መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ምክር ለሰሚው » ምክር ለሰሚው -36

የትምህርቱ ርዕስ | ምክር ለሰሚው -36

ወዳጄ ሆይ !

ኀዘነተኛ ያደረገህ የሰዎች ጉድለት ሳይሆን ያንተ ከመጠን በላይ መጠበቅ ነው ። ያንተ የሆነውን እንዲነኩብህ አትፈልግምና የሰዎች የሆነውን አትንካ ። መልካምነትህን የሰሙ ካንተ ማረጋገጥ ሲፈልጉ ፣ ክፉነትህን ሲሰሙ ግን ካንተ ማረጋገጥ አይፈልጉምና አትደነቅ ። ስለ ሌሎች በሚወራበት ጠረጴዛ ላይ አትቀመጥ ፣ እልፍ ስትል ስላንተ ይወራልና ። በጎ ሥራህን ሰዎች ሲያወሩት ክብርህ ፣ አንተ ስታወራው ውርደትህ ነው ። ስህተቱን ሲያውቅ የሚደሰት የመማር ዓላማ ያለው ሰው ነው ። ሰዎች ስላንተ ክፉ ሲያወሩ የክት ልብስህን እያወጣህ ልበስ ፣ በሚጠሉህ ፊት ደስተኛ ሁን ። የማይሠራ ሰዓት እንኳ በቀን ሁለት ጊዜ ትክክል ነው ይባላል ። ሦስት ሰዓት ላይ ቆሞ ከሆነ ጠዋትና ማታ ሦስት ሰዓት ላይ ትክክል ይሆናል ። ሰዎችም ወደቁ ብለህ ምንም መልካም ነገር የላቸውም አትበል ። በጉጉት ከምትጠብቀው ይልቅ በድንገት የምታገኘው ደስታን ይሰጥሃል ።

ወዳጄ ሆይ !

አዲሱ ቀን የተሰጠህ አሮጌ ስህተትህን እንድትቀጥልበት ሳይሆን እንድትመለስበት መሆኑን እወቅ ። እንደገና ዕድል ማግኘት በዓለም ላይ ውዱ ነውና የበደልካቸውን ካስ ፣ የወሰድከውን መልስ ። ፈርቶ ከመሞት ደፍሮ መሞት የቅጽበት መከራ ነው ። በሕይወት ውስጥ ትልቅ ትምህርት በሁኔታዎች ውስጥ መረጋጋት ነው ። ቃል ገብቶ ከማይፈጽም ፣ ቃል ሳይገባ የሚተገብር ይበልጣል ። ቃል መግባትና መፈጸም ሁለት ጊዜ ማስደሰት ነው ። በእግዚአብሔር ፊት የሚንበረከክ ፣ በኃያላን ፊት መቆም ይችላልና ሁልጊዜ ለጌታህ ስገድ ። ሁሉም ነገር በውበት ቢቀጥል ኖሮ የትላንቷ አበባ ዛሬ ላይ አትጠወልግም ነበር ። አንተም መልኬ ጠቆረ ፣ ኪሎዬ ቀነሰ ብለህ አትገረም ። ተበድለህ ይቅርታ መጠየቅ ባለጌዎችን እንዳይለወጡ ማደደር ነው ። ሁልጊዜ መፋቀር የለምና ሁሉንም ነገርህን አታሳይ ። በማውራት የሚያምኑ ዝምታን አላዋቂነት ብለው ይጠሩታል ። ለመስማት አትፍራ ፣ እውቀትን ፣ እውነትን ፣ ፍትሐዊነትን ፣ አዘኔታን የምታገኘው ሰዎችን ስትሰማ ነውና ።

ወዳጄ ሆይ !

በወንበር ላይ ተቀምጠህ ዓለምን መዞር ትፈልጋለህ ( መጽሐፍ አንብብ ። ዓለምን በእግራቸው የሚዞሩ ካላቸው እውቀት ፣ በመጽሐፍ የሚያዩአት ያላቸው ማስተዋል ይበልጣል ። መጽሐፍን መግለጥ ሕይወትን ፊት ለፊት መግለጥ ነው ። ካላነበብህ አንድ ሕይወት ኖረህ ታልፋለህ ፣ ስታነብ ሺህ ሕይወት ኖረህ ታልፋለህ ። በቤትህ ትልቅ ቴሌቪዥን ሳይሆን ትልቅ የመጽሐፍ መደርደሪያ ትከል ። ቴሌቪዥን ዓለምን ፣ መጻሕፍት ራስህን ያሳዩሃል ። ከስጦታ የሚበልጠው መጽሐፍን ለሰዎች መስጠት ነው ። ነጻ ሰው ለመሆን ዘመናዊ ፣ ነጻነት ያለው ሰው ለመሆን አንባቢ ሁን ። አለማወቅ ሰው ራሱን የሚያስርበት ትልቁ ወኅኒ ቤት ነውና በማንበብ ራስህን ፍታ ። መኖር ያለ ንባብ ጎዶሎ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

አንድ ሰው እንዲህ አለ፡- ሕይወት ሞትን እንዲህ ስትል ጠየቀችው፡- “ለምንድነው ሰዎች እኔን የሚወዱኝ ፤ አንተን ግን የሚጠሉህ?” ሞትም መለሰላት፡- “ምክንያቱም አንቺ ውሸት ነሽ ፤ እኔ ደግሞ መራር እውነት ነኝ!” አለ ይባላል ። አለሁ ማለት ፣ አለኝ ማለት ውሸት ነው ። ጠዋት ለማታ መቀጣጠር ሐሰት ነው ። በቅጽበት ብዙዎች ታይተው ይጠፋሉ ። የሰው ሕይወት በምድር ላይ እንደ ርችት ድምቀት ነው ። ርችት ከፍታ ፣ ውበትና ብርሃን አለው ። ይህ ሁሉ ግን ለቅጽበት ነው ። ሰውም ሊሾም ሊሸለም ፣ ሊያብብ ሊፈካ ፣ ሊስቅ ሊጫወት ይችላል ። ይህ ሁሉ ግን ሐሰት ሊሆን ይችላል ። አንድ እውነት አለ ፣ እርሱም መሞታችን ነው ። አንተ ግን እንዲህ በል፡-
እኔ መንገደኛ ተሸኝቶ አዳሪ ፣
ምን ክፉ አናገረኝ እንግዲህ ከቀሪ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ