ሕይወት የመለኮት ዕቅድ ናት ። መነሻና ግብም አላት ። የሁሉም ሰው መነሻ እግዚአብሔር ነው ፣ መድረሻው ግን በግለሰቡ ምርጫ የተወሰነ ነው ። መሞት የአንድ ቀን ጉዳይ ሊሆን ይችላል ፣ ሞቶ መኖር ግን ስቃዩ ብዙ ነው ። በምድር ላይ ያለ ሰው መላ/መፍትሔ አለው ፣ የሞተም በጣም የተጎዳ አይደለም ። ከሰዎች ጋር ባለን መስተጋብር እነዚህ ዐሥራ አምስት መመሪያዎች አስፈላጊ ናቸውና ብትጠቀሙአቸው ከፍ ያደርጉአችኋል ።
ይሉኝታን አርቁ
በሰላም የሚሄድ እግር የሚደናቀፈው ሰው እያየኝ ነው ብሎ ሲሰጋ ነው ። ለሕሊና የሚመቸውን ፣ እግዚአብሔርን የሚያስደስተውን ተናገሩ እንጂ ሳትናገሩ መጨነቅ ፣ ተናግራችሁ መጠበብ አይገባም ። ይሉኝታ አስፈላጊ ነው ፣ የእግዚአብሔር ቃል የሚመራውን ሰው ግን ይሉኝታ አስፈላጊው አይደለም ። ሐዲስ ኪዳን ማድረግ ሳይሆን መሆን ነው ። ማድረግ ሥራ ነው ፣ መሆን ከተለወጠ ማንነት የሚወጣ ነው ። ሰዎች ምንም ብትጨነቁ አንድ ስም ይሰጡአችኋል ። ለሕሊና መኖር ፣ ራስን መሆን ግን ያሳርፋችኋል ። በይሉኝታ ታስራችሁ እንዳትኖሩ የመግቢያው በር ላይ ቆማችሁ መውጫውንም ተመልከቱ ።
የተሻለ ነገር አትጠብቁ
ለወዳጃችሁ የማትደውሉት የተሻለ ሰዓት ስትፈልጉ ነው ። ለሰከንድ አለሁ ብላችሁ ስልካችሁን ዝጉ ። የተሻለ የምትሉት ጊዜ ሳይመጣ ዕድሜ ሊያልቅ ፣ ወዳጃችሁም ሊያልፍ ይችላል ። ደኅና ነገር ለማድረግ ብላችሁ አትዘግዩ ፣ ወዳጃችሁን የሚታደገው ጥቂት ስጦታ ሊሆን ይችላልና ድረሱለት ። ባላችሁ ነገር ላይ ወስኑ እንጂ የሌላችሁን አትጠብቁ ።
ፍቅርን ተንከባከቡት
ፍቅር አበባ ነው ፣ እንክብካቤ ይፈልጋል ። ባትንከባከቡትም አረም ያድጋል ። መልካም ነገር ሁሉ ዋጋ ፣ ክብር ፣ ጥንቃቄ ፣ ጥበቃ ፣ ቶሎ መድረስን ይፈልጋል ። ፍቅርን የምንከባከበው ጊዜ በመስጠት ነው ። ከሚያጸጽቱ ነገሮች አንዱ ለቤተሰብና ለልጆች እንዲሁም ለወዳጆች ጊዜ ሳይሰጡ የነገሮች መለዋወጥ ነው ።
አጨራረሳችሁን ጥሩ አድርጉት
ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና ኮንዲሚኒየም የሚሠራበት ብረቱም ሲሚንቶውም ያው ነው ። አንዳንዴ ቀለሙም ያው ነው ። አጨራረሱ ግን ልዩነት ያመጣል ። በአገራችን ትልቁ ችግር የአጨራረስ ነው ። የአጨራረስ ችግር የእውቀት ማነስ ፣ የዕይታ ጉድለት ፣ እልህ ፣ ወገንን አለመውደድ ፣ ሌላ ሲደሰት አለመደሰት አሊያም ሌብነት የሚያመጣው ነው ። ባለትዳር ሲለያይ እንደ ጠላት ይተያያል ፣ ይህ የእኛ አገር ችግር ነው ። መነጋገርን ስለምንፈራ ጦርነትን እንመርጣለን ። በመነጋገር ውስጥ የአሳባችን አለ ማሸነፍ ይታየናል ። መሸነፍ ግን ለግለሰቡ ሳይሆን ለእውነት ነውና ሊያስደስተን ይገባል ። መማር ያቆመ መኖር ያቆመ ነው ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” እንዲሉ በጥሩ መጨራረስ መልካም ነው ። “መራቅን የተማርኩት ከመቀራረብ ነው” ይባላል ። እንዳማረበት የሚዘልቅ የለምና በተሰበሩ ግንኙነቶች ሐፍረት ውስጥ አትግቡ ። ይሆናልን ታሳቢ ባያደርግ የሚጀምር ማንም አይኖርም ነበር ፣ አለመሆን ግን ትንሽ ቢያስቆጣም አያጸጽትም ። ሰው ከእግዚአብሔር እየተለየ ነው እንኳን ከእናንተ !
አንድ ጊዜ አታፍስሱት
ሰዎች ቀርበው ሲርቁአችሁ ምን አይተውብኝ ነው ? ትላላችሁ ፤ ወደው ሲጠሉአችሁ ፣ አክብረው ሲያዋርዱአችሁ እልህ ይተናነቃችኋል ። ቅንነታችሁን በሙሉ በአንድ ጊዜ ለአንድ ሰው ካፈሰሳችሁት ትናቃላችሁ ። ተራ በተራ ፍቅርን ፣ ቅርበትን ፣ ቅንነትን ማድረግ ሰዎቹ ዋጋ እንዲሰጡት ያደርጋቸዋል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም.