መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -10

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -10

የዳዊት ጉልበት (2)

“አቤቱ፥ ጉልበቴ ሆይ እወድድሃለሁ” (መዝ.17:1)

ለመራመድ ጉልበት ይፈልጋል። በሕፃንነት መገልበጥ፣ መቀመጥ፣ መዳህ ፣ መራመድ የሕፃኑ ናፍቆት፣ የወላጆቹ ጉጉት ነው። መራመዱ የመጀመሪያው ዕቃ ይዞ፣ በሰው እጅ ተይዞ ነው። ሁለተኛው ራስን ችሎ ነው ። መገልበጥ ዕድገት መሆኑ ይገርማል። በአንድ አቅጣጫ ብቻ መተኛት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ወላጆች ሕፃኑን በየሰዓቱ ያገላብጡታል። ሕፃኑ ግን ማደግ ሲጀምር ራሱ መገልበጥ ይጀምራል። በአንድ ጎን ብቻ ተኝቶ ከመደንዘዝና ከመላላጥ ራሱን ይጠብቃል። በአንድ አቅጣጫ ብቻ ማሰብ፣ የነገሮችን ዙሪያ ገባ ማጥናት አለመቻል አለማደግ ነው። የአንዳንድ ሰዎች ጉዞ እንደ ጋሪ ፈረስ አንድ አቅጣጫ ብቻ በማየት ነው። ግራና ቀኙን፣ ዘመኑንና የሰዎችን ሁኔታ አይገነዘቡም። በዚህ ምክንያት ደንዝዘው ፣ በአንድ ቦታ ረግተው ይቀራሉ። በአንድ ቦታ ላይ ብዙ ዘመን መቀመጣቸው ጽናት መስሎ ሊሰማቸው ይችላል፣ ይህ ግን  መደንዘዝ ለመነሣት ጉልበት ማጣት ሊሆን ይችላል።

ይህ ብቻ አይደለም ለመላጥና ለመቁሰል ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። አንዳንድ ፈተናዎችን ዘወር በማለት እናሸንፋቸዋለን። ውስጥን መላጥና ማቁሰል አንዳች ጠቀሜታ የለውም:: ሁኔታዎቹን፣ ሰዎቹን፣ ቦታዎቹን እስቲ እንቀይራቸው:: መጋፈጥ ጥሩ ነው፣ ለሁሉም ነገር እኩል ዋጋ መክፈል ግን ሞኝነት ነው ። ዘወር ስንል የተሻለ እናያለን። ምድር ሰፊ ናት እንደተባለ ጠብና ክርክር መቀነስ እንችላለን::

ሰዎች አልተው ብለውኝ እቃጠላለሁ እንላለን። እውነቱ ግን አልተው ያልናቸው እኛው ነን ::  ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ግብግብ ማድረግ ጀግንነት ይመስለናል፣ በራሳችን እንጂ በሰዎች ላይ የምንወስነው ጥቅም የለውምና ተስፋ እንቆርጣለን። ለማንም ሰው ምግብን እናቀርባለን እንጂ አንበላለትም። እኛ ስለሞትንላቸው የማይድኑ፣ በገዛ ውሳኔአቸው ብቻ የሚድኑ ሰዎች አሉ። የእኛ ታማሚ፣  ብስጩና እንቅልፍ የለሸ መሆን ለሰይጣን ፈተና የመጋለጣችን ምልክት ነው።  የራሳችንም ሰዎች ቢሆኑ የምርጫቸውን ውጤት መቀበል እንዳለባቸው ማመን አለብን። ሕይወት የመዝራትና የማጨድ እውነት ናትና የዘሩትን ያጭዳሉ።

ከራስ ወዳዶች ፣ ትላንትን  ማሰብ ከማይችሉ ይሉኝታ ቢሶች ፣ ቅናት ካሰከራቸው ሰዎች ጋር መኖር ዕድሜን ያሳጥራል። ድል በመጋጠም ብቻ ሳይሆን ዘወር በማለትም ነው። ጌታችን ወደ ግብጽ መሰደዱ ፣ ሊገድሉት ሲሉ ብዙ ጊዜ መሰወሩ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ነው። ሞት የማይቀር ቢሆንም ያለ ጊዜው መሞት ግን ተገቢ አይደለም።

ካወቅነው የተሻለ እውቀት አለ። ካወቅሁት ውጭ  ማወቅ አልፈልግም ማለት የዕድገት ሕግን አለመጠበቅ ነው::  ከትላንቱ በብዙ ነገር አድገናል። ዛሬ የተሰጠችን እንደ ትላንቱ ለማሰብና ለመኖር አይደለም። ትላንት ትክክል ያልነው ትክክል ካልሆነ ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። መኖር ለመማር ነውና ። መማርም ያላወቅነውን ለማወቅ ፣ ትክክለኛ ያልሆነውን እውቀታችንን ለማረም ነው። የተዘራ ነገር ሁሉ መታረም አለበት። በምድር ላይ የተበተንን የእግዚአብሔር ዘር ወይም ተክል ነን። እውቀታችንን ካላሳደግንና ትክክለኛ ያልሆነውን እውቀታችንን ካላረምን መላጥና መቁሰል ኑሮአችን ይሆናል። የማያስፈልጉ እውቀቶች ስለ ሰዎች ያሉን መረጃዎች ከንቱ ናቸው።

መዳህ የዕድገት አካል ነው። የሰው ልጅ በአራት እግር ድሆ ፣ በሁለት እግር ተራምዶ፣ በሦስት እግር ሽምግልናውን ገፍቶ አርባ እግር ተሸክሞት  ወደ መቃብር ይወርዳል። መዳህ በመገልበጥና በመራመድ መካከል
ያለ ድልድይ ነው። መዳህ ሰው እንደ እንስሳ የሚራመድበት ነው ፣ እንስሳዊ ጠባይ አለውና ። እንስሳት በተወለዱ ቀን መራመድ ይጀምራሉ:: ቶሎ ስለሚሞቱ ወይም ፍጻሜአቸው ምድር ላይ ብቻ ስለሆነ ቶሎ ቶሎ ያከናውናሉ ። ሰው ግን አገሩ ሩቅ ነውና ቀስ እያለ ያድጋል። ሁሉን ማወቅና ምንም አለማወቅ  ሁለቱም ክልክል ናቸው ።

መራመድ መጀመሪያ ላይ ዕቃ ይዞ ወይም በሰው ተይዞ ነው። በብዙ ነገር ራስን ችሎ መቆም ይገባል። ወንበር ይዞ ዕቃ ተደግፎ መራመድ በቂ አይደለም፡ ብዙ ሰው አላደገምና ወንበር ተደግፎ ይጓዛል። የነገሠ አካል በመጣ ቊጥር ጥገኛ ሆኖ ይራመዳል። ሁሉም ርእዮት ዓለም ይስማማዋል፣ ለሰዎች ለመዝፈን የተፈጠረ መስሎት  ራሱ ይታየዋል። ለራሱ ክብር የለውም፣ ሆድ አደር ነው። ሰርቆ አደሮች ሲያካብቱ እርሱ እንደ ውሻ በሆድ ደሞዝ ይገዛል። ገሎ አደሮች የላኛው ማማ ላይ  ሲወጡ እርሱ በርቱ እያለ ወንበሩን ይደገፋል። ሰው ይዞ ሕፃኑ እንደሚራመድ ሰው ይናገርልኝ፣ ሰው  ይሥራልኝ፣ ሰው  አብሮኝ ይሄድ ፣ ሰዉ ይወስንልኝ እያሉ በውክልና ይህችን ዓለም የሚገናኙ አሉ። ማደግ ግን በኃላፊ ሹም፣ በጥሎ ሂያጁ ሰው ሳይታመኑ መድኃኔ ዓለምን ምርኩዝ አድርጎ መሰማራት ነው ። ለመራመድ ጉልበት ያስፈልጋል። ያ ጉልበት በነቢዩ በዳዊት ተዘምሮለታል፦ “አቤቱ ፥ጉልበቴ  ሆይ እወድድሃለሁ።”

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ