መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ፈተናው ሲበዛ

የትምህርቱ ርዕስ | ፈተናው ሲበዛ

“ይለቀማል እንጂ በመላ በዘዴ ፣
ለእንክርዳድ ተብሎ ይደፋል ወይ ስንዴ ! ?”

አውድማ ላይ ያለው እህል በመንሽ ይበጠራል ። ነፋሱ እያንገዋለለው ገለባውን ሲወስድ ፍሬው መሬት ይይዛል ። ፈተና በሳልና መሬት እንድንይዝ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ነው ፣ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሶች ፣ ከነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በላይ ብዙ የሚያስተምረውና የሚተክለው በፈተና ማለፍ ነው ። በፈተና መጽናትም ወዳጅ ለአፍቃሪው የሚያሳየው ታማኝነት ነው ። ፈተና ገለባ ጠባያችንን ፣ ገለባ ባልንጀሮችን የሚያስወግድ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነው ። እንደ እኔ የተፈተነ የለም ብለን ስንናገር ግን ፈተናው እየከበደን ይመጣል ። ምክንያቱም በዓለም ላይ ብቻችንን ለስቃይ ተላልፈን የተሰጠን መስሎ ይሰማናልና ። በእኛ ላይ ያለ ፈተና በሁሉም ላይ አለ ። ዛሬ በጣም የምታምኑአቸው ወዳጆች በፈተና ቀን አብረዋችሁ የቆሙት ናቸው ። በፈተና ስንጸና የእግዚአብሔር ወዳጆች እንሆናለን ። ከፈተናዎች የተነሣ ብዙ ሰው ሕይወቱ ደስተኛ አይደለም ። ፈተና ውጤቱ እንጂ ምጽአቱ የሚያስደስት አይደለም ። ፈተናን ሲያልፉት የልብ ሐሤት ይጨምራል ፣ ሲያልፉበት ማሳዘኑ ግን የማይቀር ነው ። በዚህ ዘመን ብዙዎች የሚያልፉበትን ፈተና በጥቂቱ ማየት ያስፈልገናል ።

እርካታ ማጣት የብዙዎቻችን ፈተና ነው ። በእጃችን ላይ ያሉት ነገሮች ትላንት የእንባና የጸሎት ዋጋ የተከፈለባቸው ነገሮች ናቸው ። ዛሬ ግን እንደ ደስታ ሳይሆን እንደ ሸክም እየሆኑብን ነው ። የረሀቡ ዘመን ሲያልፍ ያለመርካት ፈተና ይመጣል ። እርካታ ማጣት ራስንና አጠገባችን ያለውን ሰው እንድናውክ ያደርገናል ። መልሱ ጥያቄ ስለሆነብን ለሰዎች ለመንገር አፍረን ብቻችንን የምንታመመው ቍስል ነው ። እግዚአብሔር ግን አለመርካታችንንም በኀዘኔታ ያየዋል ። ባለመርካት ምክንያት ብስጩ ፣ ሱሰኛ የሆኑ ፣ ትዳራቸውን የፈቱ ፣ ሁሉንም ነገር ሞክሬ ልሙት ብለው ቆርጠው የወጡ ብዙ አሉ ። እንኳን መርዝ መድኃኒትና ምግብም በልኩ ካልተወሰደ አደጋው ከፍ ያለ ነው ። መንፈሳዊ ጥያቄን በቁሳዊ አቅርቦት መመለስ አይቻልም ። እግዚአብሔር የሚሞላውን ክፍተት ማንም ደግ ሰው ሊሞላው አይችልም ። እግዚአብሔርን የሚተካ ምንም ነገር የለም ። እግዚአብሔር የማያስፈልገንም የሕይወት ቀጠና አይገኝም ። የዚህን ዓለም ትልቅነት የጨበጡ ሰዎች ስቃያቸው ከፍ ያለ ነው ። እርሱም አለመርካት ነው ። ብዙ ኮሜድያን በጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ። ብዙ ባለጠጎች መልካቸው ሳይቀር ተዥጎርጉሯል ። ብዙ ዝነኞች በሜካፕ ኃይል የቆሙ ናቸው ። ምስጥ እንደ በላው ቤትና ዛፍ ውስጣቸው ተቦርቡሮ የቆሙ ወገኖች ብዙ ናቸው ። ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “ጌታ ሆይ ለራስህ ስትል ስለፈጠርከን ልባችን በአንተ እስክታርፍ የትም ትባክናለች” ብሏል ።

እርካታ ማጣት እየታገላችሁ ያላችሁ ወገኖች ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ። ዓለም የምታሰቃየው በመጀመሪያ የሚወዳትን ነው ። ወዳጅን የሚያውቀውን ፣ ወዳጅነትን የሚያከብረውን እግዚአብሔርን ተጠጉ ። “ሰይጣን ለወዳጁ አይሆንም” ሲባል ትሰማላችሁ ። በሰዎች ፊት ለማልቀስ ትልቅነታችሁ እንቅፋት ሆኖባችኋል ። ሳይታዘብ ድካማችሁን ለሚሰማው ጌታ በእንባ አዋዩት ። የእርሱ ገበያ መልካም ነው ። የማይገኝበት በረከት የለም ። የሚገርመው በክፍያ ያጣችሁትን ሰላም ከእርሱ ዘንድ በጸጋ ትቀበላላችሁ ።

ሕይወትን መጥላት የብዙዎች ፈተና እየሆነ ነው ። አምባሳደር ራሱን ጠርቶ ወደ አገሩ ቢመለስ ከመንግሥቱ ቅጣት ያገኘዋል ። ሰውም ተራ ነዋሪ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምስለኔ ፣ የጌታ አምባሳደር ሁኖ የተቀመጠ ነው ። ሕይወቱ ላይ ወስኖ ቢሄድ በምድርና በሰማይ ስደተኛ ይሆናል ። አምባሳደር ተጠርቶ ሲሄድ ክብሩ ነው ። “ብዙ ልጆች ብንሄድ ይሻለናል” እያሉ ራሳቸው ላይ ይወስናሉ ። ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤” ቢል ክርስቶስን ናፍቆ እንጂ ፈተናን ሸሽቶ አይደለም ። ፊልጵ. 1 ፡ 23 ። ደግሞም በመጨረሻ የሞተው በሰማዕትነት እንጂ ራሱ ላይ ወስኖ አልነበረም ። ይህ ሐዋርያ ሞትን እየለመነ ስለሚያገለግለው ሕዝብ ግን መቆየትን ፈለገ ። ከደስታው ይልቅ የሌሎችን መዳን ያስቀደመ ነበር ። ራሳቸው ላይ የሚወስኑ ግን ራስ ወዳድ ናቸው ። ምክንያቱም እኔ ይህን ስወስን እናቴ ምን ትሆናለች ( አባቴ ምን ይሰማዋል ? ወዳጆቼስ አይጎዱም ወይ ? የሚል ስሜት የላቸውም ። ኑሮአቸውና አስተሳሰባቸው እኔና እኔ ብቻ ነው ። አንዳንዶቹ ነገር ትተው የሚሞቱ ፣ በደብዳቤአቸው “እናቴ እወድሻለሁ ፣ አባቴ ግን ባንተ ምክንያት ለዚህ በቅቻለሁ” ብለው ትልቅ ዓለት ወርውረው ይሞታሉ ። ይህ ቀጥታ የሰይጣን አማካሪነት ፣ የሲኦል ወራሽነት ያለበት ክፉ አሳብና መንገድ ነው ። በዕዳ ተጨንቀው የሚሞቱ ሰዎች ከሞቱ በኋላ አበዳሪዎቻቸው ቁጭ ብለው ሲያወሩ ያ ሰው አልታየውም እንጂ ብዙ በረከት እንዳለው ይገነዘባሉ ። ሰይጣን ያለንን ነገር እየጋረደ የሌለንን እያጎላ ይፈትነናል። አንድ ባለጠጋ ራሱ ላይ ወስኖ አበዳሪው ልቅሶ ላይ መጥተው፡- “ለካ ይህን ያህል ጭንቀት ሆኜበት ነበር ? ምነው በነገረኝ ፤ እርም ነው ምንም ገንዘብ አልፈልግም” አሉ ።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ወደንና ፈቅደን ወደ ምድር አልመጣንም ። በወሰነ ጊዜ የሚጠራን አምላክ አለ ። እግዚአብሔር የሕይወት ባለቤት ነውና አትግደል የሚል ትእዛዝን ሰጠ ። ራስንም መግደል ኃጢአት መሆኑን ነገረን ። በዚህ ምድር ላይ ዘላለማዊ ፈተና የለምና በርቱ ። ያቺ የመኖር አየር የምታጥራችሁ ሰዓት ስትመጣ ወደ አባቶች ፣ ወደ መምህራን ወደ ወዳጆች ሂዱ ። ትልልቅ ፈተናዎች በትንሽ ቃል ይፈራርሳሉ ። እናንተ የእናንተ ብቻ አይደላችሁም ። ስለ ራሳችሁ መኖርን ብትጠሉ እንኳ ስለሚወዳችሁ እግዚአብሔር ፣ ስለሚያስቡላችሁ ወዳጆች መኖር አለባችሁ ። ያቺ ውሻችሁ እናንተ ከሌላችሁ ትሞታለች ፣ አበባችሁ ትጠወልጋለች ። እንኳን የእናንተ ህልውና የዝንቦች ህልውናም ተፈጥሮን ያቻችላል ። ከቦታችሁ ስትነሡ የእናንተ ቦታ የዓለም ክፍተትን ይፈጥራል ። እናንተን የሚመስል የለምና ማንም አይተካችሁም ። እናንተ የሥላሴ ዕንቈዎች አትሙቱ ኑሩ ።

ይለቀማል እንጂ በመላ በዘዴ፣
ለእንክርዳድ ተብሎ ይደፋል ወይ ስንዴ!?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ