መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰው ውኃ ነው » ሰው ውኃ ነው -4

የትምህርቱ ርዕስ | ሰው ውኃ ነው -4

ውኃ ቅርብ አዳሪ ነው

ውኃ ሩቅ አስቦ ቅርብ የሚያድር ነው ፣ ሰውም አንዳንድ ጊዜ አሳቡና እግሩ እኩል አይረግጡለትም ። ካሰበው ሳይሆን ከታሰበለት ይውላል ። ያን ጊዜ ያከበረው ሊያዋርደው ይነሣል ። ያለ ምክንያት ከፍ ያደረጉት ያለ ምክንያት ዝቅ ያደርጉታል ። እርሱ የቻለውን ዝቅታ የሚያዩት መሸከም ያቅታቸዋል ። ባለ ቅኔው ፍልስፍናውን ፣ ባለዜማው ማሲንቆውን ያነሡበታል ። ሲናገር ማር የነበረው አሁን እሬት ይሆናል ። እነዚያ ሰቃይ ተማሪዎች ሰፈር ቀርተዋል ። እነዚያ የፈጠራ ችሎታ የነበራቸው የመንደሩ ጠባቂ ሆነው ከርሞ ሲሄዱ ይገኛሉ ። ያ ውበት በቁም ጠውልጓል ። የቅርብ ዘመድ እንጂ የሩቁ ላያስታውስ ረስቷቸዋል ። የሰፈሩ እንግዳ ተቀባይ ሆነው ገና ስንመጣ “አወቅኸኝ ?” ይሉናል ፣ አሁንም ሲጠፋን “የእገሌ ልጅ እኮ ነኝ” ይሉናል ። መልካቸውም ስማቸውም ጠፍቷል ። ዓለም እንደዚህ ናት ።

እመክታለሁ ሲል ዱላው ተሰብሮበት ፣
እራመዳለሁ ሲል መሬት ተንዶበት ፣
ንብርብር ንብርብር እስኪ አትበሉበት ፣
የሰው ወራት አለው ወድቆ የሚነሣበት ።

ውኃ ይፈውሳል

የፈውስ አገልግሎቶች ከብሉይ እስከ ሐዲስ ፣ ከንዕማን እስከ መፃጕዕ ከውኃ ጋር የተያያዙ ናቸው ። ውኃ ጤንነትን መጠበቂያ ነው ። የውስጥ የአካል ክፍል ጨጓራው ፣ ኩላሊቱ ፣ ፊኛው ፣ ደሙ ውኃ ይፈውሳቸዋል ። ቆዳው በውኃ እየጠራ ይመጣል ። ውኃ ድርቀትን ለማስወገድ አስፈላጊ ነው ። የምንወስደው መድኃኒት ነገ መርዝ ነውና ውኃ ለመድኃኒቱ መድኃኒት ነው ። ሰው በጣም ሲበሳጭ ውኃ ቀድቶ መስጠት እንዲበርድ ያደርገዋል ። በእጃችን ላይ ያለው ቆሻሻ የሚወገደውና ለመብላት የምንሰናዳው በውኃ ታጥበን ነው ። ምግቡ መድኃኒት ቢሆንም በውኃ መቀደስ አለበት ። ያለ ውኃ የፍጥረት ቀጣይነት አጠራጣሪ ነው ። ሰው ውኃ ነውና ይፈውሳል ። ከፍቶን ሳለ ፈገግ ብሎ ሲቀበለን ኀዘናችን ይገፈፋል ። በሰው ተጠቅተን የምንፈወሰው በሰው ነው ። በአዳም ሞተን በዳግማዊ አዳም አምላክም ሰውም በሆነው ድነናል ። አምላካችን ያልተዋሐደውን አያድነውም ሲባል ሥጋና ነፍሳችንን ተዋሕዷል ፣ ፍጹም ሰው ሆኗል ማለት ነው ። ስማችን ሲጠፋ ፣ የነበረን ማኅበራዊ መልካችን ሲበላሽ መልሶ የሚቀላቅለን በርታ ባዩ ሰው ነው ። በፈርዖን ያለቀሱ ፣ በሙሴ ተደስተዋል ። ሁለቱም ሰው ናቸው ። በዓለመ መላእክትም በቆሙት መላእክት ረድኤት ምልጃ እናገኛለን ፣ በወደቁት መላእክት እንፈተናለን ። ሁሉም አይከፋም ፣ ጨርሶ አይጨልምምና ዓይናችንን ገልጠን እስኪ እንመልከት ።

ሰው ውኃ ነው ይፈውሳል ። ከልጅ የቀረበ የለም ፣ ልጅ ሲያነደን ባዕድ ያልነው ያበርደናል ። የሚያነደን ሌላ የሚወርሰን ሌላ መሆኑ ይገርማል ። ከልጅም የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ ። የልጄን ነገር አደራ ተብለው የሙት ልጅን ሲንከባከቡ የነበሩትን እናውቃለን ። “በምድር የሰጠሁህን በሰማይ እቀበልሃለሁ” የሚል ኑዛዜ መስማት የተለመደ ነበር ። ኑዛዜ ተቀባዩም ለአደራ በመታጨቱ ፣ ደግሞም አብሮ የመብላት ትርጉምን በማወቁ ደስ ይለዋል ። ውስጣችን ማጣራት ሲያቆም ፣ ደጉን ቀን ከክፉ ቀን ሲያምታታ ፣ በዛሬው ስህተት የትላንቱን ውለታ ሲረሳ ሰው ውኃ ነውና ይፈውሰዋል ። የትላንቱን አስብ በማለት ዞር ብሎ የተዋለለትን እንዲያስብ ያስገነዝበዋል ። በዓለም ላይ የወደዱት ሲርቅ ፣ የጠሉት ሲጣበቅ መኖሩ እርግጥ ነው ። ውስጣችን ብግን ብግን ሲል ሰዎች ያበርዱናል ። “እኔም በቤቴ ይህ አለ” ሲሉን ከማን እበልጣለሁ ? ብለን እንረጋጋለን ። ሰው ያቀዘቅዛል ። ካህኑ ፣ የሥነ ልቡና አማካሪው አብርደው ይሸኛሉ ። አልቅሶ የመጣው እየሳቀ ይወጣል ። እገድላለሁ ብሎ የሰፈር ሰው ወጥቶ ሲለምነው እንቢ ያለው ሰው አንድ ወዳጁ ሲጠራ ኩምሽሽ ብሎ እግር ላይ ይወድቃል ። ከሰውም ሰው ፣ ከወዳጅም ወዳጅ አለውና ። ቤታችን እያነደደን መልሶ አትናደድ ይለናል ። የእኔ የምንላቸው የማይስተኛ ነግረውን “በል እንቅልፍ ተኛ” ብለውን መኝታችን ላይ እሾህ ጎዝጉዘው ይሄዳሉ ። በእኩለ ሌሊት ደውለንላቸው በምክራቸው የሚያስተኙን እነዚያ ፈዋሾች የሚረሱ አይደሉም ። ሰው መድኃኒት ነው ። የሚያነጋግራቸው ሰው በማጣት በብቸኝነት የሚሰቃዩ ፣ ጭር ባለ ሰፈር የሰው ድምፅ ናፈቀን የሚሉ ብዙዎች ናቸው ። ሰው መድኃኒት ነው ። የሚያነጋግር ሰው በማጣት የመርሳት በሽታ ውስጥ የገቡ አሉ ፣ እናሳምራለን ብለው ወላጆቻቸውን ፈረንጅ አገር ወስደው አዳክመው የሚልኩ ልጆች አያሌ ናቸው ። እነዚያ አረጋውያን ማንም በማያውቃቸው አገር ከመኖር በአገራቸው ቢኖሩ ፈላጊያቸው ፣ አስፈላጊነታቸው የጎላ ሆኖ ይታያቸዋል ። ልቅሶው ሰርጉ የሕይወት አካል ነውና ያነቃቃቸዋል ። ሰው ከነክፋቱ መድኃኒት ነው ። መድኃኒትም የጎንዮሽ ጉዳት አለው ፣ ሰውም የሚደክምበት ጠባይ ይኖረዋል ። ከሰው ጋር የሚኖረው ተሟልቶ ሳይሆን ችሎ ነው ። ሌላውን ስላላየህ እንጂ እንዳንተ ሚስት ቆንጆና ጎበዝ የለም ። ሌላውን ስላላየሽ እንጂ እንዳንቺ ልጆች ጭምት ፣ የሚቀናባቸው ብላቴናዎች አይገኙም ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ