር ብዙ ሰው አለው። ስለሄደው ሳይሆን ስለሚመጣው ማሰብ ትልቅነት ነው ። የተሻለ ነገር ከወደፊት አለ ። መሞከርን መፍራት አይገባም። የሚያፈስ ጣራ ያለበት ቤት የሚቆይ ተከራይ የተሻለ መኖሩን ስላላወቀ ፣ ከለመደው መውጣትን ስለ ፈራ ነው። የአገሬን ሰው አስሮ የያዘው “ካልለመዱት መንፈስ ቅዱስ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” የሚል አጉል ብሂል ነው። ወገኔ እገሌ ቢሄድ የተሻለ ማን አለ? ይላል። እገሌ እኮ የመጣው እገሌ ሄዶ ነው። ማን ይመጣል ?ብሎ ማሰብ ራስን መናቅ፣ በእግዚአብሔር አለማመን፣ የለውጥ ሕግን አለማወቅ ነው።
እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል፣
ድሀ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል ::
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም