መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰው ውኃ ነው » ሰው ውኃ ነው -2

የትምህርቱ ርዕስ | ሰው ውኃ ነው -2

ውኃ ሲጠፋ ያስጨንቃል

ሰውም እግሩ ሲርቅ ፣ ድምፁ ሲጠፋ ፣ አየሁት የሚል ወገን ሲታጣ እንቅልፍ ይነሣል ። ውኃ ሳለ ያድፋፉታል ፣ ሲጠፋ ግን ዋጋው ከወርቅ ይንራል ። እንደ ርካሽ ቆጠሩት ሰው ፣ አይሄድም ተብሎ የደመደሙበት የጠፋ ቀን ልብን በስጋት ያደክማል ። ዐርባ ዓመት ልጃቸውን የሚፈልጉ ፣ ስድሳ ዓመት ተፈላልገው የተገናኙ በዘመናችን አሉ ። እንደውም የሰው ታሪክ መጥፋትና መጠፋፋት መሆኑን እያየነው ነው ። ሰው ስጦታችን ነውና አክብረን መያዝ ይገባናል ። ከሄደ በኋላ ላይገኝ ይችላል ። እግራችንን አንካሳ ያደረጉት ሳናስደስታቸው የሞቱ ሰዎች ናቸው ። ክፉ የምንላቸው በእኛ የፍጹምነት መስፈርት መዝነናቸው እንጂ ክፉ አልነበሩም ። ሌሎችን ስናይ የነቀፍናቸው ሰዎቻችን ቅዱስ እንደ ነበሩ እንረዳለን ።

“አይመልስህ” ብለው ረግመውት ከቤት የወጣ ልጅ “ምነው አመሸ (” ተብሎ ይናፈቃል ። ሳለ ብዙ እንከን ያወጣንለት ወዳጅ ሲሞት ደግነቱ ኩልል ብሎ ይታያል ። የሚቆጣን ሰው ፣ የሚገሥጸን ወዳጅ ስናጣው “ለካ ለእኔ ብሎ ነው” ያሰኛል ። አሁን የፈለግነውን ብንሆን ስለ እኛ ግድ የሌለው ሰው በዙሪያችን ሲከበን ያ ወዳጄ ደውዬለት ምነው በተቆጣኝ እንላለን ። የሚቆጣንም ወገን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። የሚቆጡን የበለጠ እንድናምር የሚፈልጉ ናቸው ። ይቆጫል ፣ ያላነሣነው ስልክ ፣ ያልጠየቅነው ወላጅ ፣ ያልረዳነው ጓደኛ ረመጥ ሆኖ ይፋጃል ። ከጊዜ ጋር እንዳንተላለፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ።

ውኃ ብዙ ቢሆንም ትንሽ ነው

እኛ ድሆች ነንና ስለ ነዳጅ እናስባለን ። ባለጠጋ አገሮች ግን ውኃን ይሰጉታል ። ውኃን ከቆሸሸ በኋላ እንደ ገና አጽድተውና አክመው ይጠቀሙታል ። ውኃ አያድፋፉም ፣ መታጠቢያ ቤት የውኃ ሽንት ሸንተው ከድነው ይወጣሉ ቀጣዩ ተጠቃሚ ተጠቅሞ ውኃ ይለቅበታል ። ያደጉ አገሮች ያደጉት በዚህ ሥርዓት ነው ። ውኃ ብዙ ነው ፣ ግን እንደ ውኃ ትንሽ የለም ፣ የቀጣዩ ዘመን ፈተና ውኃ ሊሆን ይችላል ። ሰውም ብዙ ነው ፣ ስምንት ቢሊየን በጣም ብዙ ነው ፤ ከዚያ ውስጥ የእኛ ነገር የሚያሳስበው በጣም ትንሽ ነው ። ከስምንት ቢሊየን ሕዝብ ስለ እኛ የሚጨነቅ ስንት ሰው ነው ( ብንል ሰው ትንሽ ነው ። ያሉንን ሰዎች ቆጥበን መያዝ አለብን ። በምድር ላይ ትልቅ ሀብት ሰው ነው ። ዘፋኞች ድሆች ናቸው ፣ ሰው ግን ስላላቸው ተርበው አያድሩም ። ሰው ከወርቅ በላይ ሀብት ነው ። ሰው ከእኛ ባሻገር የሌሎችም ነውና ልንቆጥበው ልንሰስትለት ፣ “ይበቃሃል ለፍተህልናል” ልንለው ይገባል ። ለእኛ ወንድም ቢሆነን ለሚስቱም ፣ ለልጆቹም ፣ ለእናቱም መቆጠብ አለብን ። እኔ ብቻዬን ላጥቃው ብሎ መነሣት ነውር ነው ። ደግሞም “ቸር ሲያጠቁት ቢስ ይሆናልና” እናጣዋለን ።

ውኃ ርቆ ይሄዳል

ውኃ ቅርብ አዳሪ አይደለም ፣ የሚቀላቀለው ካገኘ ፣ ገባር ከገጠመው አገር አቋርጦ ወደ ጎረቤት አገራት ይፈሳል ። ሰው ውኃ ነው ፣ በአሁኑ ሁኔታው አይለካም ። ቢሳካለትም ይህ የመጨረሻ አይደለም ፣ ገና መንግሥተ ሰማያት ይጠብቀዋል ። ቢያጣም የአሁኑ የመጨረሻው አይደለም ። ስንት ምሽትና ንጋት አሳልፈን ዕድሜን ቆጥረናል ። ሰውም ብዙ ደስታና ኀዘንን አሳልፎ በድል ይወጣል ። ሰው ውኃ ነው ፣ ርቆ እንዲሄድ አጋዥ ፣ አበርቺ ፣ አብሮ የሚጓዝ ይፈልጋል ። በአንዳንድ ሰው ውስጥ የተቀመጠ ጸጋና እውቀት ለአገርና ለዓለም የሚተርፍ ነው ። አጋዥ በማጣት ግን የበቀለበት ቦታ ይደርቃል ። ሰው በትንሽ አድናቆት ብዙ ችሎታውን ማውጣት ይችላል ። ትንሽ ድጋፍ ብናደርግላቸው እስከ ልጅ ልጅ የሚተርፍ ግኝት በእጃቸው ያለ ብዙ ሰዎች አሉ ። ሰዎች የሰጠናቸውን ብቻ ሳይሆን ከሰጠናቸው በላይ ይሰጡናል ። ምናልባት በቀጥታ ለእኛ ባይሰጡንም በተዘዋዋሪ ይሰጡናል ። አምፑልን የሠራው ጠቢብ በቀጥታ የረዳውን ሰው አልመለሰለት ይሆናል ። ለዓለም ባበረከተው ስጦታ ግን የደገፉትን ተጠቃሚ አድርጓል ። ሰው ውኃ ነው ርቆ ይሄዳል ፣ ነገር ግን የእኛን ድጋፍ ይፈልጋል ። አንድን ሰው እልፍ ለማድረግ መኖር አለብን ። እኛም መድረሻችንን ቅርብ አድርገነው ገንዘብና ዝና ላይ እንዳንቀር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ስንቱ ሰማይን እያየ ጀምሮ ትዳርና ልጅ ጋ ቀረ ፤ ቤት ሲሠራ የላኛውን ቤት ተወ። አቤቱ በመንፈስ ጀምሮ በሥጋ ከመጨረስ ጠብቀን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ