ወዳጄ ሆይ!
አሸካሚው ቀላል ነው ሲል ተሸካሚው ከባድ ነው ይላል ። ለሰዎች ድርሻና አደራ ስትሰጥ አብረህ ሸክሙን መሸከም ፣ በአሳብና በጸሎት መርዳትን አትርሳ ። “ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው” እንዲሉ አንተም ሌሎችን ከመከርህ በኋላ፡- “ሌላውን በመከርኩበት እንዳልፈተን እርዳኝ” ብለህ ጸልይ ። እውነት የምትሰጥህን ግርማ ሞገስ ልብስ ሰፊህ አይሰጥህም ። ውሸት መናገር ካልፈራህ እውነት መናገር አስፈሪ አይደለም ። ለመናገር የፈራኸውን እውነት ገና አላወቅኸውም ማለት ነው ። ቁንጅና ሐሰት ስለሆነ ውድድር ይዘጋጅለታል ፣ እውነት ግን እኩያ የለውምና አይወዳደርም ። የበዛ ውበት የማስጠላት ያህል ነው ። በጣም ቆንጆ የሆነውን መወዳጀት ጥበቃውና ጥንቃቄው አድካሚ ሥራ ይሆናል ። ቆንጆ ዘማ እንጂ ዘማሪ መሆን ይቸገራል ፤ ሰይጣን የወደቀው በውበቱ ነው ። በሕይወት ውስጥ ገንዘብ የሚገዛው ርካሹን ነገር ነው ፣ ውዱ ነገር በጸጋ የተሰጠ ነው ። ከፈለግህ ማድረግ ትችላለህ ። ዝግ ልብ ስትይዝ መንገዶች ይዘጉብሃል ።
ወዳጄ ሆይ!
ሳትሞክር አልችለውም አትበል ፣ ብዙ ሙከራም ወደ ስኬት ያደርሳልና መሞከርህን ቀጥል ። ከውብ ዓይኖች ይልቅ ውብ ልብህ የዚህችን ዓለም ልክ የምታይበት መነጽር ነው ። እግዚአብሔር የሚታየው በዓይን ሳይሆን በእምነት ነውና የልብህን መስተዋት ከጥርጣሬ አጽዳው ። ከሊቆች ይልቅ ቅኖች ማራኪ ናቸው ። ሊቅ አዋቂ የሚባለው አለማወቁን በማወቁ ሲሆን አላዋቂም ከሚታወቀው የማይታወቀው ብዙ መሆኑን ባለማወቁ የሚለፈልፍ ነው ። “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” እንዲሉ ትንሽ እውቀት አፍ እንጂ ጆሮ የለውም ። ስልጡን የሚባል ሰው ድንበሩንና ገደቡን የሚያውቅ ነው ። መሳሳት የመሥራትና የመሞከር ውጤት ነውና በመሳሳትህ አትጸጸት ። ከመልከ ቀና ጋር አንድ ሰዓት መቀመጥ አንድ ደቂቃ መቀመጥ ፣ ከአዋቂ ጋር አንድ ሰዓት መቀመጥ አንድ ቀን መቀመጥ ከሆነብህ ፈራሽ ማንነት ይዘሃል ማለት ነው ። እሳቱን የማትለኩስ ከሆነ እንጨቱን አትፍለጥ ፣ የማታስተምር ከሆነ ሰዎችን አትሰብስብ ፣ የማትቀድም ከሆነ ራእይህን አትተርክ ፣ የማትቀድስ ከሆነ ደወል አትደውል ።
ወዳጄ ሆይ!
አዲስ አሳብን ለመስማት አትፍራ ። አዲስነቱ ላንተ እንጂ ለሰው ዘር አይደለምና ። ዓላማ ያለውን የሚያቆመው ሠራዊት የለምና በዓላማ ኑር ። እናትህና ሚስትህ በፍቅር ፣ ጠላቶችህ በማዋከብ እንዲያቆሙህ አትፍቀድ ። ሰውን የሚያኖረው ጉልበቱ ሳይሆን መልካም እልሁ ነውና ውስጥህን ሽንፈት አታሰማው ። ትምህርት የፍቅር ስጦታ እንጂ የአለቃ ቀንበር አይደለምና ማስተማር ዕድልህ ሲሆን ፈትፍተህ አባብለህ ስጥ ። ባንተ ደግነት የምታስተምረው ትምህርት ይወደዳል ፣ ባንተ ብስጩነት ትምህርቱ ይጠላል ። ቅኔን የማያውቅ ፣ ሰምና ወርቅን የማይለይ ትውልድ ከማሽን የተለየ አይደለም ።
ወዳጄ ሆይ!
ስልጣኔዎች ሁሉ አስደሳች የሚሆኑት በነጻነት ሲሠሩ ነው ። ነጻነት በሌለበት አገር ከእግሮች ይልቅ አእምሮዎች ይታሰራሉ ። በግድ ሥልጣኔን አምጡ ያሉ አገሮች ቢሰለጥኑና የጦር መሣሪያ የበላይነትን ቢይዙም የዜጎቻቸው እስር ቤት ናቸው ። አንተም አገርን ለመምራት ዕድል ባገኘህ ጊዜ ነጻነት እንደሚተነፍሱት አየር አስፈላጊ እንጂ ቅንጦት መስሎ አይሰማህ ። በታሪክ ሲገዳደል የሚኖር ዛሬን የሚኖርበት ምክንያት የሌለው ነው ። ታላቅ ነገርን ብቻ ሳይሆን ምሳሌ የሚሆንን ነገር ፈጽም ። ደካማ አእምሮ ደካማ አካልን እያዳበረ ይመጣል ፣ የዕለት መታከት የዘመን ፣ የጠባይ ስንኩልነት ባሕርይ እየሆነ ያድጋልና ተጠንቀቅ ። ሌላው እንዲሠራለት የሚፈልግ ሰነፍ ሌላው የእርሱን ምግብ እንዲበላበት አይፈልግም ። ሰነፍ ማለት ለሥራ የደከመ ፣ ለመብል የበረታ ማለት ነው ። ነገ በብሩህ የማትታይህ ከሆነ የዛሬ ደስታህ እንቅፋት አለበት ፣ ስለዚህ ነገን ተስፋ አድርግ ። ወርቅ ብዙ አፈር ተጭኗታል ፣ ማዕድናትም በጥልቀት ይኖራሉ ፣ ዕድልም በማዕበል መካከል ተቀምጣለች ። ከራስህና ከሰዎች ጋር የሚያስተዋውቅህ ማጣት ነውና ማጣትህን ብዙም አትጥላው ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም.